Site icon ETHIO12.COM

‹‹ግብጽ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የጎዳቻት ስለመሆኑ የሚገልጽ ምንም ዓይነት ማስረጃ የላትም››

ግብጽ ለአረብ ሊግ የግድቡን ጉዳይ ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን ማጸደቋን እርግጠኛ አይደለሁም። ይህንን ማረጋገጥ ያስፈልግ ይሆናል። በእኔ በኩል የማውቀው ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን መጠየቋን ነው:: እናም ስትጠይቅ የአረብ ሊግ አገሮች ውስጥ የኢትዮጵያም ጎረቤቶች አሉበት:: እነዚህ ጎረቤት አገሮች ደግሞ ኢትዮጵያን የሚጎዳ አጀንዳ ግብጽ አቅርባ ኢትዮጵያ እንድትጎዳ ከግብጽ ጥቅም አንጻር ለዘለቄታ የሚቆሙ አይመስለኝም::
ደግሞም የኢትዮጵያ ጎረቤት ያልሆኑ አረብ አገሮችም ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነትም ብሎም ሞቅ ያለ ግንኙነትም ያላቸው ናቸው። በተለይ በንግድም ሆነ በፖለቲካ ያላቸው ከፍ ያለ ግንኙነት እንደሆነም ይታወቃል:: ስለዚህ እነዚህም አገሮች ግብጽ የምትለውን በደረቁ ተቀብለው ለዘለቄታው አጀንዳው አጀንዳችን ነው ብለው ከያዙ የተሳሳቱ ይሆናሉ ማለት ነው::

ሲያስተምሩም ሆነ በፖለቲካ ሳይንሱ መስክ ሲመራመሩ (በተለይ በናይል ውሃ ጉዳይ) በታላቅ ደስታ ነው፡፡በታላቁ የዓባይ ግድብ ድርድርም ሆነ በዓለም አቀፍ ኮንፍራንሶች ላይ በአዘጋጅነትም ሆነ በተሳታፊነት ሲንቀሳቀሱ ተግባራቸውን የሚያከናውኑት፤ ኃላፊነታቸውን የሚወጡት በጥልቅ አገራዊ ፍቅርና በተነቃቃ ምሁራዊ ስሜት ነው፡፡

በርካታ ምሁራንን ያፈሩ መምህር እና የሀይድሮሊክ ፓወር ፍትሐዊ አጠቃቀም ፖለቲካ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተንታኝ በመሆናቸው በሚገባ የሚታወቁት እንግዳችን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፤ በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ጉዳይና በፖለቲካል ሳይንስ መስክ አሜሪካ ከሚገኘው ኦሐዩ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤች.ዲ) ደግሞ ስዊዘርላድ ከሚገኘው፣ ከታዋቂው ዙሪክ ዩኒቨርሲቲ በናይል ውሃ ጉዳይ፣ በፖለቲካል ሳይንስ መስክ ተቀብለዋል፡፡

እንግዳችን ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መስክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር፣ በመመራመርና በማማከር ሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡በተጨማሪም የፖለቲካ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር፣ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፤ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ ዳይሬክተር በመሆን የሰሩም ናቸው – የዛሬው የዘመን እንግዳችን መምህርና ተመራማሪ፤ እንዲሁም የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ፡፡

ዶክተር ያዕቆብ የአፍሪካ፣ የእሲያና የአውሮጳ ዩኒቨርሲቲዎች የውሃና ማህበረሰብ ምርምር አባልና የኢትዮጵያ አስተባባሪ፤ እንዲሁም የሰሜንና የደቡብ አህጉራዊ ምርምር የምሥራቅ አፍሪካ ዘርፍ አማካሪ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ሠርተዋል፡፡የኢትዮጵያ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን አባልም ናቸው፡፡እርሳቸው በኢትዮጵያ የጠፉ ወንዞችና የውሃ ሀብቶችን የመመለስ እንቅስቃሴ አስተባባሪም ናቸው፡፡በብዙ ደርዘን የሚቆጠሩ ሙያ ነክ የምርምርና የስርጸት ጽሑፎችንም ያበረከቱ ሲሆን፣ በአፍሪካ፣ እሲያ፣ አውሮጳ እና በአሜሪካ ተዘዋውረው ትምህርታዊ ሌክቸሮችን ሰጥተዋል፡፡

