Site icon ETHIO12.COM

” የኦንጎታ!”አምስት ሰዎች ብቻ የሚናገሩት ቋንቋ

ወይጦ ወንዝ የብራይሌ ብሔረሰብ የኑሮ መሠረት ነው።

ብራይሌዎች ከወንዙ የሚያገኟቸው ዓሳዎች እና በዳርቻዎቹ የሚበቀሉት ፍሬዎች እና ስራስሮች ዋነኛ የምግብ ምንጫቸው “ነበር”።

ዛሬ አከባቢው ክፉኛ በድርቅ ተጎድቷል። ወይጦም ለመድረቅ ተቀርቧል። ምግብ ብርቅ ሆኗል።

ከብት የሚያረቡ አርብቶ አደሮች ቁጥርም እጅግ ጥቂት ነው።

ነዋሪዎቹ ይተዳደሩበት የነበረው የንብ እርባታ እና አነስተኛ እርሻ “የለም” ወደሚባል ደረጃ ደርሷል።

የወይጦ ወንዝ ብቻ ሳይሆን ቋንቋቸው ወደ መጥፋት ተቃርቧል።

የብራይሌዎች ቋንቋ ኦንጎታ ይባላል። አሁን ኦንጎታን አምስት ሰዎች ብቻ የሚናገሩት ቋንቋ ነው። ቋንቋውን ባይናገሩም እንረዳዋለን የሚሉ ሰዎች ግን አሉ።

ጎምቦ ቃሮ ከአምስቱ የቋንቋው ተናጋሪዎች አንዷ ናቸው።

ከጊዜ በኋላ በአካባቢው የሚወለዱ ልጆች ከኦንጎታ ይልቅ የአጎራባቻቸው የጸማይ ብሔረሰብን ቋንቋ ጸማይኮን ወደ መናገር ማዘንበላቸውን ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የዚህን ምክንያት ሲያሰረዱ አርብቶ አድር የሆነው የብራይሌ ነዋሪ ወደ ጸማይ እና ሌሎች አጎራባቾች በሚንቀሳቀስበት እና በሚቆይት ጊዜ ጸማይኮን መጠቀሙ ነው ይላሉ።

“እዚያ [ጸማይ] የተወለዱ ልጆቻችን ደግሞ ጸማይኮን ለመዱ። እኛም ደግሞ የጸማይ ሰዎችን ማግባት ጀመርን። ጸማዮችም እኛን ያገቡናል” የሚሉት ጎምቦ ለቋንቋው ተናጋሪዎች መመናመን ዋነኛው ምክንያት ይህ እንደሆነ ያምናሉ።

ቋንቋቸውን ለልጆቻቸው ማስተማር ቢፈልጉም ጥቂት ቃላትን እንዲያውቁ ከማድረግ በዘለለ ጥረታቸው ፍሬያማ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ልጆቻቸውም በቋንቋው መግባባት እንፈልጋለን፤ ቋንቋቻን እንዲጠፋ አንፈልግም ይላሉ።

ቦዳ ጌዳ የጌዳ ቃውላ ልጅ ነው። ጌዳ ቃውላ ደግሞ ኦንጎታን ቋንቋን ከሚናገሩት አምስት ሰዎች አንዱ ናቸው።

ቦዳ አፉን የፈታው በጸማይኮ ሲሆን እንደ “በዳዳ ከዋስ” ያሉ “እንዴት ዋላችሁ” የሚል ትርጉም ካላቸው ጥቂት የኦንጎታ ቃላት በቀር ቋንቋውን አያውቅም።

ቦዳ በደቡብ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን የባሕል ኪነት አባል ሲሆን፣ ከአባቱ የተማራቸውን በኦንጎታ ቋንቋ የሚዜሙ የብራይሌ ዜማዎችን ይጫወታል።

ዜማዎቹ በደስታ ወይም በሐዘን ጊዜ ማኅበረሰቡ ለዘመናት ሲያቀነቅናቸው እና ሲያንጎራጉርባቸው ከመውረሱ ባሻገር የግጥሙን ይዘት በጥልቀት አይረዳውም።

እናቱ የጸማይ ብሔረሰብ አባል የሆነችው ቦዳ “ቋንቋውን መማር እፈልጋለሁ። ግን እንዴት አድርጌ መማር እችላለሁ? በመጀመሪያ የእኛ አፍ መፍቻ ጸማይኮ ሆኗል” ሲል ይናገራል።

ወሮ ሞሌም የዚሁ ብሄር ተወላጅ ሲሆን የኦንጎታ ቋንቋ ችሎታው እንደ ቦዳ ነው።

የወሮ አባት ሞሌ የኦንጎታ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገሩ የነበረ ሲሆን፣ በ1999 ዓ.ም. ላይ ሕይታቸው አልፏል። ያኔ ቋንቋውን የሚናገሩ ሰዎች አሁን ካሉት ይበልጥ እንደነበር ወሮ ይናገራል።

