Site icon ETHIO12.COM

ጥናቶች ከመደረደሪያ ወደ ተግባር …

 የአገር በቀል ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ለማሳካት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በጠንካራ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሊደገፍ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት “ችግር ፈቺ ምርምርና ልማት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘላቂ እድገትና ተወዳዳሪነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከባለሃብቶችና ከተመራማሪዎች ጋር ምክክር ተደርጓል።

በምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ባለፉት ዓመታት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ለማሻሻል በተለይም የሀገር በቀል ኢኮኖሚን ለመተግበር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አምራች ኢንዱስትሪው ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። ዘርፉ ግቡን የሚያሳካው በምርምር ሥራ ሲደገፍ በመሆኑ አምራቹ ባለሃብትና ተመራማሪዎች በቅንጅት ሲሠሩ ነው።

ባለፉት ዓመታት በቆዳ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በፋርማሲና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ጥናቶች ሲሠሩ ቆይተዋል ያሉት ሚኒስትሩ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች ከመደርደሪያ የዘለለ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው የአምራች ኢንዱስትሪው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለም ብለዋል።

ለዚህም የቅንጅት ጉድለት በመኖሩ፣ ባለሃብቱንና ጥናቱን በማቀናጀት በፖሊሲ የተደገፈ ሥራ ባለመሠራቱ እንደሆነ በመጠቆም፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር “የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ”በመንደፍ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የምርምር ሥራዎች የአምራች ኢንዱስትሪው ባለሀብቶች በቅንጅት መሥራት አለባቸው። ይህ ሲሆን የማምረት አቅም ያድጋል ብለዋል።

አቶ መላኩ አምራች ኢንዲስትሪው በመጪዎቹ አስር ዓመታት ከፍተኛ ሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የገቢ ምርቶችን በመተካት፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም እንዲያሳድግ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ገቢ እንዲያድግ ተስፋ ከተጣለባቸው ዘርፎች ቀዳሚው መሆኑን ጠቁመው፤ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 85 በመቶ እንዲሆን የገቢ ምርትን በመተካት ረገድ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ዘርፉ ትልልቅ ግቦችን ማሳካት የሚችለው በጠንካራ የምርምርና የጥናት ሥራዎች መደገፍ ሲቻል መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ከሁሉም ዘርፎች ጠንካራ ውድድር ያለበት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው። ከቻይና፣ ማሌዥያ፣ ከአውሮፓና ከሌሎች ሀገራት የተመረተ ምርት ኢትዮጵያ ገብቶ መወዳደር የሚችለው ከአምራች ኢንዱስትሪው ጋር ነው። የኢንዱስትሪ ምርቶች ግብዓትና ምርቶች መዳረሻቸው ድንበር የለውም። ስለዚህ የአገር ጥንካሬን ከሚለኩና እውቀትን በስፋት ከሚሹ የሥራ መስኮች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቁን ስፍራ የሚይዝ መሆኑን ገልጸዋል

እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፤ በሀገር ደረጃ የተያዙ ትልልቅ እቅዶችን ለማሳካት በጥናትና ምርምር የተደገፉ ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆኑ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ሲፈጠሩ ነው። ኢኖቬሽን፣ግንኙነት፣ ምርምር ሳይኖር ሀገርን ተወዳዳሪ ማድረግ አይቻልም። ያደጉ አገራት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ጎልተው እንዲወጡ ካስቻሏቸው ዘዴዎች አንዱ ምርምር ላይ በሠሯቸው ተግባራት ነው።

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚልኬሳ ጃገማ፣ ኢንስቲትዩቱ ከተሰጠው ተልዕኮ አንዱ ጥናትና ምርምር በማካሄድ አምራች ኢንዱስትሪው ምርትና ምርታማነቱ አድጎ ተወዳዳሪ ሆኖ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ማድረግ ነው። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን የሚሠራ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ምርምሮችን ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ትግበራ ላይ እንዲውል ለማድረግ እየተሠራ ነው።

የአምራች ኢንዱስትሪውን በጥናት ለመደገፍ 67 የሚሆኑ የጥናትና የምርምር ሥራዎች መሠራታቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ከምርምሮቹ ውስጥ አምስት የሚሆኑት ለአምራች ኢንዱስትሪው ባለሃብቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በቀጣይም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version