አብይ አሕመድ አዳነችን ቀነ ገደብ አስቀምጠው ሪፖርት አንዲያቀርቡ አዘዙ፤ ቢያንስ ፩ ቢሊዮን ብር ተሰርቋል

ሰሞኑን የአዲስ አበባ መስተዳድር ለከተማዋ አስመጣሁት ካላቸው አውቶቡሶች ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ብር መመዝበሩ ተነገረ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስድስት ቀን ውስጥ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ጉዳዩ ከንቲባዋን በቀጥታ የሚመለከት ነው ተባለ።

የአዲስ አበባ መስተዳድር ከቻይና ያስገባቸው 100 አውቶቡሶች ግዢ ጉዳይ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል። መስተዳደሩ እንደሚለው አንዱ አውቶቡስ የተገዛው በ19 ሚሊዮን ብር ወይም 355ሺህ ዶላር አካባቢ ነው። የ200ዎቹ ድምር ዋጋ ደግሞ 3.8 ቢሊዮን ብር ወይም 71 ሚሊዮን ዶላር ነው። አውቶቡሶቹ ይህንን ያህል ለምን እንዳወጡ ለሚጠየቀው ጥያቄ የአዲስ አበባ መስተዳደር የሚሰጠው ምላሽ አውቶቡሶቹ ልዩ ናቸው የሚል ሲሆን ለዚህም የሚከተለውን ዝርዝር ቀርባል።

በዓለም ባንክ ድጋፍ የአንድ መቶ አውቶቡሶች ግዥ ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ አውቶቡሶቹ ሙሉ በሙሉ በአውሮፓ ስታንዳርድ ተጠናቀው የሚገቡ እያንዳንዱ አውቶቡስ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበት ግዥው የሚፈፀም ይሆናል ተብሏል፡፡ የአውቶቡሶቹ ግዥ ተፈፅሞ ሲጠናቀቅም ለአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የሚሰጡ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አውቶቡሶቹም የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ እና አሁን የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል ነው የተባለው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ ምቹ፣ አስተማማኝና ተደራሽ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የብዙሃን ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (ኤ ኤም ኤን ) ሰኔ 21/2013
 • በሀይገር ካምፓኒ የተመረቱና ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ አቅራቢዎች መቅረብ መቻሉ
 • ለአካል ጉዳተኛ በልዩ ሁኔታ አጋዥ ሆነው የተሰሩ እና ዊልቸር ተጠቃሚ ለሆኑ የሚልቸር ማቆሚያ (ማሰሪያ) ያላቸው መሆኑ
 • በቴክኖሎጂ ቁጥጥር ለማድረግ ሲስተም የተገጠመላቸው መሆኑ
 • ተሳፋሪን ለመጫን ሲቆሙ ከመሬት ወለል ዝቅ ብለው ምቹ በሆነ መልኩ የሚጭኑ
 • ርዝመታቸው 12 ሜትር ፣ ቁመቱ 3.4 ሜትር እንዲሁም ስፋታቸው 25 ሜትር ነው
 • 40 ሰው በወንበርና 30 ሰው ያለ ወንበር በድምሩ 70 ሰው በተንደላቀቀ ሁኔታ የመያዝ አቅም ያለው
 • እንደየመንገዱ ባህሪ (ሁኔታ) ዝቅ እና ከፍ እያሉ የተሳፋሪን ምቾት ጠብቀው የሚጓዙ
 • ተሳፋሪ በጉዞ ላይ እያለ የUSB PORT (ሞባይል ቻርጅ) ማድረግ የሚያስችል ሲስተም አለው
 • የቻንሲ አካላት (ካንቢዎ፣ ሞተርና ኤርባግ ) በቀላሉ እንዳይጎዳ ጠንካራ ብረት የተገጠመላቸው
 • ተሳፋሪዎች በድምፅ የደረሱበትን ቦታ መረጃ የሚሰጡ
 • አውቶብሶቹ ሙሉ በሙሉ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ
 • የተሳፋሪውን እንቅስቃሴና ደህንነት በካሜራ መቆጣጠር የሚችል
 • የሞተር ሙቀትን የመከላከል አቅም ፋን (ማቀዝቀዣ) የተገጠመላቸው መሆኑ ልዩና ፍፁም ዘመናዊ እንደሚያደርጋቸው ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል በማለት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአስር ቀን በፊት በፌስቡክ ገጹ አብራርቷል

