ETHIO12.COM

ጃዋር – የኪሊማንጃሮ ጀብድና የፖለትካ ቁልቁለት

ጃዋር ኪሊማንጃሮ ተራራን መውጣቱ አንዱ የህይወት ስኬቱ እንደሆነ ባስታወቀ ማግስት አዋራ ተነስቶበታል።”አክቲቪስት፣ ተንታኝ፣ ፖለቲከኛ አሁን ደግሞ ጀብደኛ ተጓዥ” የሚሉ ስሞችን አስከትሎ የሚጠራው ጃዋር መሐመድ ውስጥ ውስጡ የተነሳበት ነፋስ ወዴት እንደሚያደርሰው ባይታወቅም፣ ከቀድሞ ይልቅ አሁን ላይ ቁልቁል እየወረደ መሆኑ በየቀኑ በአዳዲስ መረጃ እየተሰማ ነው።

አብረውት ከሚታዩት፣ መነጽር፣ የካው ቦይ ባርኔጣና ካኪ ሳይቀር አመሳስለው ከሚለብሱት፣ በቆሎ ሳይቀር አብረው ከሚግጡትና ” አባቴ” ከሚላቸው አቶ በቀለ ገርባ ጋር መቋሰሉን ተከትሎ በዙ ቢባልም፣ የኪሊማንጃሮውን የጀብዱ ጉዞ ተንተርሶ የተሰነዘረበት የዙም ስብሰባ ውርጅብኝ ግን ለየት ያለ ነው።

የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ዎርክን እንዴት “እናጠናክረው፣ በአስተማማኝ እንዴት ሳተላይት ላይ እናኑረው፣ ሰራተኛ እንዴት ቀጥረን እንዳእርጀው?” በሚሉና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከድርጅትና ሚዲያውን ሲደግፉ ከነበሩ፣ ሲያስተባበሩና ሲያደራጁ ከቆዩ አካላት ጋር የዙም ስብሰባ ማድረጉን ጠቅሰው የሚናገሩ ” ጃዋር ተቀጥቅጧል” ባይ ናቸው።

በ2002 ምርጫ ከኦፌኮ ጋር በመሆን ምርጫ ለመወዳደር ጠይቆ ለጊዜው መከልከሉን ያወሱ እንዳሉት፣ ከ2002 ምርጫ በሁዋላ መረራን ጨምሮ በርካታ የኦፌኮ አመራሮች ሲታሰሩ ምንም አቅም ያልነበረው ጃዋር ሲለቀቁ ነግሶ እንዳገኙት ያስታውሳሉ።

መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ፣ ቀጥሎ የሚስሊም ተቆርቋሪ፣ ከዛ የሚዲያ አብዮት አቀጣጣይና ተንታኝ በመሆን የጀመረርው ጃዋር፣ ቀደም ሲል አባል የነበረበትን ኦነግ በፕሮፓጋንዳ አፈር አስግጦ፣ አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ ኦፌኮን በይፋ መቀላቀሉ ይታወሳል። በ2002 ” አይሆንም” ተብሎ የተዘጋውን ደጅ በቀለ ገርባን ይዞ፣ ዝናውን አስታኮ በመበርገድ የኦፌኮ አመራር ሆነ።

ሚዲያ ሲመራ መረጃን ከማጥፋትና የኦህዴድ ታጋዮችን ለመደበቅ ሲባል የተከፈተለትን የኦህዴድ የታች መዋቅር የተቆጣጠረው ጃዋር አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ በረገጠው ከተማና ቀበሌ የህዝብ ጎርፍ ሲፈስለት ማየት የተለመደ ሆነ። ወይቦ የነበረው የፕሮፌሰር ፓርቲ ኦፌኮም አበባ በዛለት። በዚህ አስፈላጊውን የፖለቲካ መዋቅር ዘርግቶ ከጨረሰ በሁዋላ ” እኔ ከተነካሁ ድፍን ኦሮሚያ ትነዳለች” በሚል ” የዘመኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ” መሆኑንን በገሃድ መናገርና ” ሁለት መንግስት አለ” ሲል ጡንቻውን ከአገር መሪዎቹ እኩል ያሳይ ጀመር።

በየደረጃው መልኩን እየቀያየረ ስሙን ያናኘው ጃዋር ሲታሰር የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ሆነ። ብልጽግና ኦሮሞ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የትኛውን ቆጣሪ እንደተቻኑት ባይታወቅም ጃዋር በምህረት እስኪወጣ ድረስ ብልጭ ድርግም ስትል የነበረች ግርግር ከመታየቱ በዘለለ፣ እንደ ጃዋር ትንበያ የሆነም፣ የታሰበም፣ ወይም የተፈራ አንድም ነገር ሳይታይ ጃዋር በምህረት ሆኖ በማንኛውም ሰዓት ሊንቀስቃቀስ በሚችል የክስ ማቆያ ነጻ ተደረገ።

