Site icon ETHIO12.COM

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ግብጽ ውስጥ አቋም ለመያዝ ስብሰባ ይካሄዳል

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስትያን ጉዳይ የአምስቱ እህት አብያተ ክርስትያናት ቅዱሳን ፓትርያርኮች በግብጽ ካይሮ ከተማ ሊሰባሰቡ እንደሆነ የዘገበው የኤርትራ ፕሬስ አማርኛው ገጽ ነው።

ኤርትራ ፕሬስ በዜናው ” በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስም በቅርቡ የተመሰረተውን ህገወጥ ሲኖዶስ ” ሲል የጠራው ወገን ሲኖዶስ ስለማቋቋሙ ይፋ መረጃ ከማን እንዳገኘ አላብራራም። “የኤርትራ ቅዱስ ሲኖዶስን ጨምሮ የአምስቱ እህት አብያተ ክርስትያናት ቅዱሳን ፓትርያርኮች በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስም በቅርቡ የተመሰረተውን ህገወጥ ሲኖዶስ እና በቅድስት ቤተክርስትያኗ ላይ የተከሰተውን ፈተና በተመለከተ ምክክር ለማድረግና ውሳኔ ለማሳለፍ በግብጽ ካይሮ ይሰባሰባሉ” ያለው ዜና ማን ስብሰባውን እንደጠራ፣ ለምን ካይሮ እንደምተመረጠች? ዝርዝር አልገለጸም።

በስብሰባው የሚሳተፉት

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሓፊ አቡነ እንደርያስ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ ዳግማዊ – 118ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ካርኪን ዳግማዊ – 132ኛው የመላው አርማንያ ፓትርያርክ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሳልሳይ – 22ኛው የህንድ ፓትርያርክ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አግናጤዎስ ኤፍሬም- 122 ኛው የአንፆኪያና የመላው ሶርያ ፓትርያርክ

አምስቱም ቅዱሳን አብያተ ክርስትያናት በኢትዮዽያ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ውስጥ የተፈጠረውን መከፋፈል አውግዘው ከነባሩና ከህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንደሚቆሙ በመግለጽ ቅድስት ቤተክርስትያኗ የደረሰባትን ክፉ ፈተና በሰላም እንድትሻገር እግዚአብሄርን በፀሎት እንደሚጠይቁም ጭምር ገልፀው ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ ለህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለመላው ኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን መልእክት ልከው እንደነበር ኤርትራ ፕሬስ አስታውሷል።

“አሁን ደግሞ የአምስቱ እህት አብያተ ክርስትያናት መሪዎች በካይሮው ስብሰባ ተገኝተው በዘርና በቋንቋ የተዋቀረውን በእነ አቶ አካለወልድ (በቀድሞ ስሙ ሳዊሮስ) በተባለው ግለሰብ የሚመራውን ህገወጡን ሲኖዶስ ከማውገዝ ጀምሮ ከእነርሱ ጋር ህብረት ያለው፣ በገንዘብ፣ በምክር እና በሌላ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ድርጅቶችን እና ተቋማትን አውግዘው እስከመለየት ድረስ ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል” ሲል ኤርትራ ፕሬስ ግምቱን አስቀምጧል።

ዜናውን በንቃት የሚከታተለው ኤርትራ ፕሬስ፣ ” በዘርና በቋንቋ የተዋቀረውን” ሲል የጠራውን ሌላኛ ወገን የሚከተሉ ሁሉ ካይሮ ላይ ውግዘት እንደሚታወጅባቸው ሲያስታውቅ፣ ዘርና ቋንቋ ስላለው ዘርዝሮና ስም ጠርቶ አላስታወቀም። ኤርትራ ፕሬስ በኤርትራ የዕምነት ነጻነት አፈናና እስርን በመቃወም ጽፎ አይውቅም። በርካቶች በዕምነታቸው ምክንያት የሚታሰሩባት ኤርትራ ሚዲያዎቿ ምንም እንዲሉ አይፈቀድላቸውም።

Exit mobile version