Site icon ETHIO12.COM

” የፋሲል ጥበባት፣ የባሕረ ጥምቀቱ ምስጢራት”

ለታላቅ ነገር የታጩት ከእረኝነት ተጠርተው በዙፋን ላይ ይቀመጣሉ፣ አይሸነፍም የተባለውን በፈጣሪያቸው መሪነት ያሸንፋሉ፣ ድልንም ይቀዳጃሉ፣ ያልሰመረውን ዘመን ያሰምራሉ፣ ለታላቅ ነገር የተመረጡት ከትቢያ ተነስተው የወርቁን ካባ ይደርባሉ፣ በአልማዝ ያጌጠውን በትረ መንግሥት ይጨብጣሉ፣ በፊት በኋላቸው፣ በቀኝ በግራቸው በአጀብ ይከበባሉ፣ ከነብር በፈጠኑ፣ በአንበሳ በጀገኑ የጦር አለቆች ይጠበቃሉ፣ ከመኳንንቱ እና ከመሣፍንቱ ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጠው ፍርድ ይሰጣሉ። ፀሐይ እንዳይመታቸው በድባብ ይከለላሉ፣ ያማረውን ዘውድ ያጠልቃሉ፣ ባማረው ሰረገላ ተቀምጠው ይንቀሳቀሳሉ፣ ሕዝብ ሁሉ በየደረሱበት እጅ ይነሳቸዋል፣ ንጉሥ ኾይ ሺህ ዓመት ይንገሡ!! እያለ ይመኝላቸዋል።

ለታላቅ ነገር የተመረጡት ስማቸው የሚጠራበት፣ ትውልዳቸው የሚኮራበት፣ ሕዝብ ሁሉ የሚመካበት፣ ኃያልነቱን እና ገናናነቱን የሚመሰክርበት ታላቅ ጥበብ ይሠራሉ፣ በጥቂት ዘመን ቆይታቸው አያሌ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ይጽፋሉ፣ በጥቂት እድሜያቸው ትውልድ ሁሉ የሚማርበት ቅርስ ያስቀምጣሉ፣ ስማቸውን ሞቶ እንዳይቀበር፣ ወድቆ እንዳይሰበር አድርገው ከመቃብር በላይ ያኖራሉ።

ለታላቅ ነገር የተመረጡት በክፉው ዘመን ይነሳሉ፣ ፈጣሪያቸውን እያስቀደሙ በጥበብ ይሻገራሉ፣ በሞገስ ይኖራሉ፣ ሕዝባቸውን ከመከራ ይታደጋሉ፣ ሀገራቸውን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፣ የተወደደች ሃይማኖታቸውን፣ የከበረች ሠንደቃቸውን፣ ማንም እንዳይደፍራት ክብራቸውን ያስጠብቃሉ። በዙፋን ላይ ያስቀመጣቸውን አምላክ ያመሰግናሉ።

ደጋጎች የትእቢትን ነገር እየጣሉ ትህትናን ያነሳሉ፣ ልበ ቀናዎች ጥልን እየናቁ ፍቅርን ይወስዳሉ፣ መልካሞች መከራን እያራቁ ደስታን ይገበያሉ። የተመረጡት ንጉሥ የተወደደውን ሁሉ አደረጉ። ስማቸው የሚጠራበትን፣ ትውልድ ሁሉ የሚኮራበትን፣ ሕዝብ ሁሉ የሚመካበትን፣ ስልጣኔና ታሪኩን የሚገልጥበትን ሁሉ አደረጉ። ተመርጠዋልና በየቀኑ ስማቸው በመልካም ይነሳል፣ ይወሳል፣ ስለ ጥበባቸው፣ ስለ መልካምነታቸው፣ ስለ አርቆ አሳቢነታቸው፣ ስለ ሀገር ወዳድነታቸው ይዜማል፣ ይከተባል።

ስማቸው ከመቃብር በላይ ቀርቷል፣ ሥራቸው በማይጠፋ ቀለም፣ በማያረጅ ብራና ላይ ተፅፏል። በትውልድ ልብ ላይም ተቀርጿል። የገነቧቸው አብያተ መንግሥታት፣ ያስተከሏቸው አብያተክርስትያናት፣ ያስገደሟቸው ገደማት የእርሳቸውን ታሪክ ይመሰክራሉ። ታላቋን ሀገር ኢትዮጵያን በጥበብ አገለገሏት፣ ስሟን ከፍ ከፍ አድርገው ከፍ ብለው ኖሩባት። የረቀቁት አብያተ መንግሥታት፣ የተዋቡት አብያተክርስትያናት ታሪክን፣ ሃይማኖትን፣ ፅናትን፣ ጥበብን እና ቀደምትነትን ይመሰክራሉ፣ ያስተምራሉ፣ ይዘክራሉ።

