በቦረና የዝናብ ውሃን በማጠራቀም በዘመናዊ መንገድ…

በቦረና የዝናብ ውሃን በማጠራቀም በዘመናዊ መንገድ ዳግም አገልግሎት ላይ የሚውልበትን መንገድ ለመፍጠር እና በየቤቱ ያለውን የውሃ ችግር ለማቃለል በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅትም በቦረና 40 ሴቶችን በማደራጀት 200 ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ የሚያስችል ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ታመነ ኃይሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ውሃን ከመኖሪያ ቤት ጣሪያ ላይ በመያዝ መሬት ስር ወደሚቀበረው ማጠራቀሚያ በማስገባት መጠቀም የሚቻልበት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመዋል።

በቦረና አካባቢም በሰባት ትምህርት ቤቶች ላይ የተለያየ ሜትር ኪዩብ ውሃ ማጠራቀም የሚችሉ ሮቶዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ በተጨማሪም በጎንደር ከተማ በአራት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ፕሮጀክቱ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ የውሃ አቅርቦት ችግርን ለማቃለል እንደሚረዳም ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአሁኑ ሰዓትም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም እና የውሃውን ጥራት በመጠበቅ ለተለያየ አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የማጣሪያ ቴክኖሎጂ ያለ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም ኢንስቲትዩቱ ግቢ ውስጥ በመሞከር የፕሮጀክቱ አዋጭነት ተረጋግጦ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።

«ለውጥን ለማምጣት መጀመሪያ መለወጥን ይጠይቃል» ያሉት ዳይሬክተሩ ተቋሙ የነበረበትን የአቅም ችግር ለመፍታት ከክልሎች፣ ከሚኒስቴር መስሪያቤቶች እንዲሁም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለይም ሴክተሩን ለሚቀላቀሉ ባለሙያዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ብቃት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ለባለሙያዎች የሚሰጠውን ስልጠና በማስፋፋትም የሕዝቡን የውሃ ችግር በፍጥነት ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሴክተሩን ለሚቀላቀሉ ባለሙያዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ከሚማሩት ባለፈ በእውቀት የተመራ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረው፤ ከስልጠናው በኋላ ወደ ተግባር ተለውጧል የሚለውን እንደሚገመግሙ አብራርተዋል።

ዳይሬክተሩ እንደተናሩት፤ በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ሕዝብ በቂ ውሃ አያገኝም፤ የውሃ እጥረት ሲያጋጥም ትምህርት የሚያቋርጥ ተማሪ ቁጥርም ይጨምራል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም ፕሮጀክቱን በ120 አካባቢዎች ለመተግበር ታቅዷል።

የዝናብ ውሃን ከጣሪያ ላይ በመያዝ ለቤት ውስጥ አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ስኬታማ ለማድረግ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።

See also  ደግ አባት በክፉ ቀን- የብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ አዋጅ በወልድያ

ዘጠና በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ክፍል ሁልጊዜ ዝናብ የሚያገኝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ቴክኖሎጂው ውሃውን ከጣሪያው ላይ ስቦ ለተወሰነ ጊዜ ከመሬት ውስጥ አከማችቶ፤ የውሃ እጥረት በሚኖር ጊዜ መጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። ይህንንም አሠራር ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2015

Leave a Reply