ከእስር በሁዋላ “የጥሞና ጊዜ” ላይ እንደነበር ያስታወቀው ጃዋር ከወራት ዝምታ በሁዋላ ” የትትቅ ትግል ዋጋ ቢስ ነው” በሚል የምስጋና የአውሮፓና አሜሪካ ጉዞ ጀመረ። የተዥጎረጎረ ስብሰባዎችን አካሂዶ ሳይጨርስ “አባቴ” ከሚላቸው አቶ በቀለ ገርባ ጋር ሆድና ጀርባ ሆነ። አቶ በቀለ ገና ጉዳያቸው ባይለይም ላለፉት አምስት ወራት በቆዩበት አሜሪካ ማዕረጋቸውን ወደ ” ስደት” ለመቀየር በመንገድ ላይ መሆናቸውን የኦፌኮ አንዳንድ አመራሮች ለኢትዮ12 ገልጸዋል። ነገር ግን እሳቸው “ኦፌኮን እለቃለሁ” እስካላሉ ድረስ ከድርጅቱ እንደማይነሱ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ አንድ ፍንጭ ሰጥተዋል። ” ልጃቸው ሊሾም ይችላል” ሲሉ።

በዙም ኦኤሜ ኤን ስለማተናከርና ገንዘብ ስለማግኘት በተደረገ ስብሰባ ላይ ” እኛ ኪሊማንጃሮ ውጣበት ብለን አይደለም ብር ስንገፈግፍና ስናሰባስብ የነበረው” በሚል ጃዋርን ክፉኛ የተቹ በዝተዋል። ጃዋር የተሰጠውን ሃላፊነት በወጉ እንዳልተወጣ ጠቅሰው ወቅሰውታል። ክፉኛ ተናግረውታል። በራሳቸው ዕይታ ነው “የት ይደርሳል” ሲሉት የነበረው ኦኤም ኤን በዚህ ደረጃ መገኘቱ የጃዋር ክስረት ተደርጎም በስብሰባው ላይ ተወስቷል።

ኦኤምኤን በግል ተቋቋሙ ከሚባሉ ሚዲያዎች ልቆና በካፒታል ገዝፎ የሚታይ፣ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ በድጅቱ አንድ አካውንት ብቻ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ የነበረው፣ ዛሚንና የዶክተር ገመቺስን ሚዲያ ጨምሮ እየሸመተ የሚዲያ ጡንቸኛ የነበረው ጃዋር ” እኔ የማውቀው ነገር የለም” ሲል መልሷል። እሱ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ሲያመራ አቶ ግርማ ገመቹ ድርጅቱን ከነበጀቱ ሲመሩት እንደነበር ጠቅሶ እሳቸውን መጠየቅ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል። ኪሊማንጃሮንም የህይወት አጋጣሚውን ያሟላበት በመሆኑ ተራራውን መውጣቱ እንጂ ተራራውን ለመውጣት ስለሚያስፈልገው ጉዳይ ማንሳት … ስቆ አስቋል።

ጃዋር ኪሊማንጃሮ መውጣቱን ሳይሆን የተሰበሰበውን ብዙ ሃብት ማባከኑ፣ ሚዲያው ወደ ጎን ከሚሰፋ ይልቅ ራሱን የሚችልና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የሚገባውን ሚዲያ በዚህ ደረጃ ማድረሱ አሁን ለሚጠይቀው ጥያቄ ተዓማኝ እንደማያደርገው ነው በተቺዎቹ የተነሳው።

አሁን ላይ በቀጥታ ያለው የፖለቲካ አቅሙና ሌሎችን በሃይማኖት፣ በፖለቲካና በሚዲያ ሲያሰልፍ የነበረውን ሃይል ዳግም ያገኘዋል? ለሚለው ቀጥታ ምላሽ የሚሰጡ የሉም። ግን ጃዋር ከእስር ከተፈታ በሁዋላ ሁሉንም ጥይቱን ተኩሶ አለመቻሉ፣ ከብልጽግናና ጋር ከመስማማት ውጪ አማራጭ ባለመኖሩ ምን አልባትም ኦፌኮን ይዞት ወደ ቤተመንግስት ሊያመራ እንደሚችል የሚገምቱ አሉ።

የኦፊኮ አመራር የሆኑ ” ካልሆነ ልጁን እንተካለን?” ሲሉ ተሰምተዋል። ልጅ ጃዋር ሲሆን አባት አቶ በቀለ ናቸው። አቶ በቀለ ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ የሚለው ዕምነት በኦፌኮ ዘንድ የሞተ ይምስላል። አሁን ላይ ከኦፌኮ የሚሰማው ድምጽ “ኦፌኮ ወደ ቀድሞው አካታችና ለዘብተኛ ፖለቲካው ይመለስ” የሚል ነው። ጃዋርም በሃይል መንገድ ወደ ስልጣን ለመምጣት ሄዶ፣ ሁሉንም ዓይነት ሂደት አልፎ፣ የመተግበሪያው ሜዳ ላይ ገብቶ ስላልሆነለትና የስደት ህይወት ስለስለቸው ለዘብተኛ መንገድ ለመጠቀም ወስኗል። ከዚህ አንጻር “ልጁን እንሾማለን ” የሚሉትና የጃዋር አካሄድ የሚስማማ እንደሚሆን ታዛቢዎች ይናገራሉ። ጃዋር የፖለቲካ አቅሙ ቁልቁል መሄዱን ተከትሎ በከፍተኛ የበጀት አቅም ወደ ኦፌኮ የተቀላቀለው ጃዋር፣ ሃብት እንዳለው፣ ሃብቱም አዲስ አበባ እንደሆነ የሚናገሩ “ጃዋር ቀሪ ህይወቱን ከስለቸው ስደት ተላቆ መመራት ይፈልጋል” ሲሉ የሰማል። ይሁን እንጂ ሃብት የሚሉትን የትና ምን እንደሆነ አይገልጹም።

Exit mobile version