Site icon ETHIO12.COM

ዶላር መተካት የሚችል ገንዘብ ነው? ለምን የዓለም ጠንካራ መገበያያና የክምችት ገንዘብ ሆነ?

ዶላር ለምን የዓለም ጠንካራ መገበያያ እና የክምችት ገንዘብ ሆነ? ከአሜሪካ ውጪ ያሉ ሀገራት ለምን ዶላርን ያከማቻሉ? ዶላር መተካት የሚችል ገንዘብ ነው?

ከ1940ዎቹ በፊት የዓለም ሀገራት ለዓለም አቀፍ ግብይት የወርቅ ክምችትን እንደ ዋስትና ይይዙ ነበር፡፡ ምን ማለት ነው? አንድ ግራም ወርቅ ያለው ሀገር ምን ያህል ገንዘብ አቻ እንዳለው ልኬት ይቀመጣል፡፡ ይህ አሰራር Gold Standard ይባል ነበር፡፡

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቂያ ላይ (ማለትም 1944) የዓለማችን 44 ሀገራት ተሰባስበው በወርቅ የሚኖረው የአቻ ተመን ወደ አንድ ጠንካራ ወደሚባል ገንዘብ እንዲለወጥ እና ዓለም አቀፍ ግብይት ለማከናወን ጥቅም ላይ እንዲውል ሃሳብ አመጡ፡፡ በወቅቱ በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ያልተዳከመችው እና ከአውሮፓ ሀገራት የተሻለ የተረጋጋ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ የነበራት አሜሪካ ስለነበረች በስምምነት ዶላር የዓለም አቀፍ መገበያያ ወርቅን ወክሎ እንዲመነዘር ወሰኑ ይህ ስምምነት Bretton Woods Agreement ይባላል፡፡

አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች በወቅቱ የአሜሪካው ዶላር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ጠንካራ የነበረውን የእንግሊዙን ገንዘብ ማለትም ፓውንድን ቀምቶታል ይላሉ፡፡

ዶላር የወርቅ ተመን ማውጫ ሆኖ እንዲያገለግል የሚፈቅደውን ስምምነት እንዲያስፈጽሙ ከተቋቋሙት ተቋማት መካከል የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF)፤ የዓለም ባንክ (World Bank)፤ የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO)፤ ወዘተ ስራቸውን ጀመሩ፡፡

ለምሳሌ፡- ከ1944 እስከ 1970 ድረስ አንድ የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አንድ ሀገር 28 ግራም ወርቅ ማቅረብ አለባት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የወርቅ ልኬቱ 28 ግራም አንድ ዶላር በሚል ይሆናል ማለት ነው፡፡

በወቅቱ አሜሪካ በተለይ ከአሜሪካ ውጪ በተለያዩ ሀገራት የብሄራዊ ባንኮች የሚከማቸው ዶላር አቻ ወርቅ መሸፈን ሲያቅታት የወርቅ ክምችትን ከዶላር አቻ ጋር እያነጻጸሩ መገበያየት 1971 በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ኒክሰን አማካኝነት የአሜሪካ ዶላር ስንት ግራም ወርቅ ይሁን የሚለው ቀርቶ የሌሎች ሀገራት ገንዘብ ከራሱ ከዶላር ጋር ያላቸው ተመን እንዲሰራ ወሰኑ፡፡

ማለትም 28 ግራም ወርቅ አንድ ዶላር የሚለው ልኬት ቀርቶ በቀላል ቋንቋ አንድ የእንግሊዝ ፓውንድ በስንት ዶላር ይመነዘራል ወደማለት ተዛወረ፡፡ ወይም አንድ ዶላር ስንት የኢትዮጲያ ብር ነው እንደማለት ነው፡፡

በወቅቱ የዓለም ጠንካራ ኢኮኖሚ አቅም ባለቤት የሆነችው አሜሪካ ያላት የንግድ ትስስር ከፍተኛ በመሆኑ (ከፍተኛ ላኪ እና ከፍተኛ ሸማች በመሆኗ) ሀገራት በዶላር ለሚኖር ዓለም አቀፍ ግብይት እንዲረዳቸው ዶላርን ባገኙት አጋጣሚ በሙሉ በብሄራዊ ባንኮቻቸው ማከማቸት ጀመሩ፡፡ ምን ማለት ነው Foreign Reserve Currency መፈጠር ጀመረ ማለት ነው፡፡

ሀገራት ዶላርን የሚያገኙት ምርትን እና አገልግሎትን ወደ ሌሎች ሀገራት ይልኩ (Export) እና ክፍያውን በዶላር ይቀበላሉ፤ የሌሎች ሀገራት ባለሃብቶች በሀገራቸው ሲመጡ (FDI) የሚደረግን ክፍያ በዶላር ያደርጉ እና ይቀበላሉ፤ ቱሪስት ወደ ሃገራቸው ሲመጣ ዶላር እንዲከፍል እያስገደዱ ያከማቻሉ፤ ወዘተ፡፡

