Site icon ETHIO12.COM

ዛሬም ‹‹እሹሩሩ ልጄ እሹሩሩ››

የልጇ ዕድሜ እየጨመረ ነው። አሁን አካሉ ጎልብቷል፣ ሰውነቱ አምሯል። እንደ እናት እንዲህ መሆኑ ያስደስታታል። የልጇን አድጎ መለወጥ የምትፈልገው፣ የምታልመው ነው። ከዚህ እውነት ጀርባ ግን ሌላው እውነት ያስጨንቃታል። ጠዋት ማታ ለውጡን ባየች ቁጥር ትተክዛለች። ስለነገው ሕይወቱ፣ ስለመጪው ጊዜ ታስባለች። ውስጠቷ እረፍት አልባ እንደሆነ ዓመታት አልፈዋል። እስከዛሬ በሆነው ሁሉ ደክሟት፣ ሰልችቷት አያውቅም። ስለ ትንሹ ልጇ ትልቅ ዋጋን መክፈሏ ሁሌም ያኮራታል።

ዛሬ ግን ሁኔታዎች እንደትናንት አልሆኑም። ኑሮ ተወዷል፤ ቤት ኪራይ ጨምሯል። የትምህርት ክፍያና የፍላጎት መለያየት በውስጧ ካለው እውነት ጋር ተራርቋል። ያም ሆኖ ስለ ልጇ ሕይወት ፈጽሞ አይደክማትም፤ አይሰለቻትም። ሁሌም ለእሱ ካሏት ትከሻዋ ሰፊ ፣ ልቧ ብርቱና ጽኑ ነው።

እናት የትንሹ ልጅ ፍላጎቱ ይገባታል። ሁሌም ማድረግ የሚሻውን እየጠቆማት ነው። እህት ወንድሞቹን ሲያይ እነሱን መሆን፣ መምሰል ይፈልጋል። እንደ እኩዮቹ ቢሮጥ፣ ቢጫወት፣ ቢዘል ደስ ይለዋል።

ልኬለሽ – ከዓመታት በፊት

ልኬለሽ ተፈሪ የሦስት ልጆች እናት ነች። እስከዛሬ በሕይወቷ ደስተኛ ሆና ኖራለች። እሷና ባለቤቷ በተለየ መከባበር ዓመታትን ተሻግረዋል። በ‹‹አንተ ትብስ፣ አንቺ›› የመሩት ጎጆ ፍቅር ጎድሎበት አያውቅም። ጥንዶቹ ተከባብረው ፣ተዋደው ትዳራቸውን አጽንተዋል። ልጆች ወልደው በወግ በስርአት አሳድገዋል።

አራተኛው ልጅ

ልኬለሽ በቅርቡ ነፍሰጡር መሆኗን አውቃለች። ባለቤቷና መላው ቤተሰቧ ሁሌም ይደግፏታል፣ ይንከባከቧታል። እንዲያም ሆኖ ለሥራ ሰንፋ አታውቅም። ባለችበት መስሪያ ቤት በጉብዝነዋ በጥረቷ ትታወቃለች። ሥራዋን አክባሪና ወዳድ መሆኗ በአለቆቿ ዘንድ አስከብሯታል።

ወይዘሮዋ ጠዋት ወጥታ ማታ ለምትመለስበት ጎጇዋም ፈጽሞ አትሰንፍም። የቀን ውሎዋን ከውና ከቤቷ ስትገባ የወጉን ሁሉ ታደርሳለች። ባሏንና ልጆቿን፣ እልፍኝና ማጀቷን ትቃናለች። ሦስቱ ልጆቿ አዲስ ልጅ እንደሚወለድላቸው ያውቃሉ። መላው ቤተሰብ እንግዳውን ህጻን በጉጉት እየጠበቀ ነው። ሁሉም ለነፍሰጡሯ እናት ያሻትን ያደርጋሉ፣ ይታዘዛሉ።

እናት ልኬለሽ እንደቀድሞ ልምዷ ከሆስፒታል አትርቅም። በየወሩ ክትትሏን ታደርጋለች። በየጊዜው ሐኪም የሚላትን ሰምታ የተባለችውን ትፈጽማለች። አንዳንዴ ስለአራተኛው ልጇ አርቃ ማሰቧ አይርቅም። ልጁ ሲወለድ እንደ እህት ወንድሞቹ ያድጋል፣ እሷና ባሏ የአቅማቸውን አሟልተው ይይዙታል፣ ዕድሜው ሲደርሰ ትምህርት ቤት ይሄዳል፣ ከእኩዮቹ፣ ከባልንጀሮቹ ይጫወታል።

