Site icon ETHIO12.COM

ፖለቲከኞችና መሸተኞች ከዕምነት ሰፈር ውጡ፤ ሕዝብም ፖለቲካና ዕምነትህን ለይ!

የኢትዮጵያ ውሃ ልክ ከተበላሸ ቆይቷል። እንዲበላሽም የተደረገውም ሆን ተብሎ ነው። ሲበላሽም፣ አበላሾቹ በድል ስሜት ነግረውናል። እንዲበላሹና እንዲመክኑ የተደረጉ በርካታ የህዝብ ትሩፋቶች ናቸው። አንዷ ቤተክርስቲያን ስትሆን፣ እሷም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነች።በየጊዜው ፖለቲካ የሚያጠላባትና ለፖለቲከኞች በሯን መዝጋት ያልቻለችው ቤተክርስቲያን ባለፉት ሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት ያጋጠማትና የተበጀላት መንገድ ከልብ ለሚመረምረው ያስደንግጣል። የሚደነግጥ ልብ ካለን!!

ሁሉም በሚባል ደረጃ ቤተ ዕምነቶች ጉዳቸው ብዙ ቢሆንም፣ ዛሬ ኦርቶዶክስ ቤት የተፈጠረው ግን ዕረፍት የሚነሳ በመሆኑ አቋማችንን ማሳወቅ ግድ ሆኖብናል። ኦርቶዶክስ ቤታችን፣ አገራችን፣ ታሪካችን፣ ናት። እምነት ሳይለይ ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀና የሚሆኑትም በብዙ ምክንያት እንጂ እንዲሁ ሾላ በደፈናው ዓይነት አይደለም።

ዛሬ ይህቺ ቤተክርስቲያን ያጋጠማት ህመም ሁሉንም የሚያመው ይዞት የሚመጣው ጣጣ ሰፊ ከመሆኑ አንጻርና ጣጣው ከማዘንና ጸጸት የዘለለ ሊሆን እንደሚችል በማመን ነው። በተለይም ዕምነቱ ሰፈር ያሉትን ካድሬዎችና አልጠግብ ባዮች ነገሩን ወዴት ወዴት እየወሰዱት እንደሆን ስንመለከት ድንጋጤያችን ውሃ ልኩን ያልፋል። ለዚህ ነው ፖለቲከኞችና መሸተኞች ከዕምነት ሰፈር ውጡ፣ ሕዝብም ፖለቲካና ዕምነትህን ለይ ለማለት የወደድነው።

ዛሬ ማታ ማታ ማይክሮፎን ይዞ አስረሽ ምቺው ሲል የሚያድር አዝማሪ “ተነስ” እያለ ጥሪ እያሰማ ነው። ዛሬ በየጥጋጥጉ አረቄና ቁርጥ እየበላ በቀን ሶስቴ የሚዘሙት ” አትነሳም ወይ” እያለ ነው። ትናንት ወንጀለኛ የተባሉ የብሄር ግጭት ጠማቂዎች ” አረ ጎበዝ” እያሉ ነው። በቀን ሶስትና አራት ኪሎ ጫት የሚበሉና አምቡላ ሲግቱ የምናውቃቸው አንዛራጮች ” ወደፊት በሉለት” እያሉ ነው። አንዳችም የቅድስና ሰፈር ውስጥ ድርሽ የሚያደርግ ስራ የሌላቸው ስማቸውን እየተጠቀሙ ከየጎሬያቸው በመውጣት የተጋደል ከበሮ እየመቱ ነው? አገር ስትወረር ዞር ብለው ያልተነፈሱ፣ ዛሬ ታጋይ እየሆኑ ነው። የሚያሳዝነው ” እንወያይ፣ በሰላም ችግሩን እንፍታው” የሚሉት ላይ የሚጎርፈው ቤተሰብና ዘመድ አዝማዳቸው ላይ ሳይቀር የሚወርድባቸው ውርጅብኝ ዓላማው ምን እንደሆነ ሲታሰብ ነው። አደጋውም ገሃድ የሚታይ በመሆኑ ነው።

ክርስትና ” መስቀሉን መሸከም” የሚል ግልጽ መርህ እያለው ከሁሉም ወገን መስቀል ተሸክመው፣ ከካባቸው ጋር ካድሬነትን የደረቡ፣ በከርስና በድርሻ መታላታቸው እየታወቀ ይህ ሁሉ ግብ ግብ መታየቱ ” ምን እየሆንን ነው” ያሰኛል። የቤተክርስቲያን አናቷ ምን እንደሚመስል እየታወቀ ለመጋደል መንደርደር በምን መስፈርት ትክክል እንደሚሆን አይገባንም። ስለዚህ ህዝብ ” ንቃ” ለማለት እንወዳለን። ለማንና ለምን ዓላማ እንደሚደወልልህ እወቅ። ረጋ ብሎ መመርመር ለጥሩ ውሳኔ ይረዳል። ከጸጸትም ይጠብቃልና።