ይህንን አወዛጋቢ ጉዳይ በተመለከተ የፋና ብሮድካስት ጋዜጠኛ የሆነው ዳዊት መስፍን የከተማዋን የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ምትኩ አስማረን እና የግዢ ክፍል ኃላፊውን መንግሥቱ አጥናፉን አነጋግሮ ነበር። ጣቱን በተጠያቂዎቹ ላይ ከማነጣጠር ይልቅ የቤት ሥራውን በተገቢው ሠርቶ የጥያቄ ሸጉጥ ቢያነጣጥርባቸው የተሻለ ነበር የሚሉ አስተያየት ሰጪ “ዳዊት ይጠይቃቸው የነበረው ወይ ተጽፎ የተሰጠውን ነው ወይም ከጠየቀ በኋላ መልሱን ከካሜራ ውጪ እያሳያቸው ነበር” በማለት ከተማው ሚዲያውን መጠቀሚያ እንዳደረገው ይናገራሉ። ሙያዊ ምርመራ ያደረገውና ቃለ ምልልሱን የሰማው ኢንጂነር ፋሲል ሁለቱ ባለሥልጣናት ገዢ ሳይሆን ሻጭ ነበር የሚመስሉት፤ ለገዢ ሳይሆን ለሻጭ ነበር ይከራከሩ የነበረው በማለት አስተያየቱ ሰጥቷል።

ሁለቱ ኃላፊዎች ተዝናንተው የሰጡት መልስ በአብዛኛው አውቶቡሶቹ እንዴት ልዩ እንደሆኑ በመግለጽ ነበር። ከዚህ በተረፈ ቃለ ምልልሱ የተጠናቀቀው ተጠያቂዎቹ የተለመዱ “እንደ አጠቃላይ፣ እንደ ከተማ፣ እንደ ተጠቃሚ፣ እንደ … ከተማው አቅጣጫ አስቀመጠ፣ ወዘተ” በሚሉ የካድሬ ቃላትና አሰልቺ ወሬ እንደነበር ሌላ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል።

See also  ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ - ኤሌክትሪክ ለማሰራጨት ርዥም ጊዜ ይፈጃል

በዘርፉ የ21 ዓመት ልምድ ያለውና በትምህርቱ ሜካኒካል ኢንጂነር የሆነው ፋሲል ሽፈራው ከ21 ዓመት ልምዱ 12 ዓመት ከጨረታ ሥራ ጋር በተያያዘ የሽያጭ ኢንጂነር ሆኖ ሠርቷል፤ የጨረታ ሥራ ከፍተኛ ባለሙያ ነው። ነጻ ውይይት በተሰኘው ዩትዩብ ላይ ስዩም ተሾመ አነጋግሮት ነበር። ምሥጢሩን ለመተንተን በደንብ ተዘጋጅቶ የመጣው ባለሙያ እያለ ስለ ጉዳዩ ምንም ዕውቀት የሌለው ስዩም ከተጠያቂው ፋሲል የሚሰማውን ጥራዝነጠቅ መረጃ እየለቀመ የራሱ ትንታኔ እያስመሰለ ውይይቱን በተደጋጋሚ ሲደናቅፍ ቢቆይም ፋሲል በርካታ ነገሮችን በጨዋነትና በድንቅ ሙያዊ ትንተና አብራርቷል።

ኢንጂነር ፋሲል የአዲስ አበባ መስተዳድር በልዩ ትዕዛዝ ያሠራሁት ነው የሚለውን መዘርዝር ይዞ ያንኑ መዘርዝር እንደ ገዢ ሆኖ ወደ ቻይናዊው ካምፓኒ የአንድ ባስ ዋጋ ይጠይቃል። ፋሲል እንደሚለው ከዋጋው ሌላ ለማስመጣት፣ ለወደብ፣ ለመጫን፣ ለማስተላለፍ፣ ወዘተ ይከፈላሉ የሚባሉትን ክፍያዎች በሙሉ የአዲስ አበባ መስተዳድር ሊከፍል ይችላል ከሚለው በላይ እያደረገ ነው የአንዱን አውቶቡስ ዋጋ የሠራው። እንደ አብነት ለመጥቀስ ከጅቡቲ ወደብ ባሶቹን እየነዱ ቢያመጧቸውም እርሱ ግን ተጭነው ቢመጡ በሚል ነው የዋጋ ሥሌቱን የሠራው።