ይህ የአብዛኞቹ ወላጆች ህልምና ትልም ነው። ልጅ ባገኙ ማግስት እንዲህ አይነቱ ውዴታዊ ግዴታ እንደማይቀር ያውቁታል። ልኬለሽም ያለፈ ልምዷን ወደፊት ከሚኖረው ጋር እየመዘነች ብዙ አስባለች። ስለአዲሱ ህጻን ፣ ስለእንግዳው ልጅ መልካሙን ሁሉ አቅዳለች። ባለቤቷ ለእሷ ጥሩ ባል፣ ለልጆቹ መልካም አባት ነው። የቤቱ ራስ ነውና እንደ አባወራነቱ የሚጠበቅበትን ይወጣል። ለነፍሰጡር ሚስቱ፣ ለትንንሽ ልጆቹ ፍቅር እየሰጠ ቤቱን ይመራል።

ወይዘሮዋ በዚህ ማንነቱ ከልብ አክባሪው ናት። ስለእሱ ለጠየቃት ሁሉ መልካምነቱን ታወሳለች፤ ደግነቱን ትናገራለች። ዘወትር በትዳሯ ደስተኛ ናትና ገጽታዋ ሳቅ ፈገግታ አይርቀውም። ልኬለሽ በመስሪያ ቤቷ ትጉህ ሰራተኛ ነች። ባለችበት የሆቴል ሙያ ዓመታትን ዘልቃለች። ሥራዋ ለእሷ ደሞዝ የምታገኝበት ብቻ አይደለም። ወዳና ፈቅዳ በአክብሮት ኖራበታለች ፣ ሙያዋ በአንድ ቦታ ብቻ አላዋላትም። እሷነቷ በሚፈለግባቸው ታዋቂ ሆቴሎች ጭምር ተዘዋውራ ሰርታለች። ሁሌም ውላ ስትገባ የሚከተላት ድካም ብቻ አይደለም። ነገዋን በተለየ የሥራ ጉጉት ታስበዋለች።

ወይዘሮ ልኬለሽ እርግዝናዋን ከሥራ አዋዳ ወራትን ገፍታለች። ነፍሰጡር በመሆኗ የቀረባትና ያጎደለችው የለም። ለውስጧ የሚሰማት ፍጹም ጤናማነት ነው። አሁንም በየጊዜው ከሐኪም ፊት ቀርባ ስለ ራሷና ስለልጇ ጤንነት ትረዳለች። ክትትሏን አታቋርጥም።

ዘጠነኛው ወር

አሁን ወይዘሮዋ በእርግዝናዋ ዘጠነኛ ወር ላይ ትገኛለች። ይህ ወር ለዚህች እናት መልከ ብዙ ትርጉም አለው ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ልጇን በክንዷ ታቅፋለች ፣ ከድካም ስጋቷ ‹‹እፎይ›› ትላለች። ‹‹ምጡን እርሺው፣ ልጁን አንሺው ›› የሚባልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ይህ ስሜት ለእናት ልኬለሽ አዲስ አይደለም። ቀድሞ በነበራት የእርግዝና ልምድ ሁሉን አይታው አልፋለች። እንዲያም ሆኖ ማሰብ መጨነቋ አልቀረም። ሐኪም ፊት ስትቀርብ የምትባለውን በትኩረት ትሰማለች። የምታደርገውን እያሰበች ቀኑን በጣቷ ትቆጥራለች።

ዛሬ እናት ልኬለሽ ከሆስፒታል ሄዳ ሐኪም ፊት ቀርባለች። ሐኪሟ በእጁ የገባውን የአልትራሳውንድ ውጤት እያስተዋለ ለመውለድ አስራ አምስት ቀናት ብቻ እንደቀሯት ማስረዳት ጀምሯል። የሐኪሙ ንግግር በዚህ ብቻ የሚቋጭ አይመስልም። ፊቱን ቅጭም አድርጎ አንዳች እውነት ሊነግራት ተዘጋጅቷል። አሁን ልኬለሽ በትክክል እየተባለች ያለችው የልጇ ጤንነት አደጋ ላይ መውደቁን ነው።