ጀንበር ጠልቃ በዘለቀች ቁጥር ፋሲል ፋሲል እየተባሉ ይጠራሉ፣ የመናገሻቸውን ከተማ የረገጡ ሁሉ ጥበባቸውን እያዩ ስማቸውን እያነሱ ያመሰግናሉ፣ ኢትዮጵያን በአሻገር የሚያዩዋት፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ኾነው ወደ መናገሻቸው ከተማ ያልመጡት ሥራቸውን እና መናገሻቸውን ለማየት ይጓጓሉ። ባዩዋትም ጊዜ ይደነቃሉ፣ የጎንደር ጎዳናዎች ፋሲልን ይጣራሉ፣ ፋሲልን ያስታውሳሉ፣ ፋሲልን ያደንቃሉ፣ ጎንደር በፋሲል የጥበብ ውጤቶች ትደምቃለች፣ በፋሲል የእጅ ሥራዎች፣ በተፈጥሮ ፀጋዎች፣ የብዙ ብዙ በኾኑ ጀግኖች ትናፈቃለች። ኢትዮጵያ በፋሲል አብያተ መንግሥታት እና አብያተክርስትያናት ከውበት ላይ ውበት ደርባለች፣ የዓለማት ዓይን ሁሉ ማረፊያ ኾናለች።

ስመ ገናናው ንጉሥ ፋሲል የሠሯቸው እፁብ ድንቅ የሚያሰኙ ሥራዎች ዘመናትን ተሻግረው ዛሬም በዙፋናቸው፣ ከመኳንንትና ከመሳፍንቶቻቸው ጋር የጦር አበጋዞቻቸው ከበዋቸው፣ ዓለም አጫዋቾቻቸው እያጫወቷቸው፣ የቤተ መንግሥት አሽከሮች እየተፋጠኑ እያገለገሏቸው ያሉ ያስመስሏቸዋል። ለምን በፋሲል ቤተመንግሥት ዙሪያ አስፈሪው ግርማ ዛሬም ከእነክብሩ አለና። ዛሬም ንጉሥና ንግሥት በዙፋን የተቀመጡበት፣ ግብር እያበሉ፣ የተስተካከለውን ፍርድ እየፈረዱ የሚኖሩበት ይመስላልና። ፋሲል ከተጠበቡባቸው ድንቅ ኪነ ሕንፃዎች እና የከበሩ ቦታዎች መካከል አንደኛው በቀመደው ዘመን የፋሲል መዋኛ ገንዳ እየተባለ የሚጣራው አሁን ጥምቀተ ባሕር የሚሰኘው ነው።

በቀደመው ዘመን እርሳቸው ከቤተመንግሥታቸው በክብር ወጥተው፣ በጀግና ጦረኞች ተከበው፣ በአማረው ልብሰ መንግሥት ተውበው፣ ከሊቃውንቱ፣ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ ጋር ኾነው ይገኙበት ነበር። እነኾ ዛሬም ጳጳሳቱ፣ ኤጲስ ቆጶሳቱ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ፣ መነኮሳቱ፣ መዘምራኑ፣ አንባቢያኑ፣ ምዕመናኑ በአንድነት ይገናኙበታል። ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ሁሉ በአንድነት ይከትሙበታል። በዓለ ጥምቀትንም በአንድነት ያከብሩበታል። በዚያ አፀድ ሥር የከበረ ሃይማኖት፣ ያልተበረዘ ሥርዓት፣ እፁብ የሚያሰኝ ማንነት፣ የፀና አንድነት አለ። በበዓለ ጥምቀት ዓይኖች ወደ ጎንደር ይመለከታሉ፣ በጎንደር የሚኾነውን ነገርም ያያሉ።

