Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ስም ሆነ በ”ጎጃምነት”ኦሮሚያን መውረር ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም

የዝግጅት ክፍላችን በገሃድ ትህነግ የከፈተውን ጦርነትና ወረራ ከነውጤቱ ሲዘግብ የቆየው ጉዳዩ የአገር፣ ለዚያውም “የእምዬ ኢትዮጵያችን” በመሆኑ ብቻ ነው። ዘር ለይተን ሳይሆን እምዬ ኢትዮጵያን ከመጠበቅና ግፍ ለተፈጸመባቸው ሁሉ ድምጽ ለመሆን ሞክረናል። ለትግራይ ሕዝብ ጭምር።

ከዚያ በዘለለ ዘርን መሰረት ያደረገ ዘገባና ዜና ብዙም ቀልባችንን የማንሰጠው ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝንና የዘር ፖለቲካውን ጡዘት ለማርገብ ካለን አቋም የተነሳ እንጂ መረጃና ማስረጃ ሳናገኝ ቀርተን አይደለም።

በወላጋ የተለያዩ ቀበሌዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደረገውን፣ ሲደረግ የነበረውን ግፍና ግድያ፣ እንዲሁም መፈናቀል አብዝተን ኮንነናል። ጸያፍና ይቅር ሊባል የማይችል መሆኑንን የክልሉን ሃላፊዎች ተጠያቂ በማድረግ አውግዘናል። ይህ አረመኔነት የተሞላው ተግባር የኦሮሞን ስም በለጠፉ ወንጀለኞች የሚፈጸም በመሆኑ “ኦሮሞ የሆንክ ሁሉ በስሜ አትግደል” በሚል መቃወም እንዳለበት አስታውቀናል። ወደፊትም ይህ የንጽሃን ግድያ እስኪቆም ይህ አቋም ያለ ይሆናል።

በተመሳሳይ ማንም ይሁን ማን በህግ ባለቤትነቱ ያልተረጋገጠለት ቀበሌ ዘልቆ ገብቶ መኖር እንጂ በግደል፣ መውረር፣ መዝረፍ እንደማይቻል ዛሬ ላይ ድምጻችንን እንድናሰማ ግድ ሆኗል። በአማራ ስምም ሆነ በጎጃምነት ኦሮሚያን መውረርና ማስወረር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም የሚል አቋም የያዝነውም በማስረጃና በቂ ምክንያት፣ ለረዥም ጊዜ ጉዳዩን በጥንቃቄ ስናየው ከቆየን በሁዋላ ነው።

ትህነግ አማራና አፋር ክልልን ሲወር የተቃወምነው ህገወጥ በመሆን ብቻ ነው። ትህነግ የፈጸመውን ዓይነት ወረራ ማንም አካል ከፈጸመ ሊወገዝ፣ ልክ እንደ ትህነግ ሊቀጣና ትምህርት ሊሰጠው ይገባል። ምክንያቱም ወረራ ለአንዱ የሚሰጥ፣ ለሌላው የሚነፈግ አይደለምና።


ተጨማሪ ዜናዎችን ያንብቡ


ለሚጠራጠሩ “ብታምኑም ባታምኑም” ብለን የምናስታወቀው ጉዳይ ቢኖር መነሻቸውን ጎጃም ያደረጉ ታጣቂዎች፣ ነዋሪዎች “ክልሉ ሆን ብሎ በፋኖ ስም የላካቸው ልዩ ሃይል ናቸው ” የሚላቸው የተደራጁ ሃይሎች ከጉቲን ጀምሮ ድፍን ምስራቅ ወለጋን ወረው ቆይተዋል። ይህ ሲሆን የክልሉን ልዩ ሃይል ከበው ትጥቅ አስፈትተዋል። ዘርፈዋል። ገድለዋል። ብዙ የህግ ጥሰት ፈጽመዋል።

በማስረጃ ተደግፎ የደረሰን መረጃ እንደሚያመክተውና ያነጋገርናቸው እንደገለጹት፣ እኛም እንዳረጋገጥነው ኦሮሚያ ላይ በአዋጅ ወረራ ተፈጽሟል። ጎጃምና ምስራቅ ወለጋ የድነበር ውዝግብ ኖሯቸው አይውቅም። ይህ ወረራ እንጂ ሌላ ስም የማይኖረው ለዚህ ነው። በአማራ ብልጽግናና በኦሮሚያ ብልጽግና መካከል የተፈጠረው ስንጥቅም የዚሁ ውጤት ነው። በመሆኑም

የሚጠቃለል ነገር ባይኖርም ህገወጥነት በማንም ይሁን በማን ሲፈጸም በጋራ መቃወም ግዴታ ሊሆን ይገባል። የብሄር ፖለቲካ እየጋተ ያሳደገን ትህነግ በገነገነበት የዘር ፖለቲካ ለትግራይ ህዝብ ያተረፈለት ቢኖር ጭለማን መከራን ነው። ይህ ደግሞ የሆነው ህዝቡ የትህነግን አካሄድ መቃወም ባለመድፈሩ እንደሆነ አይጠያይቅም። አሁን እንደሚሰማው ይህ ወረራ መልኩን እየቀያየረ የሚቀጥል ከሆነ ተወራሪዎችም ክንዳቸውን ማስተባበራቸው አይቀርም። ፍትህ ሲጓደል የማይወዱና “ነግ በኔ” የሚሉም ልክ ትህነግ ላይ እንዳደረጉት ለተወረሩ ድጋፍ ማድረጋቸው አይቀርም። እዚህ ደረጃ መደረስ የለበትም። መከላከያ ላይ ቃታ የሳቡትን እጉያ አስቀምጦ፣ “ኢትዮጵያ” እያሉ ማልቀስና ማስለቀስ፣ በየሚዲያው ተበዳይ ብቻ ሆኖ መቅረብ አይነፋም። ማንም ይሁን ማን ወረራ፣ ዘረፋ፣ ግድያ ከፈጸመ መቀጣት አለበት። በኦሮሞ ስም ዘር ለይተው የሚገድሉና የሚዘርፉትን ጸያፎች በምንቃወምበት ልክና አግባብ፣ ኦሮሚያን በ”ተበድለናል”ስም መውረር ከቶውንም ተቀባይነት የለውም እንላለን።

Exit mobile version