ሐኪሙ ንግግሩን ቀጥሏል። እናት ልኬለሽ ደረቷን በእጇ ደግፋ የሚለውን እያዳመጠች ነው። ሐኪሙ ሀሳቡን ቀጠለ። ይህን ቃልም እንዲህ ሲል ደጋገመው‹‹ መጀመሪያ ለአንቺ ሕይወት ቅድሚያ እንሰጣለን፣ ትኩረታችን ሁሉ ከልጁ እናትየውን ማዳን ላይ ነው›› ይሄኔ ልኬለሽ ልቧ በጆሮዋ ውስጥ ሲደልቅ ተሰማት ፣ ሰውነቷ ተንቀጠቀ፣ አፏ ደረቀ፣ ላቧ በግንባሯ ቸፍ እያለ የመጨረሻውን እውነት ልትሰማው ተጋፈጠች።

ሐኪሙ ያረገዘችው ልጅ የጀርባ ላይ ክፍተት እንዳለበትና በሕይወት የመኖር ዕድሉ ዝቅተኛ መሆኑን እያስረዳት ነው። በደመነፍስ የምትሰማው እናት በማመንና አለማመን መሀል ልትሰማው ሞከረች። ከራሷ ጋር ታግላም ‹‹እንዴት›› ብላ ጠየቀች። ሐኪሙ አንዳንዴ ይህ አይነት ችግር እንደሚኖር አስረዳት። ልጇ በሕይወት ከተወለደም በቀዶ ህክምና እንደሚታገዝ ነግሮ ‹‹አይዞሽ›› ሲል አረጋጋት። ልኬለሽ ስሜቱን መቋቋም አልቻለችም። ደሟ ጨመረ፣ ውስጧ ታወከ። ከዚህ ቀደም ሦስት ልጆቿን ስትወልድ እንዲህ ተብላ አታውቅም። በዕንባ የታጀበ ስብራቷን እያስታመመች፣ በጭንቀት ተውጣ የሚሆነውን ጠበቀች።

ጊዜው ሲደርስ ወይዘሮዋ ወንድ ልጅ ወለደች። ሐኪሞቹ ያሉት ሆኖም በህጻኑ ጀርባ ላይ ክፍተት መኖሩ ታወቀ። እናት ልኬለሽ እንደ አራስ ተኝታ ፣ ወዳጅ ዘመድ ይጠይቀኝ አላለችም። ዓይኗን በዓይኗ ባየች ማግስት ጨቅላ ልጇን ታቅፋ ወደ ህክምናው ሮጠች። ለወራት ከሆስፒታል አልጋ ይዛም የትንሽ ልጇን ሕይወት ለመታደግ ታገለች።

እንደ ህጻኑ ታማ፣ ለቅሶውን ተጋርታ የእስትንፋሱን መኖር ስትናፍቅ ድካም ይሉት አልጎበኛትም። ለአዲሱ ህጻን የተለየች እናት ሆና ፍቅሯን ሰጠችው። ሲስቅ እየሳቀች፣ ሲከፋው እያለቀሰች የመኖር ተስፋውን አረዘመች። ህጻኑን እንደ ሌሎች ልጇቿ ከልብ ትወደዋለች ፣ መልኩ ሁኔታው፣ ያሳዝናታል። የልጅነት ለዛው ያጓጓታል። እናትና ልጅ ህክምናውን ጨርሰው ከቤት ሲመለሱ መላው ቤተሰብ በፍቅር ተቀበላቸው። ትንሹ ልጅ ‹‹እዮስያስ›› የሚል ስም ተችሮት ከእህት ወንድሞቹ ተቀላቀለ ።

ትንሹ እዮስያስ

እዮስያስ ጊዚያትን ባስቆጠረ የህክምና ሂደት የቀዶ ህክምና ተደርጎለታል። የልጁ ችግር በሳይንሳዊ አጠራሩ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ወይም ‹‹ስፓይና ቢፊዳ›› ተብሎ የሚታወቀው የህመም አይነት ነው። ይህ ችግር በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ወራት የሚከሰት ቢሆንም መኖሩ የሚታወቀው ግን እናቲቱ በምትወልድበት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላይ ይሆናል።

በሀገራችን እዮስያስን ጨምሮ ከዚህ ችግር ጋር የሚወለዱ በርካታ ህጻናት ፈታኝ የሚባል ሕይወትን ይገፋሉ። ይህ ህመም ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገራት በተከሰተ ጊዜ ለልጆቹና ለወላጆቻቸው የሚኖረው አመለካከት በአብዛኛው ጤናማ የሚባል አይደለም። በርካቶች ከችግሩ ባልተናነሰ መልኩ በታማሚ ልጆቻቸው ማንነት የሚደርስባቸው መገለል የበዛ ነው።

