Site icon ETHIO12.COM

ብልጽግና አጎጠጎጠ ወይስ አሞጠሞጠ?

ያጎጠጎጠ፣ ያጎነቆለ ይበቅላል። ቅርንቻፍ ይሆናል። ለግንዱ ወበት መሆን ብቻ ሳይሆን ግንዱ ፍሬ እንዲያፈራ ያደርጋል። የሚያፈራ ግን አይቆረጥም። ፍሬው ያማረ ነውና። መርዝ የሚያፈራም አለ። መርዝ የሚያፈራ ግንድ ሲያጎነቁል ገና ብትኩሱ እንደ ሙጃ ይጨፈጨፋል። ማሞጥሞጥ ለነገረኞች የሚሰጥ ተውሳክ ነገር ነው። ቁስል ሲያሞጠሙጥ የመበስበሱና መግል የመሆኑ ማሳያ ነው። መግሉ ወይም ብስባሹ ከልተወገደ ሌላውን አካል ሁሉ ይበክለዋል። መርዝ ተውሳክ ነውና!! ብልጽግናም ከሁለት አንዱን ይመስል። በቦሰና ሰዓት አቆጣጠር!!

ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚልቁ ህጻናት በቀን ሁለቴ መመገብ ቻለች። የአሜሪካንን ባንዲራ ለጥፎ ዩኤሴይድ በሚለው ፈንታ የኢትዮጵያ ባንድሪና ” ከኢትዮጵያ” የሚል ማህተም ያረፈበት ማዳበሪያ ያልመከነ ስንዴ ለትግራይ ልጆቿ አቀረብች። ኢትዮጵያ ከጎተራዋ ዝቃ የሳቁባትን፣ የተሳለቁባትን፣ ጨርቃም ያሏትን፣ ዘር ሳትለይ አረሰረሰች። ነገር ለሚገባው ከዚህ በላይ በረከት፣ ከዚህ በላይ ተስፋ፣ ከዚህ በላይ ተድላ የለም። ኢትዮጵያ ታስተሰርይ !! ቢባልስ? ያበደው ዘለለ!! ፈገገ “ተስፋ” አለ። ያለ ተስፋ አይቻልም። ያለ ተስፋ አይሆንም። ተስፋ አለን። ያጣነው አንድ ነገር ብቻ ነው። ተስፋችንን ማየት!! ስናጎነቁል እዩ … ስናዘርዝር እዩ… ስንንዠረገግ እዩ… በመረቀዘው ጎዳና መንጎድ ይቁም። የመረቀዘው መንገድ መርዝ ብቻ ነው … ያብደው “ተለዩ … ” እያለ ሮጠ!! “አብድ ምን ቀልብ አለው” ለምትሉ “ቀልብ” ያለው ማን እንደሆነ መርምሩ።

በትግራይ የእምዬን ሙልሙል እየገመጣችሁ ላላችሁ ያበደው “እንዴት አላችሁ፣ ሰላማችሁ ይብዛ” ይላል። “ያዝ እንጂ ሌባ ሌባውን” ለተከፈተላችሁ “ዘፈኑንን ስሙ” ሲል ድምጹን ይበረግድላችኋል። ያበደው ሲገርመው ብዕሩን ያሾላል። ነገር አናቱ ውስጥ ሲርመሰመስ ይለቀልቃል። ሰላም ሲሰፍን፣ ተስፋ ሲያጎጠጉጥ የሚሆነውን ያሳጣዋል።

ብልጥግና ሆይ ስማ!! ብልጥግና ግን አሞጠሞጠ ወይስ አጎጠጎጠ? ይህ ታላቅ ጥያቄ ላንተ ነው። ማጎጥጎጥ የመብቀል፣ የመፍካት፣ የማበብ፣ የማፍራት … መነሻ ነው። ማሞጥሞጥ ግን የመገለው ሊፈርጥ ሲል ነው። እንግዲህ ካሞጠሞጥክ ትፈርጣለህ። ካጎጠጎጥክ ትለመልማለህ። አንድ ዛፍ መጎጥጎጥና ማሞጥመጥ፣ መለምለምና መግል መሆን አይቻለውም። ውሳኔው የራስህ ነው። የጎነቆለ፣ ሊልውምውልም የተዘጋጀ፣ የለመለመ ብዙ አይተናል። ያብደው ይህ አይክድም። የሚክዱትንም አይሰማም። ግን “መግሎች” አሉ። ጋሬታዎች፣ እንክርዳዶች አሉ። ብልጥግና ይህን ይዞ ኣ .ኣ .ኣ… አይህንም።