ኢንጂነር ፋሲል በሠራው እና እጅግ በተቀናጣ የዋጋ ሥሌት ትርፍ ሳይጨምር የአንድ አውቶቡስ ዋጋ ቀረጥና ግብር (ቫት) የማይከፈል ከሆነ 9.7 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ነው። ቀረጥና ግብር ይጨመር ቢባልና ትርፍ ባይታሰብ አንዱን አውቶቡስ በ11.2 ሚሊየን ብር ማስገባት ይቻላል። እዚህ ዋጋ ላይ የተለመደው 12% ትርፍ ይታሰብ ቢባልና በዋጋው ላይ ቢሰላ የአንዱ አውቶቡስ አዲስ አበባ ላይ የማስረከቢያ ዋጋ 12.4 ሚሊየን ብር ነው የሚመጣው። ይህ ማለት አስመጪው በአንድ ባስ 1 ሚሊየን ብር ወይም ከ200 ባሶች 200 ሚሊየን ብር ንጹህ ትርፍ ቢያገኝ በሚል ሥሌት ነው። ትርፉ በ12% ታስቦ ግን ቀረጥና ታክስ የማይከፈል ከሆነ የአንዱ አውቶቡስ ዋጋ 10ሚሊየን ብር ይሆናል። ትርፉን ከፍ አድርጎ በ20% ቢሰላ እንኳን ቀረጥና ግብር የማይከፈልበት የአንዱ ባስ ዋጋ 10.8 ሚሊየን ብር ሲሆን ቀረጥና ግብር የሚከፈል ከሆነ ደግሞ የአንዱ አውቶቡስ ዋጋ በ20% ትርፍ ሥሌት 13.3 ሚሊየን ብር ይሆናል።

ኢንጂነር ፋሲል ሽፈራው

የአዲስ አበባ መስተዳድር ግን አንዱን አውቶቡስ ገዛሁ ያለው በ19 ሚሊየን ብር ነው። በትንሹ የ5 ሚሊየን ብር ልዩነት ከፍ ካለ ደግሞ የ7 ሚሊየን ብር ልዩነት ከእያንዳንዱ አውቶቡስ ላይ አለ። ሌላ መጠቀስ የሚገባው ነገር እነዚህ አውቶቡሶች በብዛት እንደመገዛታቸው ለ200 አውቶቡስ ተመሳሳይ ዋጋ ሳይሆን ከብዛት የተነሳ ያነሰ ዋጋ እንደሚሰጥ መገመት ይቻላል።

See also  በሳምንት ሶስት ቀናት በኦሮሚያ ባለስልጣኖች የህዝብ ጥያቄ አድምጠው ምላሽ እንዲሰጡ ታዘዘ፤ተቆጣጣሪ ግብረሃይል ይመደባል

ባለሙያው ፋሲል ሌላው በዝርዝር ያስረዳው የጨረታውን አካሄድ ነው። በተለይ በመጀመሪያውና ሁለተኛው ጨረታ አሸናፊ የነበረው ወረታ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ከግዢው ከተወገደ በኋላ ሦስተኛው ውሱን ጨረታ የተካሄደው በጥሪ ነው። ውሱን ጨረታን አሠራሩ የሚፈቅድ ቢሆንም ለጨረታ ከተጋበዙት ስምንት ድርጅቶች ውስጥ 3ቱ እንደማይጫረቱ የታወቁ ሲሆን ሌሎቹ ሦስት ድርጅቶች ምንም የበቃ ሙያ እና ልምድ የሌላቸው እንዲያውም የአስመጪነት ፈቃድ ካወጡ አንድ ዓመት አካባቢ ዕድሜ ያላቸው ናቸው።