ህጻኑ እዮስያስ ከወገቡ በታች ያለው አካሉ አይንቀሳቀስም። በልጅነት ዕድሜው ሁሉም የሚታቀፈው ለክንድ የማይከብድ ነበር። እንዲህ መሆኑ ለእናት ልኬለሽ መልካም ሆኖ አልፏል። ሁሉም ቤተሰብ በፍቅር ሲንከባከበው ቆይቷል። እዮስያስ እያደገ፣ ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ግን ክብደቱ ከፍ አለ ፣ ሰውነቱ ወፈረ፣ ሀሳብ ፍላጎቱ ተለየ።

ዘወትር የማይንቀሳቀሱ እግሮቹን በምልክት እያሳየ እንዲራመዱ፣ እንዲሮጡ ያልቻሉበትን ምክንያት ለማወቅ ይሞክራል። እንደ እህት ወንድሞቹ ትምህርት ቤት ውሎ መመለስ አለመቻሉ ያሳስበዋል። ያሰበው እንደማይሳካ በገባው ጊዜም ቤተሰቦቹን ለምን በሚል ስሜት ያስጨንቃል።

አሁን እዮስያስ ስምንተኛ ዓመቱን ለማክበር ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል። በዚህ ዕድሜ የእሱ እኩዮች ትምህርት ቤት ናቸው። ደብተራቸውን ይዘው፣ ምሳ ዕቃቸውን ቋጥረው ወላጆቻቸው ይሸኟቸዋል፣ ከትምህርት ቤት አድርሰው ይመልሷቸዋል። እዮስያስ ይህን ለማወቅ ሩቅ አይደለም። ቢያንስ ወንድሞቹ ከእሱ ጋር የማይውሉበትን እውነት አሳምሮ ያውቀዋል። ዮሲ እንደሌሎች ልጆች አይደለም። እጅ እግሮቹ አይንቀሳቀሱም። ራሱን ችሎ መጸዳዳት አይችልምና ዘወትር ዳይፐር ያስፈልገዋል።

እናት ልኬለሽ ግን የልጇን ከቤት ታስሮ መዋል አልፈቀደችም። ለእሱ ትምህርት ስትል አስራዘጠኝ ዓመት የኖረችበትን ሰፈር ለቃለች ። ርቃ የመጣችበት መንደር ለኑሮ ባይመችም ስለልጇ የማትሆነው የለም። ፍልቅልቁን ዮሲን ይበልጥ ለማስደሰት በጀርባዋ እያዘለች ትምህርት ቤት ታደርሰዋለች። ጠዋት በእሷ ሸክም ከቤት የሚወጣው ህጻን ሲመለሰም የሚጠብቀው የእናቱ ምቹ ትከሻ ብቻ ነው።

ለእናት ልኬ በየቀኑ ልጇን አዝላ ትምህርት ቤት መመላለሱ ያደክማታል። እውነታው ግን ‹‹ለላም ቀንዷ አይከብዳት›› ሆኗል። ድካሟ የበዛና አታካች ቢሆንም ስለእሱ ፈጽሞ አትሰለችም። መከፋት ፣ ማልቀሱን አትሻምና ለደስታና ፈገግታው ዘወትር ዕንባዋን ትውጣለች ፣ ችግሯን ትችላለች። አንዳንዴ አንዳንዶች ልጇን ባዩ ጊዜ እርግማን መሆኑን ሊነግሯት ይፈልጋሉ። ችግሩ ለእሷ ብቻ እንደተሰጣት ቆጥረውም የሚያሳቅቋት፣ የሚያስከፏት አይጠፉም።

ይህ ዓይነቱ እውነት ለእናት ልኬለሽ የየዕለት ገጠመኝ ነው። እስከዛሬ የብዙዎችን ክፉ ንግግር ችላ ኖራለች። የሚሰሟት ቢኖሩ ችግሩን ልታስረዳቸው ትሞክራለች። ልቦና ያላቸው በወጉ ያደምጧታል፣ ልበ መልካሞቹ ደግሞ ያዝኑላታል። ልኬ እዮስያስን አዝላ ስትንቀሳቀስ ሊያሳፍሯት የሚፈቅዱ ባለታክሲዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በርካታ የሚባሉ ትምህርት ቤቶችም ልጁን ከነችግሩ ሊቀበሉት አይወዱም።

