Site icon ETHIO12.COM

578 ዕድሜ ያስቆጠረው የኤሊ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም

ጋሞ ዞን የተለያዩ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ቅርሶች ባለቤት ነው። በዞኑ ረዥም እድሜን ያስቆጠሩ ታሪካዊ ገዳማትና ደብሮች ይገኛሉ። በጋሞ ጎፋ ሀገረስብከት ውስጥ የሚገኘው ዕድሜ ጠገቡ የኤሊ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ደግሞ አንዱ ነው ።

ታላቁ የኤሊ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም መገኛው በጋሞ ዞን ዳራማሎ ወረዳ ኤሊ ኮዶ ቀበሌ ሲሆን ገዳሙ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዘርዓ-ያዕቆብ ዘመነ መንግስት የተመሠረተ ነው።

በወቅቱ የግራኝ መሃመድ ጦርን በመሸሽ ፅላቱን በመያዝ አሁን ወዳለበት ስፍራ መምህሬ ይገዙ፣ መምህሬ ተገኝ፣ እና መምህሬ መንግስቱ የተባሉ የኃይማኖት አባቶች ይዘው መምጣታቸውን በገዳሙ ያሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ገዳሙ ህንፃ መቅደስ ውስጥ ከብሮ ስርዓተ አምልኮ መፈፀም ከጀመረ 578 ዓመታትን አስቆጥሯል ።

ታላቁ የኤሊ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በ1924 ዓ.ም ወደ ገዳምነት እንዲያድግ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ለረዥም ዓመታት ቆይቶ በ1954 ዓ.ም እንዲገደም ተፈቅዶ በወቅቱ ሀገረ ስብከት ባለመቋቋሙ ምክንያት በነገስታት በሚመረጡ ባላባቶች እና ደጃዝማቾች ሲተዳደር መቆየቱን ታሪክ ያስረዳል።

የገዳሙ አሰራር እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ክብ ነው፡፡ ጣሪያ በጽድና ወይራ እንጨት የተሰራ ሲሆን ያለምንም ሚስማር እንደ አካባቢው ባህላዊ የሳር ክዳን ቤት እንዳይበጠስ በቅቤ በታሸ ልጥ የታሰረው ጣሪያ እስከ አሁን ድረስ ምንም አልሆነም።

የአፄ ሚኒሊክ ሰራዊት ወደ አከባቢው በመጣ

ጊዜ የገዳሙን ፅላት ጨምሮ ሌሎች ቅርሶች

በደጃዝማች ገነሜ አማካኝነት ወደ ሸዋ ተወሰዱ።

በወቅቱ የአካባቢው ሽማግሌዎች ከኤሊ ተነስተው እስከ አዲስአበባ በእግራቸው ተጉዘው የተወሰዱ ቅርሶች እንዲመለስ በንጉሱ አፄ ሚኒሊክ ችሎት ጥያቄያቸውን አቅርበው ንዋየ ቅድሳቱ እንዲመለሱላቸው ተወስኗል።

በዚህ ገዳም ውስጥ ከ400 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የወርቅ መስቀል ፣የወርቅ ለምድ/ ካባ/ ፣በብርና በነሃስ የተለበጡ አክሊሎች ከዝሆን ጥርስ የተሰራ መቋሚያ፣የተለያዩ የብራና መፃህፍት እና የሠጎን እንቁላሎች ይገኛሉ።

እነዚህ ቅርሶች በሚፈለገው ልክ ጥበቃ እየተደረገላቸው አለመሆኑን የሚናገሩት የሃይማኖት አባቶች የሚመለከተው አካል ለቅርሶችን አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደረግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እና በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ገዳሙን በቅርስነት ተረክበዋል።

ኤሊ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓመታዊ የንግስ በዓል ለማክበር በሺዎች የማቆጠሩ የሐይማኖቱ ተከታዮች በገዳሙ ታድመው ፣ ተጠምቀው ፣ በረከት አግኝተው ይመለሳሉ።

የዳራማሎ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

Exit mobile version