Site icon ETHIO12.COM

ደመወዝ አልተከፈለኝም በሚል አሰሪዋን የገደለችው በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጣች

የወር ደመወዝ አልተከፈለኝም በሚል ቂም ተነሳስታ አሰሪዋን የገደለችው ግለሰብ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጣች

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ እየሰራች እያለ የተወሰነ ወራት የወር ደመወዝ ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ምክንያት ቂም ይዛ አሰሪዋን በመደብደብ ህይወቷ እንዲያልፍ አድርጋለች ባላት ግለሰብ ላይ ክስ መስርቶባት በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ አድርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱም ማህበራዊ መብቶቿ ለዘወትር እንዲሻሩ ሲል ወስኖባታል፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አበቡ ሙላቴ የተባለችው ተከሳሽ ጥቅምት 18 ቀን 2015 በግምት ከቀኑ 10፡45 ሰዓት ሲሆን፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስኮ አዲስ ሰፈር ሊዝ መንደር አካባቢ ሟች ፋሲካ ተሾመ መኖሪያ ቤት ውስጥ የቤት ሰራተኛ በመሆን እየሰራች እያለ የተወሰነ ወራት የወር ደመወዝ ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ምክንያት ቂም ይዛ ሟች በተቀመችበት በብረት ዘነዘና ጭንቅላታቸውን በመምታት ሟች ስትወድቅ በድጋሜ በብረት ዘነዘናው አንገታቸውን በመምታት እና በቢላዋ በመውጋት ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገች በመሆኑ በፈፀመችው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባታል፡፡

ተከሳሽም ክሱ ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ያለች ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግም ተከሳሿ የተከሰሰችበትን የወንጀል ድርጊት እንደ ክሱ ሙሉ በሙሉ ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሰረት በተከሳሿ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ይሰጥልኝ ሲል አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተከሳሿ በተከሰሰችበት ድንጋጌ ሥር በዝርዝር ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሰረት ጥፋተኛ ነሽ ብሏታል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተውም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም በተከሳሿ ላይ በደረጃ 2 እርከን 39 ሥር መነሻ ቅጣት በመያዝ፤ ተከሳሽ ወንጀሉን ያመነች በመሆኑ፣ 1 የቅጣት ማቅለያ ተይዞላት በእርከን 38 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል በሚል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ እንዲሁም ማህበራዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻሩ ሲል መወሰኑን ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡

Exit mobile version