መጨረሻ ላይ በላይነህ ክንዴ ቴክኒኩን ባለማለፉ የወደቀ ሲሆን ለፋይናንስ ያለፉት ሁለት ተጫራቾች ናቸው። እነዚህም ኤሊያስ ሳኒ ዑመር እና ያደታ ጁነዲን በክሪ (ብራይተን ትሬዲንግ) ናቸው። ከመጨረሻው ተጫራች ጋር የቀረበውና 22 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያቀረበው ኤሊያስ ሳኒ ዑመር በኢትዮጵያ ውስጥ መኪና አስመጪነት ይቅርና በአጠቃላይ በአስመጪነት ያልተመዘገበ ነው። የጨረታው አሸናፊ ያደታ ጁነዲን በመኪና አስመጪነት የተመዘገበው ሁለተኛው ጨረታ የወጣ ሰሞን ነበር። ከንቲባዋ አዳነች ያመሰገኑት የያደታ ጁነዲን በክሪ ብራይተን ትሬዲንግ ጨረታውን አሸነፈ ተብሎ አንድ አውቶቡስ እጥፍ በሚያክል ዋጋ እንዲያስመጣ ተፈቀደለት።

ጥያቄው እንዲህ ጨረታውን እንዲያሸንፍ የተለፋለት ያደታ ጁነዲን ማነው? የሚለው ነው። የጥቅም ትሥሥሩ ከእነማን ጋር ነው? ከከንቲባዋ ጀምሮ እስከ ታች ትራንስፖርትና ግዢ ክፍል ይህንን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ተሳትፏቸው ምንድነው? የሚሉት መመለስ የሚገባቸው ጥያቄዎች ናቸው።

በትህነግ ዘመን ይህንን መሰል ጉዳይ አይደለም በትኩሱ ዘመናት ከተቆጠሩ በኋላ እንኳን መጠየቅ ዋጋ የሚስከፍል ከመሆኑ አንጻር ይህ በዚህ ዘመን በሚዲያ ለሕዝብ መቅረቡ ይበል የሚያሰኝ ለውጥ ነው። ሊደፋፈርና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ ነው።

እነዚህ አውቶቡሶች ከመገዛታቸው በፊት በዕቅድ ላይ በነበረበት ወቅት አዲስ ሚዲያ ሰኔ 21፤ 2013ዓም (ጁን 28፣ 2021) የሚከተለውን ዜና አስነብቦ ነበር፤ “በዓለም ባንክ ድጋፍ የአንድ መቶ አውቶቡሶች ግዥ ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። አውቶቡሶቹ ሙሉ በሙሉ በአውሮፓ ስታንዳርድ ተጠናቀው የሚገቡ እያንዳንዱ አውቶቡስ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበት ግዥው የሚፈፀም ይሆናል ተብሏል”።

See also  "ጌታቸው ረዳ ዛሬም መንታ ምላሳቸው እንደተሳለ ነው"

ይህ ከአንድ ዓመት ከሰባት ወር በፊት የወጣው መረጃ የሚጠቁመው የአውቶቡሶቹን የመግዣ ገንዘብ የመጣው ከዓለም ባንክ መሆኑን እና የአንዱ አውቶቡስ ዋጋ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊየን እንደሚያወጣ ነው። ግዢው ተፈጽሞ በከንቲባ አዳነች የተረከቡት አውቶቡሶች የአንዱን ዋጋ 19 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ነው። ጭማሪው በትንሹ ከእጥፍ በላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ጉዳይ ተጣርቶ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው አስቸኳይ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያስተላልፉት እርምጃ ወይም ቆራጥ አመራር በእርግጥ ከሕዝብ ጋር መወገናቸውን የሚሳይ ነው ተብሎ ይታመናል። በተለይም በሌብነቱ የከተማዋን ከንቲባ ከሥልጣን እስከማንሳት መጀገን እንደሚገባቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። አለበለዚያ ይህ በቸልታ የሚታለፍ ከሆነ ሌሎች እጅግ በርካታ ሌቦችን ለማምረት ምቹ መደላድል የሚፈጥር ይሆናል። እርሳቸውንም የሌባ ተባባሪና ደጋፊ የሚያስብላቸው ይሆናል።

ኢንጂነር ፋሲል ያቀረበውን ትምህርት ሰጪ ሙያዊ ትንታኔ በሁለት ቪዲዮ የቀረበውን መመልከት ስለ ጉዳዩ የበለጠ ግንዛቤ ይሰጣል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ    

Leave a Reply