ራስን የመሸጫ ስልት…

እዚህ ሐገር ላይ እየሆነ ባለው ሁሉ ሌሎችን መክሰስ እና ተጠያቂዎቹ እነ እንትና ናቸው (በግልም በቡድንም) ከማለት ባለፈ ለብልሽቱ የእኔ አስተዋፅኦ ምን ያክል ነው ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ መልሱ ምንም ተጠያቂ አይደለሁም የሚል አይሆንም።

እስኪ ጥቂቶቹን እንመልከት:-

መንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላት (የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንም በዚሁ ማዕቀፍ ማዬት የተገባ ነው) የመንግስትን ምስጢር ከውጭ ላለ አካል ያሾልካሉ፣ የመንግስትን መዋቅር ተጠቅመው የራሳቸውን መንግስት የሚያሳጣ ተግባር ይፈፅማሉ፣ ያስፈፅማሉ። ምስጢር አሳልፈው የሚሰጧቸው ሰዎች እነሱን የጀግና ካባ ያለብሱና ከእኔ በተቃራኒ ቆመዋል ያሏቸውን ሰዎች ደግሞ በከሃዲነት ያስከስሳሉ። በዚህም የተነሳ በአንድ መንግስት ውስጥ ጥሬ እና ብስል የሆኑ መቀላቀሎች ያለበት በመሆኑ የተሳለጠ የመንግስት መዋቅር እንዳይኖር አድርጓል። በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት የመንግስን ምስጢር ማዝረክረክ ጀግና አሰኝቷል። ሐገርን ግን እጅጉን ጎድቷል…! እዚህ ጋ ምስጢር አባካኞች ምን ያክል ጉዳት እንዳደረሳችሁ ራሳችሁን መርምሩ እስቲ…!

ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ቢሮ ቁጭ ብሎ ከመስራት ይልቅ በአደባባይ መለፍለፍ የሚሰጠው የጀግንነት ካባ ነው። ሰዎች ቢሯቸው ቁጭ ብለው ከመስራት ይልቅ አጉል ህዝበኝነት፣ ህዝቡ ምን መስማት ይፈልጋል ብሎ መናገር፣ በትግል ጓድ ላይ ማሴር የትግል ስልት ተደርጎ ከተቆጠረ ሰንበትበት ብሏል። የልክ ልካቸውን ነገራቸው ፖለቲካ በአያሌው ተባዝቷል። በአንጻሩ ህዝቡ የሚፈልገው አንገቱን ደፍቶ የሚሰራለት እንጅ ችግሩን በውብ ቃላት አሽሞንሙኖ የሚናገርለት አይደለም። አሁን አሁን ከፖለቲከኛው ባለፈ ነጋዴው እና የኃይማኖት አባት ነን ባዮች ሳይቀሩ የአደባባይ ፍሬ ቢስ ዲስኩር ማሰማትን ራስን የመሸጫ ስልት አድርገን እየወሰዱት ይገኛሉ። በአጭሩ ሰው ሸቀጥ ሆኗል። መነኩሴ እና ሸህ ነኝ የሚለው ሁሉ በአደባባይ ሲለፍፍ መዋል ምንኛ ኃይማኖት እንደሆነ ጌታ የወቀው…! ይኸ ያልተገራ ምላስ ምን አጎደለ ብሎ መጠየቅ ችግሩን በተወሰነ ይቀርፋል፣ ወደ መፍትሄውም ያሰርሳል።

ውሸት እና የተጋነነ ዜና ጉዳይ ደግሞ ሌላኛው ሐገራችንን ችግር ላይ እየጣለ የመጣ ተውሳክ ሆኗል። ባለፉት አምስት እና አራት ዓመታት ውስጥ የሶሻል ሚድያ ፕላት ፎርሞች በብዛት ጠቀሜታ ላይ ውለዋል። ይሁን እንጅ የሚድያዎች መስፋፋት እንዳለ ሆኖ የሀሰት ዘገባ እና የተጋነነ ዘገባ ግን ብዙ ጉዳይ አድርሷል፣ እያደረሰም ይገኛል። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተፈፀሙ እና የሚፈፀሙ ጥቃቅን ስህተቶችን እጅግ አጉኖ በመናገር ህዝብ በመንግስት ተስፋ እንዳይኖረው፣ ይልቁንስ ህዝቡ ራሱን እንደ እድለ ቢስ እንዲቆጥር እና ልፍስፍስ ትውልድ እንዲፈጠር ከፍተኛ የሆነ የሚድያ ዘመቻ ይደረጋል። ህዝቡ የመንግስት እና የህዝብ ተቋማትን እንዲጠራጠር (ለምሳሌ የሐገር መከላከያ ሰራዊትን፣ የፍትህ እና የብሄራዊ ደህንነት ተቋማትን፣ የፋይናንስ እና መሰል ተቋማትን) ከራሱ የራቁ እንዲመስሉ በተቀናጀ እና በተደራጀ ሁኔታ ተሰርቷል፣ እየተሰራም ይገኛል። በእርግጥ እዚህ ጋ ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋማት እንዳይኖሯት የሚፈልጉ ኃይሎች የዘመቻው አቀናባሪ እና መሪ ነበሩ። ኢትዮጵያ ቅልጥ ያለ ጦርነት ይዛ በነበረበት ወቅት መከላከያውን ስም ሲያጠለፉ የነበሩ፣ እንዳትዋጋ እያሉ ሲያስኮበልሉ የነበሩ፣ የመንግስትን ምስጢር አሳልፈው ለጠላት ይሰጡ የነበሩ ኃይሎች አሁን ላለንበት ብልሽት ምን ያክል አስተዋፅኦ ነበራቸው የሚለውን ማየት ይጠቅማል። በዚህ እኩይ ዘመቻ የተነሳ ሐገራችን ስትን ዋጋ እንደከፈለች መቸም አናጣውም።

See also  24 ሠዓታት በውትድርና ህይወት- ምስክርነት ክፍል 8 "አይ አንቺ ሀገር ጠላትም ፣ ጀግና ልጅም አታጪም"

የሚድያ ጋጋታ እና ውሸትን በተጋነነ አኳኋን በተደጋጋሚ በመናገር እውነት የማስመሰል አካሄድ ሐገራችንን እንዴት እንዳቆሰላት እስቲ ዘወር ብለን እንመርምር። በዚህ ሁሉ ምን ያክሎቻችን ተሳትፈናል? ምን ያክሎቻችን ያለ ኃላፊነት ያገኘነውን መረጃ አጋርተናል? ምን ያክሎቻችን በኃላፊነት ስሜት ተንቀሳቅሰናል? ምን ያክሎቻችን ነገን ታሳቢ ባደረገ ስሜት ተንቀሳቅሰናል?

እነዚህን በኃላፊነት ስሜት የፈፀምን ከሆንን ብልሽቱ ላይ የለንበትም ብንል ያምርብናል። ብልሽቱ ውስጥ ስናቦካ ከርመን ከሆነ ግን ተወቃሾች እነ እንትና ብቻ ሳይሆኑ እኛም ነን ማለት ነው። ሁልጊዜ እኔ ምን አደረኩ ማለትን እናስቀድም…!

By Gashaw Meresha

Leave a Reply