አርቆ አሳቢውና ታላቁ ንጉሥ ፋሲል በቀኃ ወንዝ ዳርቻ አስውበው አሠሩት፣ ከጥበብ ላይ ጥበብ ደራረቡበት፣ ንጉሡ ያማረውን ግቢ አሠርተው የተወደደውን ሁሉ ያደርጉ ነበር። አሰግድ ተስፋዬ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በሚለው መጽሐፋቸው የአፄ ፋሲል መዋኛ ግቢ ( ባሕረ ጥምቀት ) “ለጠባቂዎች የሚያገለግል ስድስት ያክል የእንቁላል ቅርፅ ያላቸው ግንቦች በአጥሩ ላይ የተሠራበትና በእድሜ ጠገብ ዛፎች የተከበበ በብርቅዬ አዐዋፋ የተከበበ ነው። ወደዚህ ግቢ መግቢያ በስተምሥራቅ የፈረስ ማሠሪያ እንደነበር የሚነገርለት ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ይገኛል። በአጠገቡ ለባሕረ ጥምቀቱ ከቀኃ ወንዝ ውኃ የሚያመጣው የምድር ውስጥ ቦይ ይገኛል” ብለዋል።

አፄ ፋሲል እጅግ ባማረው ግቢ ውስጥ ያሠሩት ገንዳ የጥበባቸውን ታላቅነት ይመሰክራል። በገንዳው ውስጥ አሽከሮቻቸው በእንሥራ እየተሸከሙ ውኃ እንዲሞሉበት አላደረጉም። ይልቅስ በቀኃ ወንዝ ታላቅ ጥበብ ያረፈበት የውስጥ ለውስጥ ቦይ አሠርተው፣ ለቦዩም በር ከፍተው ውኃ እንዲሞላ አደረጉ እንጂ። ይህን ጥበብ በዚያ ዘመን ማን አስቧል? በሮቹ በጥበብ ይከፈታሉ፣ በጥበብም ይዘጋሉ። በተከፈቱም ጊዜ አምሮ በተሠራው ገንዳ ውስጥ ውኃ ይሞላሉ። ውኃው ከገንዳው እንዲወጣ በተፈለገም ጊዜ በጥበብ የተሠራ በር ተዘጋጅቶለታልና ይፈስሳል።

ታምራት ወርቁ ደግሞ የግዮን ልጆች በሚለው መጽሐፋቸው ” አፄ ፋሲል በቀኃ ወንዝ ዳርቻ ያሠሩት የመዋኛ ገንዳ ዛሬ ድረስ ለጎንደር ጥምቀት መድመቅ ፈርጥ ኾኖ ዘመን ሲነጉድ የዚያ ዘመን የስልጣኔ አሻራችንን ያስቃኛል። ከመዋኛው አንድ ጫፍ ታቦተ ፅላቱ በክብር የሚያርፍበት መቅደስ አሠርተዋል። በዚያ የጸሎት ቤት ሥርዓተ ቅዳሴ፣ ማሕሌት ሽብሸባው ጥምቀት በመጣ በሄደ ቁጥር ይከወንበታል” ብለዋል።

እጅግ ባማረው ግቢ ውስጥ ያለ ምክንያት የተሠራ፣ ያለምሳሌ የቆመ የለም። ሁሉም በምክንያት ተሠራ፣ በምክንያት አማረ እንጂ። እንደዚያ አምሮ የተሠራ፣ እንዲያ በጥበብ ያማረ ሥፍራ ከዚያ ውጭ የት ይገኛል? በዚያ ያማረ ግቢ ውስጥ እየተመላለስኩ፣ አጸዱን በቀስታ እያሰስኩ ተመለከትኩት። የፋሲልን ጥበባት፣ የባሕረ ጥምቀቱን ምስጢራት አየሁ፣ ተመለከትኩም። ልቤ በደስታ ዘለለች፣ መንፈሴ በሀሴት ተመላች፣ ምን አይነት ውበት ነው? ምን አይነት ጥበብ ነው? ምን አይነትስ ብልሃት ነው? ይሄን እፁብ ከማለት ውጭ ምን ሊባል ይችላል? ጸጥታ በነገሠበት አጸድ ሥር፣ በረጃጅም ዛፎች ውስጥ ለውስጥ እያለፍኩ የአበውን ጥበብ አደነቅኩ። ግሩም የግሩም ግሩም ነው።

