Site icon ETHIO12.COM

ለመቆጣጠር በሚል በኬላዎች ሲሚንቶን መያዝ ‹‹በጥብቅ›› ተከለከለ

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ጸድቆና ተግባራዊ ተደርጎ ሲሠራበት የነበረው የሲሚንቶ አቅርቦትና ሥርጭት መመርያ ተቀይሮ፣ ሲሚንቶን ለቁጥጥርና ለክትትል በሚል በየኬላዎችና ሌሎች ሥፍራዎች መያዝና መውረስ በጥብቅ ተከለከለ፡፡

ከባለፈው ሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ መመርያ፣ በተቀየረው መመርያ ላይ ይከናወኑ የነበሩ ሲሚንቶን በየኬላው በቁጥጥር ምክንያት መያዝ፣ እንዲሁም አከፋፋዮችንና ቸርቻሪዎችን ለፋብሪካዎች መምረጥ የመሰሉ ዓይነት ተግባራት፣ በማንኛውም የመንግሥት አካላት እንዳይከናወኑ ተከለከሉ፡፡ በአዲሱ መመርያ ‹‹በጥብቅ ለተከለከሉ ጉዳዮች›› መካከልም ሲሚንቶን ካለ ደረሰኝ መሸጥና ተሽከርካሪዎች ከፋብሪካ ሲወጡ ካለ መዳረሻ ሰነድ መያዝ እንደማይችሉም ይገኙበታል፡፡

መመርያውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ እንደገለጹት፣ ከዚሁ መመርያ በኋላ መኪኖች ክትትልና ቁጥጥር እየተባለ ‹‹የሚታደኑበት ምክንያት የለም›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ተቆጣጣሪ አካላት ተሰጥቷቸው የነበረው ኃላፊነት ከዚህ መመርያ በኋላ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹በጣም የሚያሳዝነው የባለፈው መመርያ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በቁጥጥር ስም የሲሚንቶ አዳኙ ብዙ ነው ሆነው፤›› ሲሉ አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡ እንደ ሚኒስቴር ዴኤታው ገለጻ ከዚህ በኋላ ቁጥጥር የሚኖረው መንገድ ላይ የሲሚንቶ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ሳይሆን በደረሰኝና በዋጋው እየተሸጠ መሆን አለመሆኑን በመሸጫ መጋዘን ውስጥ መቆጣጠር ብቻ ነው፡፡ ‹‹ይህ ምርት ከዚህ በኋላ በነፃ ይንቀሳቀሳል›› ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

የክልልና የከተማ መስተዳደሮች ከፋብሪካ አውጥተው የሚያከፋፍሉና የሚቸረችሩ የመንግሥትና የማኅበር ድርጅቶችን ከዚህ በፊት ይመርጡ የነበረ ሲሆን፣ እንደ ሚኒስቴር ዴኤታው ገለጻ ይህ ተግባር ከዚህ መመርያ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ተነስቶ አምራች ፋብሪካዎች በራሳቸው አከፋፋዮችንና ቸርቻሪዎችን መምረጥ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ሲሚንቶን ‹‹ነፃነቱ የተጠበቀ ሸቀጥ›› ሆኗል በማለት በነፃነት ከማምረቻው እስከ ፋብሪካዎች መሄድ እንደሚችል አቶ በልሁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሚያሳልጥና ቀልጣፋ ይሆንልናል ያሉትን ነገሮች ፋብሪካዎች ይመርጣሉ›› በማለት አክለዋል፡፡

በተጨማሪም ከተከለከሉ ተግባራት ውስጥ የሲሚንቶ ተሽከርካሪዎችን ከፋብሪካ ያለ መዳረሻ ሰነድ ማስወጣት ሲሆን፣ መዳረሻቸውን የሚያሳውቅ ሰነድ አዘጋጅተው ፋብሪካዎች መሸኘት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዙሪያም ከፋብሪካዎች ጋር በመነጋገር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡

በሲሚንቶ ሥርጭትና ግብይት ላይ የመንግሥት ድርሻ ሰፊ እንደበረና ከዚህ በኋላ ግን፣ ‹‹በረባ ባልረባ ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ይቆማል›› ሲሉ አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የመንግሥት ድርሻ ሊሆን የሚችለው የሲሚንቶ ሽያጩ በደረሰኝ መሆን አለመሆኑን መቆጣጠር፣ እንዲሁም አጠቃላይ የበላይ ክትትልና ቁጥጥር ብቻ ይሆናል፡፡

ሆኖም ግን መንግሥት የሲሚንቶ የፋብሪካ ዋጋን አሁንም ‹‹ለተወሰነ ጊዜ›› በየስድስት ወር እያወጣ የሚቀጥል ሲሆን፣ ባለፈው መስከረም ወር አውጥቶት የነበረውን ዋጋ አሁን በድጋሚ ከልሶታል፡፡ ይህም ለቀጣይ ስድስት ወራት የሚቆየውና እንዳዲስ የተከለሰው ዋጋ ፋብሪካዎች ሲሸጡበት ከነበረው የተወሰነ ጭማሪ ተደርጎላቸዋል፡፡

Ethio FM 108

Exit mobile version