Site icon ETHIO12.COM

[አብይና ትግሬ ታረቁ – አብረው አማራን ሊያጠቁ] የአንገት በላይ ቁምጥና

የአንገት በላይ ቁምጥና … ቃሉ እንዴት አናቱ ውስጥ እንደተቀረቀረ ያበደው አልገባውም። የአንገት በላይ ቆማጦች እንዳሉ ግን ይረዳል። የአንገት በላይ ቆማጦች ሴራ እየተሸከሙና እንዳለ እየዋጡ የሚተፉቱ ናቸው። የተመረቱት ተጭነውና ተሞልተው መልሰው ለመድፋት ነው። መሞላት፣ መድፋት። መጫን ማከፋፈል። ዘመኑ የአርሰናል ነው እያሉን ነው። እዴት ከረመችሁ። የአንገት በላይ ቁምጥና መድሃኒቱ አርጅቶ ወይም በአደጋ መሞት እንጂ ሌላ መፍትሄ የለውም። መድሃኒቱ የትውልድ ለውጥ ብቻ ነው። ቢያንስ ሃይ ሁለት ዓመት ይፈጃል። ካነሰም አስራ አምስት። እናም ለጊዜው ተውጠናል።

ሰው ምንም ሳይደርስበት በሰማው ደንግጦ፣ በሚገመተው ፈርቶ ያነባል። በጭንቀት ይዋትታል። ሃኪም ዘንዳ ሄዶ የጭንቀት መድሃኒት ይቅማል። ምንም ሳይደርስበት እኮ ነው። ያበደው “እመኑኝ” ይላል። “ለዩክሬን የተላከው እኔን ይበላኛል። አርማ ጌድዮን ደረሰ” ብሎ ስም ሰጥቶ ሰቀቀን ይጨርሰዋል። ከርሱ ሳይጎድል፣ ስራ ሳይፈታ፣ መብራት ሳይስተጓዶል፣ ስልኩ ሳይበጠስ፣ ህክምና ሳይጓደል፣ ለነዳጅ ሳይሰለፍ … ምን አደከማችሁ ምንም ሳይሆን ሰው ከሩቅ በሚሰማውና በሚያየው አዝኖ “ሰላም” እያለ ያነባል። ልቡና!!

ወደ እኛ አገር እንመለስ። በተራ የድንቁርና ትምህርትና ስብከት ” መግደል ባህላችን፣ ባህሌ፣ መለያችን፣ መለያዬ …” ስለተባለ ብቻ ጥይት የማይመታው፣ ፈንጂ ትራሱ የሚሆንለት የሚመስለው፣ ድሮን ሸረሪት ሆና የምትታየው፣ ጀት መጫወቻ፣ ሚሳይል የኮባ ዛፍ … እንዲመስለው ሆኖ የተሰራ ትውልድ እምሽክ አለ። እምሽክሽክ አለ። መቼ ሂሳቡ እንደሚወራረድ ባይታወቅም ተቆላ። ተፈጨ። ተረፈረፈ። ይህ ሁሉ የሆነው እቤታችን፣ ጎረቤታችን፣ ዘመዳችን፣ ወንድማችን፣ እህታችን፣ አባታችን፣ አጎታችን፣ እናታችን፣ አክስታችን፣ ታላቃችን፣ ታናሻችን፣ ወዳጃችን … ላይ ነው። አስከፊው ስደት፣ ጨለማ፣ ሞት፣ ረሃብ፣ ጠኔ፣ መፈናቀል… እስኪታክተን ያየነው በቤታችን እንጂ በጎረቤት አይደለም። ይህ ሲሆን ያላየህ፣ አንተ በድን ነህ። አንተ ሙት ነህ። አንተ ደሙ የሚዛወር ሃውልት ነህ። ማንም ሁን ማን ኢትዮጵያ ላይ ላለፉት አራት ዓመታት የሆነው ሁሉ ካልታከተህ፣ ካላሳቀቀህ፣ ካላስጨነቀህ ወይም ካላስጨነቀሽ አንቺ፣ እሱ፣ ሁላችሁም፣ ሁላችንም በድን ነን። ወይም ህሊና ቢስ እንዲሆን ተደርጎ የተመረተው ትውልድ መሪና አመራር ወይም የኮር አለቃ ነህ። የአንገት በላይ ቁምጥና!!

