Site icon ETHIO12.COM

ክልሎች የህገመንግስት አግባብን ጠቅሰው ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው

“መንግስት ባለፉት የለውጥ አመታት ህገመንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ ለእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድነት ለአገራዊ አንድነት መጠናከር እጅግ አሰፈላጊ መሆኑን በማመን የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል” ሲል ያስታወቀው የቤኒሻንጉል ክልል ” መንግስት ከህገመንግስታዊ ስርዓቱ ውጭ የሆነ መፍትሔ መስጠት እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ የተሠጠ መግለጫ

ሀገራችንን ወደብጥብጥ በማስገባት የምናተርፈው ባለመኖሩ፣ ሠላማዊ ሂደቶችን መከተል ማስቀደም ከሁሉም ይጠበቃል።

ሠሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የእምነት አባቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ መንግስት ችግሩ በውይይትና መግባባት ላይ ተመሥርቶ እንዲፈታ ጽኑ አቋም ይዞ እየሠራ ይገኛል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የእምነት አባቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በቤተክርክቲያኗ የውስጥ አሠራር በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪውን ያቀርባል።

በእምነቱ አባቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የተለያዩ አካላት አጋጣሚውን በመጠቀም ሀገራችንን ወደግጭት ለማስገባት እየሠሩ እንደሚገኙ መገንዘብ ያስፈልጋል።

መንግስት ባለፉት የለውጥ አመታት ህገመንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ ለእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድነት ለአገራዊ አንድነት መጠናከር እጅግ አሰፈላጊ መሆኑን በማመን የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል። በዚህም ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ከዚህ ባሻገር መንግስት በእምነት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች በዋናነት መፍትሄ የሚያገኙት በራሳቸው በተቋማቱ የውስጥ አሰራር በመሆኑ፣ መንግስት ከህገመንግስታዊ ስርዓቱ ውጭ የሆነ መፍትሔ መስጠት እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል።

በአኢትዮዽያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበ ከመሔዱ ባለፈ፣ በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ የፓለቲካ ኃይሎች ተቀናጅተው ኢትዮዽያን ለማዳከም ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ሚስተዋለው አዝማሚያ መረዳት ይቻላል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄዱና የሀገርና የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅሳቃሴዎች ውጤታቸው የከፋ በመሆኑ ድርጊቱን እንደሚቃወም ለመግለጽ ይወዳል።

በተለይም ደግሞ ለአገራችን ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ዝግጅት እየተጠናቀቀ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ስልጣን በተሰጠው አካል ያልተፈቀደ እና ለሀገርና ለዜጎች ደኅንነት ስጋት የሚፈጥር የሕገወጥ ሰልፍ ቅስቀሳ ማድረግ ተገቢነት እንደሌለውም ያሣውቃል።

በመሆኑም የክልሉ መንግስት ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ ማናቸውንም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ያሣስባል።

በተጨማሪም የፌዴራል የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለሀገር ሠላምና ለዜጎች ደኅንነት ሲባል ያስቀመጣቸውን ውሳኔዎች የመፈፀምና የማስፈፀም ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ይወጣል።

መንግስት ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃለፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት ሁሉ ሕዝብ አሰፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደረ‍ደርግ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት

የካቲት 03/2015 ዓ.ም

አሶሳ፣

Exit mobile version