የድንበር ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ወንዞች የድርድር ጉዳይን በተመለከተ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ ናቸው፡፡የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፓናል አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት፤ የሕዳሴ ግድቡ ብሔራዊ የድርድር ቡድን አባል፤ እንዲሁም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ዶክተር ያዕቆብ ሰፋ ያለ ሥራና ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣታቸውን ተከትሎ ከውጭና ከአገር ውስጥ በርከት ያሉ ሽልማቶችን ማግኘት የቻሉም ናቸው፡፡

ካገኟቸው በርካታ ሽልማቶቻቸው መካከል አንዱ የ2012 ዓ.ም የዓመቱ በጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ መሆናቸው ተጠቃሽ ነው፡፡እኚህ የዛሬው እንግዳችን በዓባይ ግድብ ላይ በድርድሩም ሆነ አስፈላጊ በሆነው ተሳትፏቸው ከፍ ያለ ሚና የተጫወቱ ሲሆኑ፣ እኛ የዓባይ ግድብን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ስላላቸው ከዶክተር ያዕቆብ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ ብለናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግድቡ ዙሪያ የተጣለብዎትን ኃላፊነት እየተወጡ እንደሆነ ይታወቃል፤ ከግድቡ ጋር ተያይዞ ያዘኑበት አልያም የተደሰቱበት አጋጣሚ ካለ እሱን በማስቀደም ወደ ጭውውታችን እናምራ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- እኔ በዚህ ግድብ በአጠቃላይ ደስተኛ ነኝ:: ምክንያቱም በኢትዮጵያ ከ1958 አ.ም ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመሥራት ጥናቶች ተካሂደው አመቺ ጊዜ እየተጠበቀ ነበር የቆየው:: የተወሰኑ አነስተኛ ሥራዎች እየተሠሩ ቢቆዩም የተፈለገውን ያህል ባለመሆኑ ቅር ያሰኛል:: የሕዳሴ ግድብ የዛሬ 12 ዓመት ሲጀመር ግን እጅግ የሚያስደስት ሆኖ አግኝቼዋለሁ:: ይህም አገርን የሚያስከብር፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከፍ የሚያደርግ፣ ኢትዮጵያ ባላት ሀብት የመጠቀም ችሎታ እንዳላት የሚያመላክት በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል::

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ የውጭ ብድር ሳታገኝና ሳትፈልግ፤ በእሱም ሳትገደብ ኅብረተሰቡን ዳር እስከዳር አስተባብራ፤ ከመንግሥትም በጀት ተጠቅማ ይህንን ትልቅ ግድብ በብዙ ተግዳሮትም ውስጥ ሆና ቢሆንም ዛሬ ላይ መድረስ ችላለች:: በየመሃሉ የተነሱ ማደነቃቀፊያዎች ቢኖሩም እዚህ ደረጃ መድረሱ እና ለማጠናቀቅም ጥቂት ጊዜ የቀረው በመሆኑ በጣም የሚያስደስት ነው::

