Site icon ETHIO12.COM

ነፋስና የበረዶ ውሽንፍር የበላት ቡፋሎ ከተማ ‘የጦርነት ቀጠና’ 

በመላው አሜሪካ የተከሰተው የበረዶ ውሽንፍር እና አውሎ ንፋስ በኒውዮርክ ስር የምትገኘውን ቡፋሎ ከተማ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያለች አስመስሏታል ሲሉ የግዛቲቱ ገዢ ተናገሩ።

በኒውዮርክ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው ቡፋሎ ከበረዶ ውሽንፍር ጋር በተያያዘ የ28 ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።

ገዢዋ ካቲ ሆቹል ከባለፈው ሃሙስ ጀምሮ የነበረውን ከባድ የበረዶ ውሽንፍር ሲገልጹት “ይህ ከተፈጥሮ ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው። ተፈጥሮ ባላት ነገር ሁሉ እየወጋችን ነው” ብለዋል።

ከካናዳ እስከ ሜክሲኮ ያደረሳው እና በአውሎ ንፋስ የታጀበው የበረዶ ውሽንፍር እስካሁን ለ56 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

በቡፋሎ ከተማ ዙሪያ የአየር ሁኔታው ያስከተለው ውጤት ከሁሉም የከፋ ሲሆን እስካሁን የ27 ሰው ሞት ተመዝግቧል።

የቡፋሎ ተወላጅ የሆኑት ገዢዋ “በጦርነት ቀጠና ውስጥ መጓዝ ይመስላል። መንገድ ላይ የሚታዩት መኪኖች ያስደነግጣሉ” ብለዋል።

ጨምረውም ነዋሪዎች ለህይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎች በችግሩ ክፉኛ ወደተጎዱ አከባቢዎች መጓዝ አልቻሉም ወይም ራሳቸው በበርዶ ተይዘዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ከ2 እስከ 6 ዓመት ህጻናት ያሉት አንድ ቤተሰብ ከፈረንጆቹ ገና በፊት ከአደጋ ለመታደግ የቤተሰቡ አባላት 11 ሰዓት ለመጠበቅ መገደዳቸውም ተጠቁሟል።

የቤተሰቡ አባወራ ሲቢኤስ ለተባለው መገናኛ ብዙኃን ሲናገር “ምንም ተስፋ አልነበረኝም” ያለ ሲሆን ከሁኔታው ለመሸሽ የመኪና ሞተር በማስነሳት ሙቀት በማግኘት እና ከልጆቹ ጋር ጌም በመጨዋት ከጭንቅት ለመውጣት መሞከሩን ተናግሯል።

የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ሲችሉ እና ያልተደረሱባቸው አከባቢዎች ሲደርሱ የጉዳቱ ሰለባዎች አሁን ካለው ቁጥር ከፍ እንደሚል ተጠብቋል።

ትናንት ሰኞ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ስለ ሁኔታው ያወሩት የቡፋሎ ገዢ፣ ፕሬዚዳንቱ ለኒውዮርክ ግዛት ድጋፍ ለማድረግ የፌዴራሉ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደገቡ ተናግረዋል።

የአካባቢ አየር ግፊት ሲቀንስ የሚከሰተው ከፍተኛ አውሎ ንፋስ ወይም ቦምብ ሳይክሎን ከፍተኛ እና በረዶ የቀላቀለ ንፋስን አስከትሏል። በአሜሪካ በርካታ በረራዎችንም አስተጓጉሏል።

የአየር ትንበያው በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ይህ የአየር ሁኔታ እንደሚስተካከል ያመላከተ ቢሆነም እጅግ ወሳኝ ካልሆነ በስተቀር ሰዎች የአውሮፕላን ጉዞዎችን እንዳያደርጉ አሁነም እየተመከሩ ነው።

ባለፉት የእረፍት ቀናት ከ250 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤቶች እና የንግድ ቷቋማት ኤሌክትሪክ የተቋረጠባቸው ሲሆን ተመልሰው መብራት እያገኙ ነው።

በከባዱ አየር ጸባይ ምክንያት በቬርሞንት፣ በኦሃዮ፣ በሚዙሪ፣ዊስከንሰን፣ካንሳንስ እና ኮሎራዶ ግዛቶችም ሞት ተመዝግቧል። በደቡባዊ ፍሎሪዳ የሙቀት መጠኑ እጅግ በመውረዱ ኢጓንስ የተባሉት እንስሳት በበረዶ እጅግ እንደሚሞቱ እና ከዛፍ ላይ እንዲወድቁ ሰበብ ሆኗል።

በምዕራብ አሜሪካ በሞንታና ግዛት እጅግ የከፋ የአየር ሁኔታ የተመዘገበ ሲሆን የቀዝቀቃዜ መጠኑ ከዜሮ በታች 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሷል።

በከናዳ በኦንታሪዮ እና ኩቢክ ግዛቶች ከፍተኛ አውሎ ንፋስን አስመዝግበዋል።

via – BBC Amharic

Exit mobile version