Site icon ETHIO12.COM

ከሃይማኖት ወደ ጤፍ ፖለቲካ እድገት ያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚገመድ ሴራ

ሰሞኑንን አዲስ አበባን በጤፍ አቅርቦት ጠኔ ለመምታት ዝግጅት መኖሩ ሲሰማ ነበር። ጤፍ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ ሲሰራ እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሲጽፉ የታዩ አሉ። ይህ በተሰማ በሳምንት ጊዜ ውስጥ የጤፍ ዋጋ በሚገርም መልኩ አሻቅቧል። ይህ አቅርቦትን የማገድ ሴራ የአዲስ አበባን ህዝብ በእጅጉ የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን ለአመጽም የሚያነሳሳው ነው።

ያነጋገርናቸው ዕህል ነጋዴዎች እንደሚሉት የጤፍ ችግር የለም። ምርቱ በብዛት ነው። ነገር ግን በግልጽ ባላወቁት ምክንያት ቀደም ሲል ኢስያቀርቡላቸው ወይም ሲልኩላቸው የነበሩ ነጋዴዎች አቁመዋባቸዋል። ለጊዜው የሚያውቁት ይህን ብቻ ነው። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልደረቦቻቸው የጤፍ ዋጋ አስመራ እየረከሰ ወይም እየወረደ መሆኑንን እንደገለጹላቸው አመልክተዋል። ለምን እንዴት ሊረክስ እንደቻለ ግን ግልጽ አላደረጉም። ኢትዮጵያና ኤርትራ በተሰማማኡ ማግስት የተዘጋው ድንበር ሲከፈት ተጀመሮ በነበረው ልቅ ንግድ በተመሳሳይ አሁን እንደተሰማው ዕህል ረክሶ እንደነበር ይታወሳል።

ዕህል እንዳይወጣና ወደ ገበያ እንዳይላክ የሚደረገው ሴራ በዚህ ከቀጠለ ክልሎች በተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ፍርሃት ያላቸው፣ እንዲህ ያለ ህዝብን ለስቃይ የሚዳርግ ሴራ ጣታው ብዙ እንደሚሆን ያስተነቅቃሉ። ኢዜአ ነዋሪዎችህን ማነጋገሩ ጠቅሶ የሚከተለውን ዘግቧል።

 ሳሙኤል ወንደሰን እና አዲሱ ገረመው

አዲስ አበባ፦ በቂ የጤፍ አቅርቦት ባለመኖሩ እና በጤፍ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመደረጉ ጤፍ ገዝተን እንጀራ መብላት አልቻልንም ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጤፍ ሲገዙ ያገኘናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሮ አረጉ ጥፍጤ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የጤፍ ዋጋ በጣም ጨምሯል፤ በወፍጮ ቤቶች ጤፍ የለም። በአንዳንድ ወፍጮ ቤቶች ቢገኝም እንደጤፉ ዓይነት እስከ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል።

25 ኪሎ ጤፍ በሁለት ሺህ ብር ገዝቻለሁ ያሉት ወይዘሮ አረጉ፤ ነገር ግን ዋጋው በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ «ጤፍ ገዝቼ እንጀራ የምበላ አይመስለኝም» ሲሉ ገልጸዋል። በተጠቀሰው ዋጋ ለመግዛት ምርቱን ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቅሰው፤ መንግሥት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ ሊያየው ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው፤ በገበያው ላይ በቂ ጤፍ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ሳያልቅ እንግዛ እየተባባለ ነው። በወፍጮ ቤት ተቀጥሬ መስራት ከጀመርኩ አምስት ዓመት አልፎኛል። ነገር ግን የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት ቤተሰቤን ለማስተዳደር እንደዚህ የተቸገርኩበት ወቅት የለም ብለዋል። ስለዚህ ይህ ጉዳይ ሥር ሳይሰድ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች ችግሩን በአስቸኳይ እንዲፈቱት ጥሪ አቅርበዋል።

ኅብረተሰቡ ለዕለት ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በአቅራቢያው በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኝ ይገባል፤ እየታየ ያለው የገበያ ዋጋ ግን የሚቀመስ አልሆነም። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማኅበረሰብ የዋጋ ጭማሪውን መቋቋም አልቻለም ያለው ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ አብርሃም ዳኜ ነው።

የዋጋ ጭማሪ ለዕለት ተዕለት በሚውሉ ምርቶች ላይ መደረግ የለበትም። የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መሠረት ያደረገ አይደለም ሲልም ነው የሚገልጸው።

መንግሥት ለዕለት ተዕለት ፍጆታዎች የዋጋ ተመን አውጥቶ ሕግ የሚተላለፉ አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል ሲልም አሳስቧል።

በልደታ ክፍለ ከተማ የወፍጮ ቤት ባለቤት አቶ ሰለሞን ባይሳ (ስማቸው የተቀየረ) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የጤፍ አቅርቦት ችግር እና የዋጋ ጭማሪው ከኅብረተሰቡ ጋር ያለመተማመን ሁኔታ ውስጥ ከቶኛል። ወፍጮ ቤቴን ለአራት ቀን አልከፈትኩም። ለኅብረተሰቡ የምሸጠው ጤፍ ስለሌለ ኅብረተሰቡ ጤፍ የደበቅኩ እየመሰለው ነው።

ስለሆነም ከኅብረተሰቡ ጋር ላለመጋጨት ጥቂት ጤፍ ያላቸው ነጋዴዎችን ተለማምጬ ለኅብረተሰቡ ጤፍ አምጥቻለሁ። የኅብረተሰቡ አቅም እና የገበያው ሁኔታም የሚጣጣም አይደለም። ስለዚህ መንግሥት ጉዳዩን በትኩረት ሊያስብበት ይገባል ብለዋል።

የእህል በረንዳ ነጋዴ የሆኑት አቶ አማን ይሁን (ስማቸው የተቀየረ) በበኩላቸው፤ መንግሥት የንግድ ዘርፉን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት የሰጣቸውን አካላት በዘርፉ ምን እየሠሩ እንደሆነ መመርመር ያለበት ሲሆን በኬላዎች አካባቢ እየተሠራ ያለውን ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ከሥር ነቅሎ ማጥፋት አለበት ብለዋል።

ወቅቱ ከፍተኛ ምርት ያለበት እና ኢትዮጵያ ሰላም የሆነችበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት በተለየ ሁኔታ የእህል ዋጋ እንደ ሰማይ እየራቀ በመምጣቱ ዜጎችን ይበልጥ እያስጨነቀ ነው። ስለሆነም ይህንን ጉዳይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንዳለበትም አቶ አማን አሳስበዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ በላይነሽ ረጋሳ በበኩላቸው፤ አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደማይመለከተው እና ጉዳዩ ዘርፈ ብዙ ተዋንያን ያሉት ነው ብለዋል። ዋጋ ባልወጣበት ነገር ላይ ኃላፊነት መውሰድ እንደማይቻልም ገልጸዋል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አሁን ለተፈጠረው የጤፍ ዋጋ ኃላፊነት «ማንዴት» የለውም የንግድ ሥርዓቱን በተመለከተ አጥንተን በቀጣይ ምላሽ የምንሰጥበት ይሆናል ብለዋል።

የጤፍ ዋጋ ግብይት ሥርዓቱን በተመለከተ የአዲስአበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ምላሽ እንዲሰጠን ብንጠይቅም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ግብረኃይል መቋቋሙን በመግለጽ የደረሰበትን በቀጣይ እናሳውቃለን ከማለት ውጪ ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version