ይህ ግድብ ተሠርቶ ሲያልቅ በዓባይም ሆነ በሌሎች ወንዞች ላይ በዚሁ መጠንም ይሁን ከዚህም ከፍ ባለ ደረጃ እንደሚሠሩ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ለኅብረተሰባችን ሲናገሩ ቆይተዋል:: ከሁሉም በላይ የዚህ ግድብ አጀማመር እና አካሄድ እንዲሁም የዚህ ግድብ አጨራረስ ሁሉንም ችግር ተቋቁሞ እዚህ መድረስ ቁርጠኛነትንና አገራዊ የሆነ ታላቅ ፍላጎት እና ችሎታን የሚያሳይ ይመስለኛል:: ይህ በጣም ያስደስተኛል:: ደግሞም ተገቢ ነገር ነው። እንደማንኛውም የአጭር ጊዜ ሥራ በአንድ ዓመት በሁለት ዓመት ተሠርቶ የሚያልቅ ነገር ስላልሆነ ረጅም ጊዜና ሰፊ ትዕግስት፤ ብልሃትም የሚፈልግ ሥራ ስለሆነ ይህን ሁሉ ለመሥራት ኢትዮጵያ ያገኘችው ችሎታና ብልሃት ትልቅ ነው:: ከዚህም የተነሳ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ተግባር ነው::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በተፈለገው ደረጃ እንዳልተጠቀመች ይነገራል፤ ይህን እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ያዕቆብ፡– ኢትዮጵያ ለውሃ አጠቃቀሟ ልዩ ትኩረት ልትሰጥ ይገባታል ብዬ አስባለሁ:: የውሃ አጠቃቀም በእጅጉ መሻሻል ይኖርበታል:: ከሁሉም በላይ እየደረቁ ያሉ የውሃ ምንጮች እንደገና እንዲጎለብቱ ማድረግም ይጠበቅብናል:: እየደረቁ ያሉ ገባር ጅረቶችና አነስተኛ ወንዞች እንደገና ሕይወት መዝራትም ይኖርባቸዋል::

እንደ ሳንባ የሚያገለግሉ ጨፌዎችና የውሃ ማቆሪያዎች እየደረቁ በመሆናቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው የግድ ይላል:: በወንዞቻችን ላይ ትንንሽ (ካስኬድ) ግድቦች እየተገነቡ ለእርሻ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ለዓሣ ሀብት ልማት እና ለጠቅላላው ሥነ ምህዳር መንከባከቢያ መዋል ይኖርባቸዋል:: በኢትዮጵያ ያለው የውሃ ችግር ከውሃ አስተዳደር ድክመትና ከመሬት አጠቃቀም ጉድለት የሚመነጭ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል:: የገጠር መሬት ልማትም ሆነ የከተሞች ግንባታ ተገቢና ዘላቂ የውሃ አጠቃቀምን መሠረት ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል::

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም ከመገዳደሯ ጎን ለጎን ፈተናው ዓለምአቀፍ ይዘት እንዲኖረው እየጣረች ነው፤ ይህ በአገራቱ መካከል በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሀዊ አሠራር እንዳይሰፍን አያደርግም?

ዶክተር ያዕቆብ፡– እንደሚታወቀው ግብጾች ከኢትዮጵያ ጋር የውሃ ሀብት ይጋራሉ። በተለይ ዓባይ፣ ተከዜ እንዲሁም ባሮ አኮቦ ሱዳንን ተሻግረው ከኢትዮጵያ ወደ ናይል ግብጽ ስለሚሄዱ በተፈጥሮ እኛና ግብጽ የምንጋራው የውሃ ሀብት ነው:: ይህን የውሃ ሀብት በተቻለ መጠን በመተሳሰብና በመመካከር መጠቀሙ መልካም ነው:: በተለይም በውሃው ላይ የትኛው አገር ምን ቢሠራ ይሻላል በሚል እቅድ በማውጣት ተጠቃሚ መሆን ይገባል:: «ከውሃ የሚገኝ የኢኮኖሚ ሥርዓት ምን ቢሆን ይሻላል?» በሚል ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሱዳንም ሆነች ግብጽ፤ እንዲሁም ሌሎችም በውሃ አጠቃቀም የሚጋሩ አገሮች እቅድ እያወጡና እየተሳሰቡ በአንድ መጓዝን የግድ የሚል ነው:: ለምሳሌ ብዙ በውሃ የሚለማ ልማት እንዳለ ይታወቃል::