“አሁን ላይ [በአካባቢው] ይሄ ቋንቋ ይጠቅመኛል ብሎ የሚያምን ወጣት የለም” የሚለው ወሮ ኦንጎታን ባለማወቁ ከመቆጨት ባሻገር አሁን ቋንቋውን ለመማር እየሞከረ ነው።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የባሕል እና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሰኢድ አህመድ (ዶ/ር)፣ በጸማይኮ ተጽእኖ ምክንያት የኦንጎታ ቋንቋን የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር በዓመታት ውስጥ እያሽቆለቆለ መሄዱን ይናገራሉ።

ሰኢድ (ዶ/ር) በ1999 የቋንቋው ተናጋሪዎች 15 እንደነበሩ በወቅቱ የተደረገ ጥናትን ዋቢ አድርገው ይገልጻሉ።

ባለፈው ዓመት የተገኘ መረጃ ደግሞ የቋንቋው ተናጋሪዎች ሰባት ናቸው እንደሚል የተናገሩት ዳይሬክተሩ “እኛ በዚህ ዓመት ባደረግነው ምልከታ ይህን ቋንቋ የሚናገሩት ሁለት ሴቶች እና ሦስት ወንዶች ናቸው” ብለዋል።

ቋንቋውን የሚናገሩት አምስቱ ሰዎች ማን ናቸው?

የደቡብ ክልል ቴሌቪዥን በቅርቡ ባሰራጨው መረጃ መሠረት የብራይሌ ብሔረሰብ ተወላጆች አጠቃላይ ቁጥር 365 ነው።

ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ የማኅበረሰቡብ ቋንቋ የሚናገሩት አምስቱ ሰዎች ብቻ ናቸው።

የኦንጎታን ቋንቋ በሚናገሩት ብቸኞቹ ሁለት ሴቶች እና ሦስት ወንዶች መካከል ዝምድን አለ። ሁለቱ ወንደማማቾች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ሁለቶች ደግሞ እህት እና ወንድም ናቸው።

ጎምቦ ቃሮ በአካባቢው የሃብት መለኪያ የተሻለ ኑሮ ላይ ያሉ ሲሆን፣ ፍየሎች እና ሁለት በሬዎች አሏቸው። የተቀሩት አራት ሰዎች ድርቁ ክፉኛ በርትቶባቸው በመንግሥት የስንዴ ድጋፍ ያሉ እና ጥሬ ሙዝ እስከ መመገብ እንደደረሱ ይናገራሉ።

ለዚህ ነው ሰኢድ (ዶ/ር) ለእነዚህ ሰዎች በተለየ መልኩ የምግብ ዋስትናቸው የሚረጋገጥበት መንገድ እንዲዘረጋ የሚጠይቁት።

ኦንጎታ ቋንቋ ከመጥፋት መዳን ይችላል?

ለዚህ ጥያቄ የሰኢድ አህመድ (ዶ/ር) ምላሽ “አዎ ይችላል” የሚል ነው። ግን ጊዜው አጭር በመሆኑ ፍጥነት እና “የተለየ ትኩረት” ይፈልጋል ይላሉ።

ነገር ግን በኣካባቢው ባለው ኣሳሳቢ ድርቅ የተነሳ ማኅበረሰቡ ከባድ አደጋ ውስጥ በመሆኑ ከቋንቋው በፊት የሰዎቹን ሕይወት ማዳኑ ሊቀድም ይገባል በማለት ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

“መንግሥትም ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እነዚህን ሰዎች በሕይወት እንዲቆዩ ካደረጉልን ቋንቋው በአጭር ጊዜ ሊመለስበት የሚችለበት ዕድል አለ።”

ጨምረውም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ከመጥፋት አፋፍ ላይ የሚገኘውን ቋንቋ ለመታደግ የበኩሉን ሥራዎች መጀመሩን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የኦንጎታ ቋንቋን ተናጋሪዎችን ለማበራከት ግዕዝን እንደ አብነት በመውሰድ ለመሥራት አቅዷል።

“ግዕዝ አሁን ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው ያለው። በግዕዝ አፉን የሚፈታ የለም። ይህንን ምሳሌ በማድረግ የአዋቂዎች መሠረተ ትምህርት ወይም የተግባር ትምህርት በማስተማር እነኚን አምስት ሰዎች ሕብረተሰቡ በሚሰባሰብበት ቦታ እንዲያስተምሩ ለማድረግ እያሰብን ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል ቋንቋውን ባይናገሩም እንሰማለን የሚሉ ሰዎች መኖራቸው ትልቅ ተስፋ እንደሆነም ያስረዳሉ። “ሕብረሰተሰቡ ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት” ህጻናት አፋቸውን እንዲፈቱበት ማድረግ እንደሚቻልም ያስረዳሉ።

“ጠብ” የሚል ነገር የለም እንጂ ጥናት ለዚህ ቋንቋ እና ብሄረሰብ አዲስ አለመሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጎምቦ ቃሮም በየጊዜው ቋንቋውን “እናጠናለን” የሚሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው በተደጋጋሚ መምጣታቸውን ያስታውሳሉ።