ከመዋኛው መካከል እንደ ታላላቆቹ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ሁሉ አምሮ የተሠራ ድንቅ የጥበብ አሻራ አለ። ይህ ድንቅ የጥበብ አሻራ ሰገነት ያለው ባሕሩን ለማየት የተመቼና ያማረ የኾነ፣ በስተ ምዕራብ በኩል ባለው በር ሲገቡ ወደ ላይኛው የሕንፃ ክፍል የሚያሻገር መሻገገሪያ ድልድይ ያለው ድንቅ የጥበብ ፈርጥ ነው። የጎንደር ሊቃውንት በበዓለ ጥምቀት በዚያ እየተመላለሱ በፈጣሪያቸው የተወደደውን ነገር ያደርጋሉ። በበዓለ ጥምቀት ሕዝብ ሁሉ ከአፍ እስከ ገደፍ በአጸዱ ዙሪያ ይሞላል፣ በአንድነት ያመሰግናል፣ በአንድነት ይዘምራል፣ እልልም ይላል፣ አጸዱ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ያሸበርቃል፣ ነጫጭ በለበሱ ቁጥራቸው ብዙ በኾኑ ምእመናን ይደምቃል፣ ያማረውን ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ጳጳሳት በዚያ የአማረ ሥፍራ ለበዓለ ጥምቀት የተሰበሰበውን ሕዝብ ይባርካሉ። ምድር ሰላም ትኾን ዘንድ ይጸልያሉ።

የጎንደር ከተማ የግል አስጊብኚዎች ማኅበር ሊቀመንበር ፋንታሁን ያለው “በቀደመው ዘመን የፋሲል መዋኛ ገንዳ፣ የአሁኑ ባሕረ ጥምቀት እጅግ ባማረ መልኩ የተሠራ ነው። በዚህ ሥፍራ አፄ ፋሲል ከታላቁ ቤተመንግሥት እየወጡ የሚቀመጡበት፣ አምሮና ተውቦ የተሠራ ነበር ። አፄ ፋሲል ካለፉ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ኾኖ ኪዳን እየተደረሰበት፣ ቅዳሴ እየተቀደሰበት ምዕመናን እየተሰባሰቡበት ለረጅም ዘመን ኖረ። በኋላም በጣሊያን ወረራ ዘመን ታቦቱ ወጥቶ ወደ ቀኃ ኢየሱስ እንደሄደ ይነገራል። አሁን ደግሞ መንፈሳዊ ይዘቱን በጠበቀ፣ በቀደመው ዘመን መንፈሳዊ ሥርዓት ይካሄድበት እንደነበር ሁሉ ባሕረ ጥምቀት ይከበርበታል” ብሎናል።

የአፄ ፋሲል ድንቅ አሻራ ባሕረ ጥምቀቱ አሁን ካለው የገዘፈ እንደነበርም አቶ ፋንታሁን ነግሮናል። በቀደመው ዘመን ስፋቱ እስከ አጥሩ ድረስ ይደርስ ነበር። አሁን ካለውም የሰፋ ነበር። በጣሊያን ወረራ ዘመን ከቀደመው ስፋቱ መቀነሱም ይነገራል። ነገር ግን ያማረው ግቢ፣ የተዋበው ባሕረ ጥምቀት ዛሬም ከእነ ውበቱና ከእነ ግርማው አለ።ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕረ ዮርዳኖስ እንደተጠመቀ ሁሉ በባሕረ ጥምቀቱ ሕዝብ ሁሉ ተሰባስቦ ይጠመቅበታል።

እነኾ በዓለ ጥምቀት ተዳርሷልና ሂዱ በዚያ በአማረ አጸድ ሥር ተሰባሰቡ። ከቀኃ ወንዝ ዳርቻ ከጥምቀተ ባሕሩ ዙሪያ ተመላለሱ። ድንቁን ጥበብ ታያላችሁ፣ የተዋበውን ሥራ ትመለከታላችሁ፣ የቀደመውን ታሪክ፣ መኩሪያና መመኪያ የኾነውን የአበውን ብልሃት ታደንቃላችሁ። የኢትዮጵያን ውበትና ምስጢርነት ትመሰክራላችሁ፣ በነገሥታቱ ድንቅ ሥራ ሃሴት ታደርጋላችሁ፣ ልባችሁንም በተባረከው ሥራ ታስደስታላችሁ።
አሚኮ
በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ኮሙኒኬሽን

Exit mobile version