ያበደው ውግዘቱን አቁሞ ዝም አለ። የቅዠት አሳብና፣ የክፋት ዕቅድ ሲመረት መስማት እንግዳ ባይሆንም የዛሬው ግን … “አብይና ትግሬ ታረቁ፣ አማራን አብረው ሊወግሩት ነው” ብለው በበረዶ ውስጥ እሳት ሲያነዱ ያበደው ጆሮ ደረሰ። “ተው ” የሚል የለም። አምስት ሆነው አብይ የሚባሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ይቀጠቅጣሉ። ስልክ እየደወሉ ያራባሉ። ያበደው ጠጋ ብሎ ” ግን እውነት ነው” ሲል ጠየቀ። ” በምን ሰማችሁ ይገርማል” አለና አናቱን ነቀነቀባቸው። አፉን ብረት ብረት እያለው መልስ ጠበቀ።

የዓለም ሁሉ ደቆሮዎች ድምር የሚመስለው ቀድሞ ” እንትና እኮ ነው የለጠፈው” አለና ስም ጠራ። “እሱ እኩ ከሶስት ቀን በፊት ትህነግ ምሽግ እየቆፈረ ነው፣ አራተኛ ውጊያ ሊከፍት በገፍ ወታደር እያስመረቀ ነው” ብሎ ነበር ሲል ወደ ቀልብ የሚመልስ አስተያየት መሰል አሳብ ያበደው አከለ። እብደቱ አፍንጫው ጋር ደርሳ ምራቁ ወፍሮ ምላሱ ላይ እየተዝለገለገ ቢታገለውም ቻለው። መልስ ጠበቀ። ” ዛሬና የዛሬ ሶስት ቀን አንድ ነው? ” ሲል ያው ክምሩ ደንቆሮ ተናገረ። ጨምሮ መስማት ስለማይቻል። ያበደው ” አራችሁን እሩና ተቀቡ” ብሏቸው ነካው። ምን ይላቸዋል።

አር ቆሻሻ ነው። አር ሆድ ውስጥ ይቀመጣል። ሰው አሩ ሲመጣ ቶሎ የሚከንፈው ቆሻሻ ከመሸከም ለመገላገል ነው። አንዳንዶች ግን አራቸውን ከተፈጥሮው መንገዱ ውጭ በሌላ መልኩ ያወጡታል። ንግግራቸው ይሸታል። ይህን እያሰበ ያበደው አንድ ጥግ ደረሰ። በትግርኛ ” አብይን እናመሰግናለን ይለዋል” ብላ ደብረጽዮንን ታነኩተዋለች። “ድሮም ተደምሮ ነበር” ብላ ታናፋለች። “ማታ ስታሊን ልክልኩን እንዲነገረው እደውልለታለሁ” ስትል ጣፊያዋን ትመርጣለች።

“በጨለማ ውስጥ ያሉ ብርሃን አዩ” እንደተባለው ሳይሆን “ከጨለማው ድቅድቁ የሚስማማቸው” በሚል ሊተካ ይገባል። ለሰላም ሰዎች ተሰብስበው መቀለ ደርሰው ሳያድሩ መመለሳቸው እንዴት ያናድዳል? አሁን ያበደው ትግስቱ አልቋል። ” ስሚ አንቺ” አለ። ማንን ነው ” ጨናዊት ያልሺው?” አላት። ደብረጽዮንን እንደሆን ይፋ አደረገች። ያበደው ላይዋ ላይ ባይሆነም ጢቅ አድርጎባት ሄደ። እንዲህ ያሉ የቁም ሟቾች። ሽንት ቤት አጥበው ያገኙትን ለሽብር አምራቾችና አከፋፋዮች የሚገብሩ ድፍኖች። አይ ኢትዮጵያ ሆድ አር እንደሚሸከም አንቺም እንዲህ ያሉትን … ያበደው ደሙ ቀዘቀዘ።

በቅድመ ጦርነት አብይ አፍ መጥረጊያ ነበሩ። በጦረነቱም ወቅት ተለይተው የስድብና የተጠኑ የስድብ ውርጅብኝ በቅብብሎሽ የሚወርድባቸው እሳቸው ነበሩ። ትህነግ የአገር መከላከያን በክህደት ሲያርድም እሳቸው ነበሩ የሚሰደቡት። ትህነግ መከላከያን አዳክሞ፣ የቻለውን ሁሉ ዘርፎ ሲወር እሳቸው ነበር የሚደበደቡት፣ ከተራ የሸቃይ ስድብ ጀምሮ እስከ ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘ ውግዘት ሲወርድባቸው የነበሩ እሳቸው ነበሩ። ትህነግ ደብረሲናን ሲያልፍ ክተት አውጀው ጦር ሜዳ ሲገቡም ” ለምን አልከዳህምና አልኮበለልክም” በሚል ሲወቀጡ የነበሩት እሳቸው ነበሩ። በሁለት ሳምንት ትህነግን ልምሻ ሲያደርጉትም ይሰደቡ ነበር። አየር ሃይልና የምድር ሃይሉን በአዲስ አደራጅተውና አዘምነው ” አፍንጫህን ይዘን” እያሉ ሲያንቧርቁ የነበሩትን ” የሰላም ዘማሪ” ሲያደርጉዋቸውም ስድብ … ቦሰና ” ምን አለበት ይኼ ሰውዬ በቃኝ ብሎ ቢያርፍና የሚሆነውን ባይ” ትላለች። ሰልችቷት።