“ፈረንጆች ይመጣሉ፣ ከመንግሥት ከዩኒቨርሲቲም ይመጣሉ። ግን እስካሁን ድረስ ጥናታቸው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ እንኳን የነገረን የለም። ‘ተመልሰን እንመጣለን’ ካሉን በኋላ በዚያው  ይቀራሉ።”

በርካታ አጥኚዎች አካባቢውን በመጎብኘት የማኅበረሰቡን አባላት በመጠየቅ የተለያዩ ጥናቶች እንዳደረጉ ቢታመንም፣ ሌላው ቢቀር ኦንጎታ በየትኛው የቋንቋ ምድብ እንደሚካተት የሚታወቅ ነገር የለም።

ወጌ፡ የተረሳው የብራይሌ በዓል

ብራይሌዎች በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በበናጸባይ ወረዳ ውስጥ ይገኛሉ።

የብራይሌ ብሔረሰብ ከተለያዩ ብሔረሰቦች የመጡ ሰዎች የመሠረቱት እንደሆነ ጎምቦ ስለ ብሔረሰቡ አመጣጥ ከአያት እና ከአባቶቻቸው የሰሙትን “አፈ ታሪክ” መሠረት አድርገው ይናገራሉ።

ደቡብ ክልል ስር ከሚገኙት ከጸማይ፣ ከገማሌ፣ ከገማዳ እና ከሌሎች ብሔረሰቦች እንዲሁም ከኦሮሚያ ከቦረና አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተሰደዱ ሰዎች ሙሴ በተባለው የወይጦ ወንዝ ዳርቻ ላይ ከተሰባሰቡ በኋላ ማኅበረሰቡ እንደተመሰረተ ይነገራል።

ከዚያም ኦንጎታ ቋንቋን የጋራ መግባቢያ አድረገው በመጠቀም ለዘመናት ቆይተዋል።

ብራይሌዎች በደቡብ ክልል እንዳሉ ሌሎች ብሔረሰቦች የሚሰባሰቡበት የሚደምቁበት የዘመን መለወጫ በዓል ነበራቸው።

ጎምቦ፣ ወሮ እና ቦዳ ይህ በዓል እንዴት እንደሚከበር ይናገራሉ።

ኤሌቤ በሚባለው ዛፍ ስር የብሔረሰቡ ተወላጆች ይሰባሰባሉ። በቆሎ፣ ቦርዴ እና አረቄ ይቀርባል። ፍየል ይታረዳል። ተበልቶ ተጠጥቶ ምርቃት ይደረጋል። ከዚያም “ወጌ ወጌ” እየተባለ ይጨፈራል።

ይህ የብሔሩ ተወላጆች የሚሰባሰቡበት እና የሚመራረቁበት በዓል ከተከበረ 16 ዓመታት ተቆጥረዋል።

የብሔረሰቡ ብቸኛ በዓል ለመጨረሻ ጊዜ ሲከበር የ10 ዓመት ልጅ የነበረው ቦዳ የሚያስተውሰውን ሲናገር “እህሉ እንደደረሰ ሁሉም የብሔረሰቡ አባላት የደረሰ እህላቸውን ከመብላታችው በፊት ጫፍ ጫፉን ይይዙና ይመጣሉ። ከዚያ በእንጨት በተሰራ ዕቃ [መያዣ] ይሰበሰባል። ተመርቆ ሰው እሸቱን ይበላል” ሲል ያስታውሳል።

ሆኖም በብሔረሰቡ ትልቅ ተሰሚነት የነበራቸው የወሮ አጎት ከሞቱ በኋላ የቀሩትን የማኅበረሰቡን አባላት የሚያሰባስብ በመጥፋቱ እና በኑሮ ዘይቤ መቀየር ምክንያት በመራራቃቸው ይህ በዓል ታሪክ ሆኖ መቅረቱን በቁጭት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ወሮም ይሁን ቦዳ በዓል እና ቋንቋቸውን እንደሚወዱ፤ መማር እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ። የእኩዮቻቸው ፍላጎትም ይኸው ነው።

ወሮ “ቋንቋችን ከሌለ ብሔረሰባችን አይኖርም። የእኛ ቋንቋ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። እየሞተ ነው” ሲል ቦዳ ደግሞ ቋንቋውን አለማወቁ “በጣም በጣም” ይሰማዋል።

ጎምቦ ቃሮ እና የተቀሩት የቋንቋው ተናጋሪዎች ለልጆቻቸው ቋንቋ እና ባሕላቸውን ለማስተማር ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ጥያቄው ግን በየጊዜው ከሚደረገው “ጥናት” ባሻገር የጎምቦን እና የቦዳን ትውልድ ማን ያስተሳስር? ቋንቋውስ እንዴት ይቆይ? የሚለው ነው።

ነጋይ ኩኩ – ደህና ሰንብቱ! credit – BBC Amharic

Exit mobile version