ለምሳሌ፡- በቅርቡ ኢትዮጲያ ያላት የውጪ ምንዛሬ ክምችት የ21 ቀን ፍጆታ ብቻ ነው የሚል ትንበያ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንደወጣው ማለት ነው፡፡

የዶላር ክምችቱ የሚያስፈልገው በዋናነት ዓለም አቀፍ ግብይት ለማከናወን እና እዳ ለመክፈል ሲባል ነው፡፡ በቀላል አነጋገር ህንድ ከጃፓን እቃ ለመግዛት ብታስብ የምትከፍለው የህንድን ገንዘብ/ሩፒ ሳይሆን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል ወይም ጃፓን እቃውን ለህንድ ለመሸጥ ህንድን የምታስከፍላት በጃፓን የን ወይም በህንድ ሩፒ ሳይሆን በአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ ለምን?

ጃፓን ምንም ቁስ ከሌሎች ሀገራት ለመሸመት የምትጠየቀው ዶላር በመሆኑ በራሷ ገንዘብ ግብይት ልታደርግ አትችልም ወይም ብራዚል ከኮርያ ብድር ብትወስድ ልትከፍል የምትችለው በዶላር ነው! ምክንያቱም ብራዚል የሆነ እቃ ከቱርክ ለመሸመት ብታስብ የምትጠየቀው ዶላር በመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁንም ድረስ ጠንካራ የወለድ ምጣኔ፤ ዝቅተኛ የዋጋ ንረት፤ ጠንካራ ኢኮኖሚ አቅም ያለው ሀገር ገንዘብ መሪ ነው! እሱ ደግሞ የአሜሪካው ዶላር ነው፡፡

ዶላር የዓለም መገበያያ መሆኑን ተከትሎ አሜሪካ በቀላሉ ለተለያዩ የዓለም ሀገራት ብድር እና ቦንድ በማቅርብ ከፍተኛ ሃብት እንድታካብት ከማድረጉ በተጨማሪ የዶላርን ጉዳይ የፖለቲካ ጫና መፍጠሪያ በማድረግ ትጠቀማለች (የፖለቲካ ቅራኔ የፈጠረችባቸውን ሀገራት የዶላር ክምችት ሃብት ማንቀሳቀስ አትችሉም እስከሚል ክልከላ ድረስ ማለት ነው!)፡፡

የየሃገራት ኢኮኖሚ አቅም የአሜሪካን አቅም ተገዳዳሪ አለመሆን፤ አሜሪካ በብዙ ሀገራት ያላት ወዳጅነት እና ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ መሆን፤ የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ገንዘቡን/ዶላርን ለማስተዳደር የሚወስደው የወለድ ማሻሻያ እና የዋጋ ንረትን ተቆጣጥሮ ለማቆየት ባላቸው ጥረት ዶላር አሁንም ድረስ በጣም ተፈላጊ የገንዘብ አይነት ሆኖ ቆይቷል፡፡

በዓለም ላይ የዶላር አጠቃቀም ሶስት ባህሪ ይዟል፡፡ አንደኛ፡- ዶላርን እንደ ገንዘባቸው አቻ አድርገው የሚጠቀሙ ሀገራት (ከ65 ሀገራት በላይ) አሉ! (ማለትም አንድ የራሳቸው ገንዘብ አንድ ዶላር እንደማለት ነው) ስለዚህ በገበያቸው ዶላርን ቀጥተኛ መገበያያ አድርገው ይጠቀማሉ፡፡ #ለምሳሌ፡- ፖርተሪኮ፤ ኢኳዶር፤ ፓናማ፤ ዝምባብዌ፤ ወዘተ ዶላርን ገንዘባቸው አድርገው ይጠቀማሉ፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት የሀገራቸው ገንዘብ አቅም በጣም ደካማ ከመሆኑ የተነሳ የሚፈጠርን ከፍተኛ የዋጋ ንረት ለመቋቋም ሲባል ነው፡፡
ሁለተኛ፡- ዶላርን ከሀገራቸው ገንዘብ ጎን ለጎን እንደ ህጋዊ መገበያያ የሚጠቀሙ ሀገራትም (Quasi-Currency of Exchange) አሉ #ለምሳሌ፡- አብዛኛው የካሪቢያን ወይም የላቲን አሜሪካ ሀገራት ይጠቀሳሉ፡፡ #ለምሳሌ፡- ካናዳ እና ሜክሲኮ አንድ የየትኛውም ሀገር ቱሪስት ቢሄድ በዶላር እየከፈለ በቀጥታ መጠቀም ይችላል፡፡