“እንቀብርሃለን፣ ለፍርድ እናቆምሃለን፣ የትም አትገባም፣ አቅመ ቢስ፣ ዱርዬ፣ አረመኔ፣ ፋሺስት…” ሲሉ የነበሩ አንደበቶች ሁሉንም ሞክረው ሲያቅታቸው በኪሳራ ለሰላም ሲዘምሩ፣ ለዚህ ትምህርት ላበቃቸው ክብር ሲሰጡ ” አይ ፖለቲካ፣ ደሃ ያለቀው ለዚህ ነበር” በማለት አዲሱን ዘፈን በክስረቱ እያሰላህ ወደ ምርጫ ከመጓዝ ይልቅ ሌላ ድራማ በሰዓታት ውስጥ ደርሶ መናወዝ … ያበደው የሰማውን ለቦሰና ነገራት።

” ያው ታመናል እኮ” ብላ ጀመረች። ትግራይ መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትምህርት ቤት፣ ሰላም …እንደሚያስፈልጋት ከሚሸረፍላቸው ካድሬዎች ልቃ አስረዳች። ደጎል እግሮቹን ዘርግቶ ከተንጋለለበት በድንገት ዘለለ። ሲገርመው እንዲህ ያደርገዋል። አፍ ቢኖረው ” አንቺ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አስተባባሪ…መሆን ነበርብሽ ” ይል ነበር። ቦሰና የተፈጥሮ ተማሪ ናት። የላቅ አንጎል አላት። በረከት ስምኦንን “ክፋት እንጂ ቅስቀሳ አይችልም” ስትል በ97 ምርጫ ተርባዋላች። ያበደው አቆረዘዘ።

97 አልተማርንበትም። ንጉሱን ስንጥል ከተሰራው ስህተት አልተማርንም። ትህነግ አዲስ አበባ ሲገባ ይባስ ኢትዮጵያን ሸንሽኖ ጥላቻን ዘራ። ኮተኮተ። አጨደ። ከምሮ ወቃ። በየቤቱ አከፋፈለ። ይኸው ዛሬ ድረስ በሱ ድግስ በሰከሩ አሳራችንን እያየን ነው። ገና ብዙ እንደሚቀር መረዳት ይገባል። ጂጂ “ገና ብዙ ብዙ … ብዙ ይቀራናል …” እንዳለችው ነው። ብዙ እየቀራን ግን ” የአመድ ለመድ ጉዞ” ላይ ነን። ብልጽግናም እድሉን በወጉ እንድንጠቀምበት ማደርገና አለማድረጉን ስናረጋግጥ አሳር ውስጥ ነከሩት። “ቤት ለንቦሳ” የተባሉት ሁሉ ወመቱ!!

ደግ ነገር ሰምተን በቅጽበት በመርዝ ለውሰው ደጉን አውሬ አድርገው የሚያሳዩን ይነሳሉ። ለተንኮል ፍጥነታቸው ይገርማል። አራት ዓመት ሙሉ ስድብና ተንኮል ማጥናት… ለማሰብ ይሰለቻል። አራት ዓመት ከሆድ እንደሚወታው አይነት ቆሻሻ በዋናው ቱቦ መልቀቅ… በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር በተለይ የሆነውን ያየ እንዴት ሰላም ይጠላል?

አብይ አህመድ ከትግሬ ታርቀው አማራን ሊያጠፉ ነው። አማራ ቶሎ በልና ትግሬንና አብይን አጥፋ … ማፈሪያዎች … አንድ ቀን አንድ መድሃኒት ቸርቻሪ የአማራ ነጻ አውጪ ለያበደው ወዳጅ ደወለ።

አብራራ። ተነተነ። አስረዳ። ጀነጀነ። የሚመራው ድርጅት ከእስራኤል ድጋፍ ያለውና የአይሁድ ተሞክሮ የተላበሰ። ከፍተኛ በጀት የተመደበለት። ትህነግ አማራውን ጎንበስ ብሎ ይቅርታ ከጠየቀ ተቀላቅለው ለመስራት የሚያስችል መንገድ