ለአብነት ያህል አንደኛው አገር ከፍተኛ የእርሻ ልማት ላይ የሚሰማራ ከሆነ ሌላኛው ደግሞ ከፍተኛ የኃይል ምንጭ ላይ ሊሠራ ይችላል:: ስለሆነም በዚህ መልኩ በምክክር መሄድ ይገባል:: ነገር ግን ኢትዮጵያ ሀብቷን በምታለማበት ጊዜ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ልማት ግብጽን የሚጎዳ እየመሰላት ወይም ደግሞ የሚጎዳት እንደሆነ እያስመሰለች ግብጽ ብዙ ለማሳመን ርቀት ለመሄድ ሞክራለች:: ይሁንና ኢትዮጵያ በውሃዋ ለማልማት በተነሳች ጊዜ ግብጽ የኢትዮጵያ ልማትና የውሃ አጠቃቀም እየጎዳኝ ነው ትበል እንጂ በዚህ በዚህ መንገድ፣ ወይም ደግሞ በዚህ ሁኔታ የእኔ ልማት ተደናቀፈ የሚል ማስረጃ እስካሁን ማቅረብ አልተቻላትም::

ምንም እንኳ ግብጽ ማቅረብ ባትችልም ‹‹ኢትዮጵያ ትጎዳናለች›› የሚለውን ተደጋጋሚ ሐሳብ ለሕዝቧ እንደ መሠረታዊ የፖለቲካ ትምህርት እያደረገች በፕሮፖጋንዳ ደረጃ በመግለጽ ዛሬ ላይ ደርሳለች:: ለወዳጆቿም ‹‹ኢትዮጵያ ውሃዬን እየወሰደችብኝ ነው፤ ከአሁን ቀደም በአግባቡ እጠቀምበት የነበረውን ውሃ እንዳልጠቀም ኢትዮጵያ እያጠፋችብኝ ነው›› በማለት ከመናገር ቦዝና አታውቅም:: ይህንን ሐሳቧን ኢትዮጵያ በሌለችበትና ባለችበትም ጭምር ከመናገር ወደ ኋላ የቀረችበት ጊዜ የለም::

ግብጽ በየመድረኩ ‹‹ኢትዮጵያ ውሃዬን እንዳልጠቀምበት እያደረገች ነው›› ትበል እንጂ ግብጽ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የጎዳቻት ስለመሆኑ የሚገልጽ ምንም ዓይነት ማስረጃ የላትም:: «ግብጽ ለምን ሰጋች?» ብሎ መናገር አይቻልም። ስጋቷ ግን መሠረት እንደሌለው መናገር ይቻላል:: ስለዚህ የግብጽ ወዳጆችም ሆኑ የግብጽ ሕዝብ ‹‹ኢትዮጵያ ውሃውን በመጠቀሟ ግብጽ ተጎዳች›› የሚሉት የተሳሳተ መረጃ ስለሚደርሳቸው እና በተሳሳተ መንገድ የግብጽን ሐሳብ በመቀበላቸው ነው እንጂ ሐሳቡ ትክክል ሆኖ አይደለም:: በእርግጥ ግብጽና ኢትዮጵያ በአግባቡ ውሃውን ተሳስበው ወደ መጠቀም ብልሃት ቢመጡ መልካም ነው፤ ይህ ብልህነትም ጭምር ነው:: ምክንያቱም ከውሃው ለሁለቱም የሚበቃ ልማት ማግኘት ይችላሉ:: ከውሃ የሚገኝ ጥቅም፣ ሀብት፣ ምቾትም ሆነ ብልጽግናም ጭምር ይገኛል ብዬ አስባለሁ::