ሶስተኛ፡- ሀገራት ደግሞ ልክ እንደ ኦትዮጲያ ዶላር በብሄራዊ ወይም በባንኮች እየተመነዘረ እንጂ ገበያ ውስጥ ዶላር ከፍሎ መጠቀም የማይፈቅዱ ሀገራት አሉ፡፡ #ለምሳሌ፡- ኢትዮጲያ ውስጥ የሚመጣ ቱሪስት ታክሲ ለመያዝ ዶላር ሳይሆን የሚከፍለው በባንክ ሄዱ በእለቱ ምንዛሬ ዶላሩን መንዝሮ ነው የኢትዮጲያ ብርን ይዞ የሚጠቀመው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሃገራት ጠንካራ ኢኮኖሚ እየፈጠሩ መምጣት፤ ያደጉ ሀገራት ብድር የመውሰድ ፍላጎት መቀነስ፤ የሀገራት የንግድ ትብብር መጠናከር መጀመር፤ የአሜሪካን ጫና ላለመቀበል መወሰን መጀመሩ፤ ወዘተ ተደማምሮ ጠንካራ ገንዘቦች መፈጠር ጀምረዋል፡፡

ለምሳሌ፡- ብዙ ሀገራት የአውሮፓ ህብረት የሚጠቀመውን #ይሮን ለመገበያያ ማከማቸት እንዲሁም ከይሮ ዞን የተወሰዱ ብድሮችን ለመክፈል እንዲረዳ በብሄራዊ ባንኮቻቸው ይሮን ማከማቸት ጀምረዋል (ኢትዮጲያ ውስጥ ይሮ ከዶላር በላይ የምንዛሬ ዋጋ አለው!)፡፡ ማለትም ብዙ ዓለም አቀፍ የንግድ ደንበኞች በግብይት ወቅት ይሮን መቀባበል መጀመር ማለት ነው፡፡

በአንድ ወቅት የአረብ ሀገራት ነዳጅን በዶላር ለመሸጥ በነበራቸው ስምምነት የዓለም ሀገራት ለነዳጅ ፍላጎቶቻቸው ሲሉ ብቻ ከአረብ ሀገራት ነዳጅ ለመግዛት እንዲችሉ ዶላርን ባገኙት አጋጣሚ በሙሉ ለማከማቸት ተገደዋል፡፡

አሁን ላይ ለነዳጇ ሲባል ከፍተኛ ፍላጎት ያለባት ኪዌት አርቴፊሻል በሆነ መልኩ ገንዘቧን/ዲናር ከዶላር በላይ አድርጋለች (አንድ የኪዌት ዲናር ከ3 ዶላር በላይ ይመነዘራል)።

ብዙ ጥናቶችን ስንመለከት ወደፊትም የአሜሪካ ዶላር የዓለም መሪ ዓለም አቀፍ መገበያያ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ቻይና እና ሩስያ ዓለም እራሱን ከአሜሪካ ጫና ለማላቀቅ አዲስ የዓለም መገበያያ እና የክምችት ገንዘብ ለመፍጠር ጥረት እንዲያደርግ እየሞከሩ ነው።

የBRICS አባል ሀገራት ማለትም ብራዚል፤ ሩስያ፤ ህንድ፤ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ በቀጣይ ሳውዲን በመቀላቀል በግብይት ዘርፍ ዶላር/አሜሪካ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው (ለምሳሌ፦ አሁን ላይ ቻይና እና ሩስያ እርስ በርስ ግብይት ሲያከናውኑ በአብዛኛው ዶላር ላለመጠቀም ወስነዋል)፡፡

ለምሳሌ፡- በ2018 አሜሪካ/ትራንፕ ኢራን ላይ የኢኮኖሚ መአቀብ በመጣሉ የኢራን የነዳጅ ሽያጭ ተጽኖ ውስጥ በወደቀ ጊዜ ፈረንሳይ፤ እንግሊዝ እና ጀርመን ከዶላር ውጪ (Dollar Free System) ከኢራን ጋር ግብይት ለማከናወን ስምምነት አድርገዋል ቀጥለዋል፡፡

በዓለም ላይ ከ1.8 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ተሰራጭቷል እንዲሁም ከ75% በላይ የ100 ዶላር ኖት እና ከ50% በላይ ባለ 50 ኖት ዶላር ተሰራጭቶ የሚገኘው ከአሜሪካ ውጪ ባሉ የዓለም ሀገራት ነው (ኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አጠገብ የሚመነዝሩት ልጆች እጅ ሳይቀር ባለ 100 እና ባለ 50 ዶላር አለ ማለት ነው!)።

Source – the ethiopian economist viwe

በሰፊው ሙለውን በቪዲዬ https://youtu.be/_X6UzWi8p1w ማየት ይቻላል)።

Exit mobile version