ያበደው በፍጥነት ለመለስ ዜናዊ ባሉበት ደወለ። “አሁን ሁሉም አልፏል። ሃቋን ከች ያድርጓት እስኪ” ሲል አሁን ላይ ያለውን የትህነግን አቋምና አቋቋም እንደ መረጃ ለብልጥግና እንዲያካፍሉ ጠየቃቸው።

መለስ ከት ብለው ሳቁ። የሚያውቋቸውን ላለመቀሰቀ አፋቸውን አፍነው አንተፋተፉ። “ቴድሮስን ስማው፣ እዚህ ሆኜ አብርቼለታለሁ። እሱ ጨርሶታል። እስኪ ቲዲኤፍ ይሞክር ደግሞ” አሉና ተሸበለሉ። አያስቅም። የዛሬ ሃያ ዓመት መለስ ” በስብሰናል። ገምተናል። የበሰበስነው ከአናታችን ነው ከጉሮሯን ነው…” ብለው ” እመገለው” ድርጅት ውስጥ ኖሩ። ድርጅታቸው አሞጥሙጦ ሳለ ያጎተጎጠ መስሏቸው ቀጠሉ። ቆይቶ ድርጅታቸው ዛሬ የሆነውን ሆነ። ቴዲ ርዕዮት “በራለት” የተባለውን ቴድሮስን ያበደው ከፍተው። ያብደው በሚሰማው ተገረመ። ቴድሮስ አስቦና ተዘጋጅቶ መለስ ያበሩለትን ለቀቀው።

“አሁን ትህነግ የሚሰራውን ቢያውቅ …” እያለ አፈሰሰው። መለስን ማለቱ ነው። ቴዲ “ሌጋሲው ይቀጥል” ሲባል ጨላማ ውስጥ ነበር? … ለካ የዛኔ የኪነትና የውዝዋዜ ሰፈር ነበር። ውዝዋዜ ሲባል ለካ ሌላም ተወዛዋዥ አለ? ቦሰና ይህ ጨዋታ ሲነሳ ” ደፋርና ደደብ መሆን ብቻ ነው መስፈርቱ” ትላለች። ቴዲን በዚህ አታማውም። ሰማችው። ቴድሮስ ትህነግ ለምን የሰላም ስምምነት ፈረመ ብሎ ከመለስ ጀምሮ ጠረገ።

“ከካርቶኒ” ውጭ ወጥተው ማሰብ የማይችሉ። ካርቶን ራሶች። የሚሰሩትን የማያውቁ ደደቦች። አዲስ አበባን ለቀው፣ አብይን ሾመው የመጡ ካርቶኖች። ቴዲ ትህነግን የጀግና ማማ። የጦር ኤክስፐርት፣ የኢትዮጵያ ባለ ልዩ አዕምሮ አድርጎ ሲዘፍን እንዳልነበር ትህነግን ዘነጣጠለው። ክሸቀጥ አሳንሶ አራገፈው። ቀነታጥቦ አሰጣው። ሰድቦ ለተሳዳቢ አቀበለው። ያበደው ጆሮውን እየጠራረገ ከደጎል ጋር በአይን እየተጠቃቀሰ ቴዲን ሰማ።

ቦሰና ድንገት “እኔን የሚገርመኝ አድማጩ እኮ ነው” አለች። ቴዲ ትህነግን ሲቆልል አምነውት የከፍሉት ነበር። ዛሬ ትህነግ ከፍጥረቱ ጀምሮ አስቦ ሰርቶ የማያውቅ ካርቶን እንደሆነ ሲነግራቸውም ማዋጣት አላቆሙም። ቦሰና በንዲህ ያሉት ስለምትበሽቅ “ኤጭ” ብላ ምራቋን ጢቅ ታደርገዋለች።

ያበደው ታግሎ አንጎሉን ሰበሰበው። “ልክ ነው” አለ። ዘግይቶም ቢሆን ብቴዎድሮስ ልክ ትህነግን ያበሻቀጠ አካል እምድር ላይ አልታየም። በካርቶን ውስጥ ያሉ። ከካርቶናቸው ውጭ ማሰብ የማይችሉ። ካርቶን ራሶች ብሏቸው ቁጭ!! ብልጥግናም ባጎጠጎጠው ዛፍህ ላይ ያሞጠሞጡ መርዞች እንዳሉ አውቀህ ቆርተህ ካልጣልክ ካርቶን ትባላለህ። የት ጋር አጎጥጉጠህ የት ላይ እንዳሞተሞጥክና እንደተመረዝክ ሲነግሩህ ስማ።

Exit mobile version