ይህንን ” ከርስ ተክር” ልዩነት፣ ግጭቶ የጥቅም በመሆኑ ነው “ከርስ ተኮር” የምንለው፤ ለፖለቲካ ዓላማቸው ለማዋል የሚራወጡትን ስናይ ድንጋጤያችን ይበዛል። ሃዘናችን ይገዝፋል። ልባችንም ምቱ ይጨምራል። ለምን ቢባል አያያዙ አያምርምና!! ነጥቦች እናንሳ

ብዙ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። ከላይ በመግቢያ እንዳልነው ” ከሜሲ በላይ ሊከፈለኝ በተገባ ነበር” ከሚሉን ዘራፊ ፓስተሮች ጀመሮ የዕምነት ቤቶች ስለቆሸሹ ለክፉ ተግባራት ተጋልጠዋል። ይህንኑ ሌብነታቸውን ስለሚያውቁና ስለሚንቋቸው ፖለቲከኞች እንዳሻቸው ይነዱዋቸዋል። እነሱ ረክሰው ሕዝቡን ያዋርዱታል። አንድ መመሸጊያ፣ ድህነቱንና ብሶቱን መናዘዣ ቤት ቢኖረው፣ ይህንኑ ሊያሳጡት ደርሰዋል።

ምንም እንኳ የጸዳ ጀርባ ስለሌላቸው ብትንቅቋቸውም ፖለቲከኞች እባካችሁን ከህዝብ ብቸኛ ቅርስ ” ዕምነቱ” ላይ ውረዱ። የምታዛንፉት ፍትህና የምትዘርፉት ሳያንሳችሁ ይህን ህዝብ አታስቀይሙት። ስሜት ውስጥ ለመግባት የተደላደለ አቋም እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራውን ትውልድ በጥበብ አሳልፉት።

ምን ነክቷቸው እንደሆነ ባይታወቅም ዶክተር ብርሃኑ ነጋን የወቀሱት ዶክተር ዳናቸው እንዳሉት ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈተና ማለፍ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ምን ያህል እንደሆነ አሳውቀውናል። እንደ ማህበረሰብም ሆነ እንደ አገር መውደቃችንን ያሳየን ፈተና፣ አገሪቱን የሚመሩዋት በአብዛኛው ወይም ከጥቂቶቹ በስተቀር ብቃቱ፣ አቅሙና የስብዕና ጥራት የሌላቸው እንደሆኑ አሳይቶናል። በግዢና በግብዣ በሚታደል ዲግሪ የተሽሞነሞኑት መሪዎች በገፍ በሌብነት ፈተና እያለፉ የመጡ ናቸውና ብዙ አንጠብቅ።

ኢትዮጵያ ለውጥ ትሻለች። ይህ ምንም ጥርጥር የለውም። ግን ለውጡ ሃይማኖትና እምነትን ታኮ በነውጥ እንዲመጣ የሚታሰብ ከሆነ እንደ አገር የማይመለስ ኪሳራ፣ ዳግም ሊያንሰራራ የማይችል ውድቀት ውስጥ እንቀረቀራለን። እንኳን ለጸሎት ቤት በሰፈር መቆሚያምም ላይኖረን ይችላል። በሃይማኖት ሰበብ የሚለኮስ እሳት ሲበላ አይመርጥም። ማንም ሰካራም ዳንክረኛና አርጥራጭ፣ በኢትዮጵያ ላይ የሴራ መርዝ እንዲረጩ የሚከፈላቸው፣ ለኢትዮጵያ መፍትሄ ለማበጀት ካይሮ ከተሰበሰቡ የሚገኝ በጎ ነገር የለምና እንጠንቀቅ። ለውጡ በድርጅት፣ በጥበብ፣ በምርጫ እናድርገው። ሶስት ዓመት ቀላል ጊዜ ነውና። ከዚ ውጭ በትርምስ ትርምስምስ ማለት እንጂ ሌላ ጥቅም አይገኝም። ለማዘን እንኳን ጊዜ አይኖረንም። ኢትዮጵያ የተሰራችበትን የጎሳ ፖለቲካና ህገ መንግስቷንም አንርሳ። ኢትዮጵያ ብዙ ነገሯ ዥጉርጉር ነው። አንድ ቀለም ብሎ ነገር የለም። ሚዲያም የራሱን ሃላፊነት ይወጣ። የተወረወረውን ሁሉ መለጠፍ አይጠቅምም። “እገሌ እንዲህ አለ” ብሎ ከማሰራጨትና ከማራባት በፊት መመርመር ደግ ነው።

ሰላም ይስጠን!!

Exit mobile version