Site icon ETHIO12.COM

የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ በመደረጉ 29 ቢሊዮን ብር ወጪ ማዳን ተችሏል

ባለፉት አምስት ወራት የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ በመደረጉ 29 ቢሊዮን ብር ወጪ ማዳን መቻሉን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ገለጸ። በእነዚህ ወራትም መንግስት ለህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ለነዳጅ ድጎማ ሶስት ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አመልክቷል፡፡

በባለስልጣኑ የነዳጅ ውጤቶች የገበያ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ እንደገለጹት፤ የታለመ የነዳጅ ድጎማን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት የጅምላ ድጎማ ለማስቀረትና የነዳጅ ዕዳ ለመክፈል ታስቦ ነው።

በጥቅል ድጎማ በነበረ ወቅት በየወሩ መንግስት ከ10 እስከ 14 ቢሊዮን ብር አላስፈላጊ ወጪ ያወጣ እንደነበር ገልጸው፤ ለወጪው ትልቁ መንስኤ መንግስት በጅምላ ድጎማ ሲያደርግ ስለነበርና ነዳጅን ከውጭ ካስገባበት ዋጋ በከፍተኛ ቅናሽ ለገበያ በማቅረቡ ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት 2014 ዓ.ም ሰኔ ወር ብቻ እስከ 14 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ነዳጅን እንደ ሀገር ማቅረብ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረስ እንደነበር አስታውሰዋል።

መንግስት የጅምላ የነዳጅ ድጎማን በማንሳት መክፈል የሚችለው በራሱ ገዝቶ እንዲጠቀምና አነስተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆን ለህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የተለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ተናግረዋል።

የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ በመሆኑም በየወሩ ከ10 እስከ 14 ቢሊዮን ብር በጅምላ የነዳጅ ድጎማ ሲደርስ የነበረውን አላስፈላጊ ወጪ አስቀርተናል ያሉት አቶ ለሜሳ፤ አሰራሩ ተግባራዊ ባይሆንና በጅምላ ድጎማ ብንቀጥል ባለፉት አምስት ወራት ብቻ እስከ 60 ቢሊዮን ብር ኪሰራ ይደርስ ነበር ብለዋል።

የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ በመደረጉም ይደርስ የነበረውን ወርሃዊ ኪሳራ ከ14 ቢሊዮን ወደ 5 ቢሊዮን ዝቅ ማድረግ በመቻሉ ባለፉት አምስት ወራት የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ በመደረጉ 29 ቢሊዮን ብር ወጪ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

የታለመው የነዳጅ ድጎማ ስርዓት የመንግስት ወጪና ኪሳራን መቀነስ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የሚፈፀመው ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ጨምሮ የነዳጅ ብክነትን መቀነሱን ገልጸዋል።

መንግስት ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ ወጪ እስከ ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም 3 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን ጠቅሰው፤ ገንዘቡ ህዝቡ ዘንድ የማይደርስና ህገወጦች ኪሳቸውን የሚሞሉበት ከሆነ ድጎማው ቀርቶ ገንዘቡ ወደ ሌላ አማራጭ መዞር አለበት ነው ያሉት።

በሌላ በኩል አቶ ለሜሳ ቱሉ እንደገለጹት፣ መንግስት የዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ ክፍል የኑሮ ጫናን ለማቃለል መንግስት የታለመ ዓላማ ያለው የነዳጅ ድጎማ እያደረገ ነው። ከሀምሌ ወር ጀምሮ እስከ ህዳር 2015ዓም ድረስ ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሶስት ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ባይኖር ኖሮ ህብረተሰቡ በስድስት ብር የሚወስደውን መንገድ 15ብር፤ 15ብር የሚሄደውን 30 ብር ይጓዝ እንደነበር ተናግረዋል። ይህም የትራንስፖርት ወጪ በኑሮው ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይሆንም ነበር ብለዋል።

በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ህብረተሰቡ በተገቢው መልኩ ተጠቀመ ማለት አይቻልም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞች አልፎ አልፎ ከሚታዩ ችግሮች በስተቀር ድጎማ ተጠቃሚ የህዝብ ተሽከርካሪዎች በተቀመጠላቸው ታሪፍ እየሰሩ ቢሆንም በዞኖች፣ በወረዳዎች ግን ታሪፍ በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ከአዲስ አበባ አምቦ ታሪፉ 106 ብር ቢሆንም የድጎማ ነዳጅ ተጠቃሚ የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች 130 እስከ 150 ብር ድረስ እንደሚያስከፍሉ ተናግረዋል።ይህም የሆነው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ተናበው መስራት ባለመቻላቸው ነው ብለዋል ።

አነስተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ ክፍል በነዳጅ ድጎማው በአግባቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የትራንስፖርት ታሪፍ በትክክል ማስፈጸም ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የታለመው የነዳጅ ድጎማ አተገባበር እና በአፈፃፀም ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን የዳሰሰ የጥናት ውጤት ይፋ ያደረጉት በተቋሙ የጥናት ቡድን መሪ አቶ ታደሰ ጣሰው፤ኅብረተሰቡ ከታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሠራር ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ እና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት እንዲሁም ቀጣይ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ያለመ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

የነዳጅ ድጎማው የመንግሥትን ወጪ ለመቀነስ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ፣ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ፣ በነዳጅ ላይ የሚስተዋለውን ኮንትሮባንድ ንግድ እና ብክነትን ለማስወገድ ያለመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ሰፊ ክፍተቶች እና ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑን በጥናቱ አመልክተዋል። በተለይ የነዳጅ ማደያዎች እና ቸርቻሪዎች አካባቢ ሌብነት ፣ሕገ-ወጥነት እና ብክነት በስፋት የሚስተዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጎማውን ከኅብረተሰቡ ይልቅ አሽከርካሪዎች ያላግባብ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸው፣ ድጎማ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መደበኛ አገልግሎት መስጠት ትተው በኮንትራት ሥራ ላይ እንደሚሰማሩና ድጎማ የተደረገለትን ነዳጅ ቀድተው የተፈለገውን አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው የ90 ብር ታሪፍ እስከ 200 ብር እንዲሁም የ300 ብር ታሪፍ እስከ 600 ብር እያስከፈሉ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ በትራንስፖርት ስምሪት አካባቢ የተቀናጀ ስምሪት እና ቁጥጥር ያለመኖር፣ የንግድ እና የትራንስፖርት ዘርፉን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች እና ሙያተኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣትና የተቀናጀ አሰራር ላይ ሰፊ ክፍተት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሠራር ማጠናከር፣ ድጎማውን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በ’ጂፒ ኤስ’ ቴክኖሎጂ መቆጣጠር እንደሚገባ አመልክተው፤የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ዓላማን መሠረት ያደረገ አሠራርና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2015

Exit mobile version