Site icon ETHIO12.COM

ተስፋ የተጣለባት ኢትዮጵያዊት አትሌት መጨረሻ ለምን እድሜ ልክ እስር ሆነ?

አትሌት በሱ ሳዶ ከሁለት ወንድሞቿ እና ከሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በመሆን ባለቤቷን በመግደል ወንጀል ተከሳ፣ ድርጊቱን መፈጸሟ በመረጋገጡ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባታል።

የመካከለኛ እና የረዥም ርቀት ሯጯ አትሌት በሱ ሳዶ፣ ከተባባሪዎቿ ጋር በመሆን ወንጀሉን የፈጸመችው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ መሆኑን ከሰጠችው የእምነት ክህደት ቃል መረዳት ይቻላል።

ሟችን እና አትሌት በሱን በቅርበት የሚያውቋቸው መሆናቸውን የሚናገሩት የአዳማ አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ ሐብታሙ ግርማ ስለ ግድያው ሲናገሩ “እኔ በጣም ነው ያዘንኩት፤ በእርሱ ሞትም በጣም አዝኛለሁ። የእርሷም እስር ከሞት የማይተናነስ በመሆኑ እና አገሪቱም እንዲህ ዓይነት ሰው በማጣቷ በጣም ነው ያዘንኩት” ብለዋል።

የአትሌት በሱ ሳዶ የቀድሞ አሰልጣኝ ስለ ሁኔታ ቢቢሲ ባናገራቸው ጊዜ የተፈጸመውን ወንጀል አምነው መቀበል እንዳዳገታቸው ሲናገሩ “እኔ አሁን ራሱ ይሄ ነገር እንዴት አንደተፈጠረ ሊገባኝ አልቻለም” ሲሉ ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል።

የመካከለኛ እና የረዥም ርቀት ሯጯ አትሌት በሱ ሳዶ እንዲሁም አብሯት የነበረው ወንድሟ ከባለቤቷ ግድያ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ቤት የእድሜ ልክ እስራት በይኖባቸዋል።

ነገር ግን ሌላ ወንድሟ እና ከሻሸመኔ በገንዘብ ገዝቶ ያመጣቸው ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉ በተፈጸመበት ምሽት በማምለጣቸው እስካሁን በቁጥጥር ስር አልዋሉም።

የተከሰተው ምንድን ነው?

አትሌት በሱ እና የቀድሞ አትሌት ከነበረው ባለቤቷ ተሻለ ታምሩ ጋር ከስምንት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ አብረው በትዳር መቆየታቸውን የፖሊስ ሰነድ ያስረዳል።

ተሻለ ሩጫ ካቆመ በኋላ በሰንዳፋ ከተማ 01 ቀበሌ፣ ሶላር ፋብሪካ ወይንም ጎማጣ የሚባል ቦታ ከባለቤቱ ጋር ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በስልጠናም ይረዳት ነበር።

የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያስረዳው ባለፈው ዓመት ነሐሴ 08/2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ ተሻለ በመኖርያ ቤቱ ውስጥ ተገድሏል።

የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ አየለ ኢማሙ፣ በዚያን ቀን በግምት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ የተፈፀመውን ነገር ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ወንጀሉ በተፈጸመበት ምሽት ተጠርጣሪዋ አትሌት በገንዘብ ገዝታ አምጥታቸዋለች የተባሉ ግለሰቦችን የመኝታ ክፍል ውስጥ እንዲደበቁ ማድረጓን ይናገራሉ።

“ባል ተሻለ ውጪ ቆይቶ ሁለት ሰዓት አካባቢ ቤት ከገባ በኋላ፣ ሳሎን ተቀምጦ የእጅ ስልኩን በሚነካካበት ወቅት እነዚህ በገንዘብ የተገዙ ሰዎች ከተደበቁበት ወጥተው በብረት መትተው እና በስለት ወግተው ግድያውን ፈፀሙ።”

በዚህም የተነሳ ሟች ወድያውኑ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ ከዚያም ግድያውን በመተባባር የፈጸሙት ግለሰቦች የሟችን አስከሬን አውጥተው መንገድ ላይ እንደጣሉት ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

“ሚስት ደግሞ ከእርሷ ጋር ከሚኖር ወንድሟ ጋር እንዲሁም ከቤት ሠራተኛዋ ጋር በመተባበር ቤት ውስጥ የፈሰሰውን ደም አፀዱ፤ የሶፋውን ጨርቅ አውጥተው አጥበው፣ የሟችን ልብስ እና ደም የነካውን ምንጣፍ ሰብስበው. . .” መደበቃቸውን የአትሌት በሱን የእምነት ክህደት ቃል በመጥቀስ ያስረዳሉ።

በግድያ ወንጀሉ ውስጥ በሱ እና ከእርሷ ጋር የሚኖረው ወንድሟ፣ እንዲሁም ከሻሸመኔ ሁለት ተጠርጣሪዎችን ያመጣው ሌላ ወንድሟን ጨምሮ በአጠቃላይ አምሰት ሰዎች መሳተፋቸውንም አክለው ገልጸዋል።

ባል ከተገደለ በኋላ ከሻሸመኔ የመጡት ተጠርጣሪዎች እና አንድ ወንድሟ የዚያኑ ዕለት ምሽት አምልጠው መጥፋታቸውን ዐቃቤ ሕጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚያ በኋላም ቀድሞ አብሯት የሚኖረው ወንድሟ እና እርሷ ቤት ውስጥ ቆይተው ሟች “ወደ ቤት እንዳልገባ ለወዳጆቻቸው እየደወሉ ሲናገሩ ነበር።”

