Site icon ETHIO12.COM

መኪናው ውስጥ ያገኘውን የወርቅ ሸዋሊያ ጌጥ ለባለቤቷ የመለሰው የድሬዳዋ ነዋሪ ወጣት

መኪናው ውስጥ ያገኘውን 170 ሺህ ብር ዋጋ የሚገመት የወርቅ ሸዋሊያ ጌጥ ለባለቤቷ በመመለስ አርዓያነት ያለው ተግባር የፈጸመው የድሬዳዋ ነዋሪ ወጣት ከፖሊስ ምስጋና ተቸረው።

ወጣቱ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ናርዶስ ዳንኤል ሲባል በተሽከርካሪው ውስጥ ወድቆ ያገኘውን 170 ሺህ ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው የወርቅ ሸዋሊያ ጌጥ ለባለቤቷ መመለሱ ተገልጿል።

ወጣት ናርዶስ ነዋሪነቱ በድሬደዋ ከተማ ቀበሌ 05 ሲሆን በሚያሽከረክረው መኪና የእለት ተዕለት ህይወቱን ይመራል።

ወጣት ናሮዶስ እንደ ወትሮው ሁሉ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ሳለ ወይዘሮ ጀሚላ አደም በምሽት ከነበሩበት አካባቢ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዲያደርሳቸው ይጠይቁታል እሱም ግለሰቧን መኖሪያ ቤታቸው አድርሶ የአገልግሎቱ ክፍያ ተቀብሎ ይመለሳል።

በማግስቱ ጠዋት እንደ ወትሮው ሁሉ ወደ ሥራው ሊያመራ ተሽከርካሪውን በማፅዳዳት ላይ ሳለ አንድ የወርቅ የእጅ ጌጥ (ሸዋሊያ) በተሽከርካሪው ውስጥ ወድቆ ያገኛል።

ወጣት ናርዶስ ያገኘውን ሸዋሊያ ለግል ጥቅሙ ለማዋል አላሰበም ይልቁኑም ምሽት ላይ አሳፍሯቸው የነበሩት ግለሰብ ንብረት ሊሆን እንደሚችል በመገመት ወደ መኖሪያ ቤታቸው በማምራት ግለሰቧ ይጠይቃል።

ለግዜው በቤታቸው አለመኖራቸው ይነገረዋል። ግለሰቧ በተመለሱ ግዜ በስልኩ እንዲደውሉለት የስልክ ቁጥሩን ሰጥቶ በመመለስ ያገኘውን የወርቅ የእጅ ጌጥ ለሳቢያን ፖሊስ ጣቢያ ያስርክባል።

የወርቅ ጌጡ ባለቤትም ወደ ቤታቸው እንደተመለሱ ወደ ወጣት ናርዶስ ዳንኤል በመደወል የወርቅ ጌጣቸው ካለበት ፖሊስ ጣቢያ የቀርቡ ሲሆን የፖሊስ ጣቢያውም ጊዜ ወስዶ የወርቅ ጌጡ የግለሰቧ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማጣራት ካከናወነ በኋላ ወጣት ናርዶስ ዳንኤል በተገኘበት ለግለሰቧ ሻዋልያውን ማስረከቡን ኢዜአ ዘግቧል።

የግል ጥቅምና ነዋይ ሳያታልለው በተሽከርካሪው ውስጥ ወድቆ ያገኘውን የወርቅ ጌጥ ለባለቤቱ እንዲመለስ በማድረግ ለሌሎች ምሳሌ መሆን ለቻለው ወጣት ናርዶስ ዳንኤል የድሬዳዋ ፖሊስ የላቀ ምስጋና አቅርቦለታል።

Via EPD

Exit mobile version