የስምንት ዓመቱ እዮስያስ አሁንም የዳይፐር ተጠቃሚ ነው። ይህ እውነት አብሮት ይቀጥላልና እንደማንኛውም ተማሪ አያደርገውም። እናት ልኬ በልጇ ዕድሜ መጨምር ምክንያት ሥራዋን ልትለቅ ተገዳለች። በየቀኑ ትምህርት ቤት አዝላ በመውሰድ ዳይፐር መቀየር ይኖርባታል። ይህ ብቻ አይደለም መንገዷ ሁሌም በፈተና የተሞላ ነው። ሰፊ ጫንቃዋን የሚያግዙ እግሮቿ በየቀኑ ከዘጠና ያላነሱ ደረጃዎችን መውጣት መውረድ ግድ ይላቸዋል።

አሁን ከእዮስያስ ዕድሜ ከፍታ ጋር ያለው ተጽዕኖ እየከበዳት ነው። ዛሬ ላይ ዮሲ ሰውነቱ ጨምሯል፣ እሱን የሚሸከመው የእናቱ ጀርባ እንደትናንቱ አልሆነም። ጫናውን መቋቋም አልሆነለትም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልኬ የነርቭ በሽታ ታማሚ ሆናለች። ሁሌም እጆቿ ይዝላሉ ፣ እግሮቿ በድካም ይንቀጠቀጣሉ። እንዲያም ሆኖ ልጇን መተው አልሆነላትም። ዛሬም ፣ ነገም እያዘለች ትምህርት ቤት ትወስዳለች።

ዛሬ ላይ ሕይወት እየከበደ ነው። ኑሮ በእጅጉ ጨምሯል፣ በየጊዜው የሚያስፈልገው የዳይፐር ወጪም አቅምን የሚፈትን ነው። ይህ ሁሉ ችግር የእናት ሌኬለሽ የየዕለት ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል።

እናት ልኬ እንደምትለው፤ የእዮስያስን አይነት ችግር ያለባቸው ልጆች በርካታ ናቸው። ህብረተሰቡ ግን ችግሩንም፣ ልጆቹንም አያውቃቸውም። በተለይ መንግስት ለእነዚህ መሰል ህጻናት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። የትምህርታቸው፣ የወጪያቸውና የዊልቸራቸው ጉዳይ ቢታሰብበት የወላጆችን ጫና ያቀላል።

ወይዘሮ ልኬ በኢትዮጵያ ብቸኛ በሆነውና በዚህ ችግር ዙሪያ ከሚሰራው ‹‹ሆፕ ኤስ ቢኤች››/Hope-SPH / የተሰኘውን ድርጅት ካወቀች ወዲህ ብዙ ግንዛቤ አግኝታለች። ድርጅቱ እሷን መሰል ለሆኑ እናቶችና ችግሩ ላለባቸው ህጻናት መከታና መድህን ሆኗል። ዛሬ ልኬለሽ እናቶች በእርግዝናቸው ጊዜ የፎሊክ አሲድን በወጉ እንዲወስዱ በትኩረት ለመምከር ቀዳሚዋ ነች። እንደእሷ ሌሎች በችግሩ እንዲያልፉ አትሻም።

ዛሬም ሰፊ የሆነው የእናት ልኬለሽ ጀርባ ልጅ ከማዘል አልቦዘነም። ወይዘሮዋ እንደሌሎች እናቶች አይደለችም። ልጇን አሳድጋ በዳዴና ድክድክ ‹‹ወፌ ቆመች›› አላለችውም። እንደሌሎች ልጆቿ ግንባሩን ስማ፣ ምሳውን ቋጥራ ትምህርት ቤት አትሸኘውም። የእሱ ትምህርት ቤት፣ የእሱ ተስፋና ሕይወት እሷ እና እሷ ብቻ ነች።

አሁንም ጀርባዋ ልጇን ለማዘል ጊዜ አልገደበውም። ሁሌም ይሸከማል፣ እጆቿ ዘወትር ባለጓዝ ናቸው። እግሮቿ አታካች መንገድና ደረጃዎቹን ሲወጡ ሲወርዱ ድካም እንጂ መሰልቸትን አያውቁም። አሁንም በታላቅ ድካም፣ በሰፊ ችግር ልኬለሽ ልክ የሌለውን ፍቅር ለልጇ ትስጣለች። ዛሬም ልጇ ለእሷ ህጻን ነው። ዘወትር አዝላ ‹‹እሹሩሩ ልጄ እሹሩሩ›› ትለዋለች። በታላቅ ድካም፣ ፍጹም በሆነ አለመሰልቸት ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 22 /2015

Exit mobile version