መንገድ ላይ የሟች አስከሬን ተጥሎ ከተገኘ በኋላ መረጃ የደረሰው ፖሊስ ምርመራውን ከባለቤቱ አትሌት በሱ ነበር ጀመረው።

ዐቃቤ ሕግ “ሟች በማኅበረሰቡ ዘንድ ተወዳጅ ስለነበር በግድያው ማኅበረሰቡ በጣም ተከፋ፤ የፀጥታ ሰዎች ቀድመው ባይደርሱ ኖሮ ባለቤቱ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችል ነበር” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ከምርመራ በኋላ “እርሷም ከተባባሪዎቿ ጋር በመሆን ባሏን ያስገደለችው መሆኗን አምናለች” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የምስሉ መግለጫ,በሱ በለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በተሳተፈችበት ጊዜ

የግድያው ምክንያት ምንድን ነው?

አትሌት በሱ እና ባለቤቷ መካከል ይህ ችግር ከመከሰቱ በፊት ወደ ሕግ ቀርቦ ቅሬታ ወይንም ስጋቱን የገለጸ አካል የለም። ነገር ግን በጥንዶቹ መካከል ግጭት እንደነበር ዐቃቤ ሕጉ ጠቅሰዋል።

በሱ ባለቤቷ “እንዳይሳካልን በቤተሰቤ፣ በእናቴ፣ በወንድሞቼ እና በእኔ ላይ ያስጠነቁላል” በሚል ይህንን ወንጀል እንደፈጸመች ቃሏን በሰጠችበት ወቅት መናገሯን ተናግረዋል።

በጥንዶቹ መካከልም ከገንዘብ ጋር በተያያዘ አለመግባባት እንደነበር ተከሳሿ በሰጠችው የእምነት የክህደት ቃል ላይ መስፈሩን ተገልጿል።

የትዳር አጋሮቹ በቆይታቸው ልጅ ባይኖራቸውም የተለያየ ንብረት አፍርተዋል።

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፊንፊኔ ዙርያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (አሁን የሸገር ከተማ የተባለው) በጥር 09/2015 ዓ.ም. የእድሜ ልክ እስራት ውሳኔውን በእርሷ እና በወንድሟ ላይ አስተላልፏል።

ሁለቱ የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች በቀጥታ ግድያው ላይ ባይሳተፉም “አብረው በማሴር ግድያ የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ጠርተዋል። ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ ሟች እንደጠፋባቸው በማስመሰል ለሰዎች ሲያወሩ ነበር” ሲሉ ዐቃቤ ሕጉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በተጨማሪም የቤት ሠራተኛዋ ይህንን ጥፋት እንዳትናገር ገንዘብ እንደሚሰጧት በመናገር ለመደለል መሞከራቸውን ለፖሊስ ቃሏን ሰጥታለች።

ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ግን የዚያኑ ዕለት ሌሊት ስለጠፉ እስካሁን ድረስ ያሉበት እንዳልታወቀ እና በፖሊስ እየተፈለጉ መሆናቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

ከዚህ ግድያ በፊት ይህች አትሌት ሟችን እንደምታስገድለው ትዝትበት እንደነበር ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ወቅት እንደ ደረሰበት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አትሌት በሱ ሳዶ ማን ናት?

የ27 ዓመቷ አትሌት በሱ ሳዶ እና ባለቤቷ ተሻለ ታምሩ የአዳማ አትሌቲክስ ክለብ አባል ነበሩ። የክለቡ ረዥም ርቀት አሰልጣኝ ሐብታሙ ግርማ ሁለቱን አትሌቶች ማሰልጠናቸውን ይናገራሉ።

“እኔ ለሁለቱም እንደ አባት ነኝ” የሚሉት አሰልጣን ሐብታሙ፣ አትሌቷ በጠባይዋ ምስጉን እንደሆነች “በሱ ሳዶ እንዲህ ዓይነት ነገር ትፈጽማለች ብዬ አስቤም አላውቅም” ሲሉ የሆነውን ማመን እንደከበዳቸው ይገልጻሉ።

አትሌት በሱ በዓለም መድረክ ላይ ተስፋ እንደነበራት ሲናገሩም “የገጠማት ጉዳት ትንሽ ያስቸገራት እንጂ ማራቶን ላይ ውጤታማ ልትሆን ትችላለች ብዬ አስብ ነበር” ይላሉ።

የአትሌቷ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አትሌት በሱ አገርን ወክላ ኦሊምፒክ ላይ ጭምር ተሳትፋለች።

በብራዚል ሪዮ ኦሊምፒክ፣ በለንደን እና በቤይጂንግ በተካሄዱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ በ1500 ርቀት አገርን ወክላ ተሳትፋለች።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመትም ሜክሲኮ ላይ በተደረገ ግማሽ ማራቶን ስታሸንፍ፣ ፓሪስ ላይ በተደረገ የማራቶን ውድድር ላይ ተሳትፋ በሦስተኝነት ጨርሳለች።

በሌላ በኩል ደግሞ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ናት።

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ደግሞ በ1500 ሜትር ለሦስት ዓመታት ሻምፒዮና ሆናለች።

ባለፈው ዓመት በ2014 ዓ.ም በተካሄደው የኦሮሚያ የክለቦች መመዘኛ ላይ ክለቧን ወክላ ሮጣ በ10ሺህ ሜትር አሸንፋለች።

Exit mobile version