የያበደው ወዳጅ የገርመው ሰውየው ስለሚቋቋመው የአማራ ጦር የተናገረው ነው። ” አማራ የሚናደፍ ጦር ይገናባል። የአማራ ቀዩ ጦር የተለያዩ ክፍሎች አሉት። አንደናው ክፍሉ በየትኛውም ወገን፣ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል፣ አማራ ላይ ጥቃት ሲደርስ እስፍራው ላይ ደርሶ የማያዳግም እርምጃ ይወዳል። ምህረት የለውም። ልክ እንደ እስራኤል አይነት ኮማንዶ ነው…” ማብራሪያው ብዙ ነ።

የበደው ወዳጁን “እንደው ምን ምላሽ ሰጠኸው” ሲል ጠየቀ ወደ ምልልሱ

ያበደው የተለያየ ቀለም ታየው። በኢትዮጵያ በሁሉም ስፍራ በሰላም የሚኖረውን አማራ ጠላት የሚገዙለት እንዲህ ያሉ ቅጥረኞች ናቸው። አርፎ ለፍቶ ከቅርብ ወዳጆቹ ጋር በሰላም እንዳይኖር በስሙ “እቺም ቀይ፣ እቺም ጥቁር” ይጫወታሉ። ትህነግ ፈርጆ ጠላት አመረተለት። በስሙ የሚነግዱ እየቆሰቆሱ ለእርድ ያመቻቹታል። ያበደው አዘነ። በወላጋ የሚሞቱት ምስኪኖች ደም ግን በገዳዮች እጅ ላይ ይጮሃል። ለፖለቲካ ቁማ ስትሉ ምስኪን የምትገድሉና የምታፈናቅሉ ዋልኝ!! ትህነግ ስንት አስጨርሶ ይሆን ዛሬ ምስጋና የገባው? ትግራይ ሰላም ትሁን። ቆየት ብሎ ግን ትህነግ ከፍሎ የማይጨርሰውን ሂሳብ እንዲያወራርድ ራሱ ህዝቡ ይጠይቀዋል።

“ድሮ ሞተን ስልታን ያዝን። ዛሬ ሞተን ምን አገኘን? ለምን አስገደለከን፣ ስንት አስገደለክ? ልጄን … ” የሚሉትን ማስቆም የትህነግ ራስ ምታት ነው። ከመሬት ተነስቶ ውጊያ ገጥሞ በኪሳራ ” ስደት የወጣ እንኳን ምን ይዤ ልመልስ ” ይላል። ጎበዝ ፖለቲካ ይቀፋል። ከሁሉም በላይ ካድሬነት ቆሻሻ ነው። ያበደው ለካድሬ ማተቢያ ልዩ በረኪና እንዲመረት ይጠይቃል። በደሃ ደም ላይ መሞጋገስ። እፍረት አልባዎች!! ፍትህ በወጉ እንዲበየን፣ ተጣርቶ ወንጀለኞችና ለድሃ ሞት ምክንያት የሆኑ ሁሉ ለፍርድ ችሎት እንዲቀርቡ ከመጠየቅ ይልቅ ” አብይ ከትግሬ ጋር ሆኖ…” የሚገለማ ተረት!!

አሁን ብርድ ነው። ያለፉት ሰላሳ ዓመታት “ለምን” ብሎ የማይመረምር፣ የስነምግባር ትምህርት አጢያት የሆነበት ትውልድ ሲመረት፣ የገበያ ዲግሪ ሲታደለባት፣ መስቀልና ሽጉጥ፣ ቁራንና ኮልት አንድ የሆኑበት፣ ታላቅ እንዲጠፋ የተደከመባት አገር ዛሬ እያገገመች ይመስላል።

ያበደው ዘለለ የትግራይ ህጻናት በቀን ሁለቴ እየበሉ ሊማሩ ነው። አራጣዎች ግማሹን እየጎረዱ ሲነግዱበት የነበረው ንየትግራይ ህዝብ በቀጥታ ከቤተስዘመዶቹ ሊገናኝ ነው። ይህ ተስፋ ነው። በጨለማ የኖሩ በራላቸው። በትግራይ ህይወት እየለመለመ ነው። ተስፋ ደስ ይላል። ማምሻም ዕድሜ ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ንቃ። ትህነግን መርምረው። በቃኝ … ሰዓቱ የደጎልና የቦሰና ነው። ቦሰና ዛሬ ተጫጭኗታል። በወር ሶስት ቀን ክፉና ያማታል። ከአገልግሎት መስጫ ክልል ያወጣታል። ትግራይ ስትበራ እሷ ታጠፋለች። ሙዷ ሁሉ ይንጋደዳል። በዚህ ላይ የሴረኞች ቧልት ታክሎበት … ሰላም ሰብቱ!! ከአንገት በላይ ቁምጥና ይጠብቃችሁ። ይህን ከማለት ውጭ ምን ይባላል? እንደው ዝም ነው!!

Exit mobile version