Site icon ETHIO12.COM

የ3.5 ሚሊዮን ብር ተሽከርካሪ በጨረታ አሸንፎ የወሰደው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

የ3.5 ሚሊዮን ብር ተሽከርካሪ በጨረታ አሸንፎ የወሰደው ግለሰብ ያቀረበው ሰነድ ሐሰተኛ ሆኖ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር ዋለ


ከ3 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው ተሽከርካሪ በጨረታ አሸንፎ የወሰደው ግለሰብ ያቀረበው ሰነድ ሲረጋገጥ ሐሰተኛ ሆኖ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ወንጀሉን የፈፀመው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለጨረታ ባቀረባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ተጫራች ሆኖ በመሳተፍ ነው፡፡

ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው በዚሁ ጨረታ ላይ የተሳተፈው ተጠርጣሪው፤ ለማስያዥያነት በዳሽን ባንክ ስም የተዘጋጀ ሐሰተኛ ሲፒኦ እንዲሁም ጨረታውን ካሸነፈ በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መስቀል ፍላወር ቅርንጫፍ 3 ሚሊዮን 565 ሺህ ብር ገቢ ተደርጓል የሚል ሐሰተኛ ደረሰኝ ለድርጅቱ በማቅረብ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2-B87869 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪ ወስዶ ከአካባቢው መሰወሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሰነድ የማረጋገጥ ስራ በሚሰራበት ወቅት ጨረታውን አሸንፎ ተሽከርካሪውን የወሰደው ግለሰብ ያቀረበውን ሰነድ ትክክለኛነት ተጠራጥሮ ለፖሊስ ካመለከተ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል ግለሰቡን ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር በማዋል እና የሰነዱን ሐሰተኛነት በማረጋገጥ በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል።

ተቋማት በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀርቡላቸውን ገንዘብን ተክተው የሚሰሩ እና ከገንዘብ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሌሎች ሰነዶች አስቀድመው በማረጋገጥ ሊፈፀምባቸው ከሚችል ወንጀል ራሳቸውን ሊከላከሉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል።

Exit mobile version