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ግብጽ የዓባይ ግድብ ጉዳይ በአረብ ሊግ ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን አስደርጋለች፤ ይህ አካሄድ አረቦቹን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት አያስመስልባቸውም? የግብጽንስ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ግብጽ ለአረብ ሊግ የግድቡን ጉዳይ ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን ማጸደቋን እርግጠኛ አይደለሁም። ይህንን ማረጋገጥ ያስፈልግ ይሆናል። በእኔ በኩል የማውቀው ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን መጠየቋን ነው:: እናም ስትጠይቅ የአረብ ሊግ አገሮች ውስጥ የኢትዮጵያም ጎረቤቶች አሉበት:: እነዚህ ጎረቤት አገሮች ደግሞ ኢትዮጵያን የሚጎዳ አጀንዳ ግብጽ አቅርባ ኢትዮጵያ እንድትጎዳ ከግብጽ ጥቅም አንጻር ለዘለቄታ የሚቆሙ አይመስለኝም::

ደግሞም የኢትዮጵያ ጎረቤት ያልሆኑ አረብ አገሮችም ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነትም ብሎም ሞቅ ያለ ግንኙነትም ያላቸው ናቸው። በተለይ በንግድም ሆነ በፖለቲካ ያላቸው ከፍ ያለ ግንኙነት እንደሆነም ይታወቃል:: ስለዚህ እነዚህም አገሮች ግብጽ የምትለውን በደረቁ ተቀብለው ለዘለቄታው አጀንዳው አጀንዳችን ነው ብለው ከያዙ የተሳሳቱ ይሆናሉ ማለት ነው::

ሌሎች ለግብጽ እጅግ በጣም ይቅርባሉ የሚባሉት አረብ አገሮች እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ትልቅ አገር፣ ያውም ለአካባቢው ብዙ ጥቅም የምትሰጥ፣ በኢኮኖሚም በፖለቲካም ልትከበር የሚገባት ሆና ሳለ የመከባበርን መስመር ሊያበላሽ የሚችልን መንገድ በዘለቄታ ተከትለው ከግብጽ ጋር የሚያብሩ አይመስለኝም:: በእርግጥ ግብጾች አባል በሆኑበት በአረብ ሊግ በእነሱ ከተማ ተቋቁመው በብዛት በግብጽ ፖለቲከኞች የሚስተናገድና የሚመራ የአረብ ሊግን ቀርቶ በአውሮፓና በአሜሪካም እየዞሩ አገራቱ የግብጽን ፖሊሲና ፕሮፓጋንዳ ተከትለው ኢትዮጵያ ላይ ዱላ እንዲያነሱ ሁሉ ግብጽ ስታግባባ እንደቆየች የታወቀ ነው::

እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ልማት ጉዳይ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ለመጥቀም፣ የኢትዮጵያን ልማት ከፍ ለማድረግ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ መብትና ጥቅም ለማስከበር ነው። ስለሆነም ግብጾች በአረብ ሊግም ሆነ በሌላ ቦታ በኢትዮጵያ ላይ የሚያጠነጥኑት አሉታዊ የሆነ ፕሮፖጋንዳም ሆነ የማሳሳት ዘመቻ መሠረት አይኖረውም። ኢትዮጵያ፣ ግብጽን ለመጉዳት አስባ ሳይሆን ልማቷን በቁርጠኝነት ለማሳለጥ በጥንቃቄ በመሥራት ላይ ትገኛለች:: እንዲሁም ምንም እንኳ ሦስተኛ ወገን ከግብጽ ጋር ቢያብርም የጋራ ውሃ እንደመሆኑ መጠን ግብጽም በከፋ ሁኔታ እንዳትጎዳ ጥንቃቄ በመውሰድ ኢትዮጵያ ውሃውን መጠቀም ትችላለች:: ይህንን መብቷን ደግሞ ሊከለክላት የሚችል ኃይል አይኖርም::

ኢትዮጵያ በግብጽ ላይ የኢኮኖሚም የማህበራዊም ጉዳት አምጥታለች ወይም ደግሞ ኑሮዋ እንዲስተጓጎል አድርጋለች የሚባል መረጃ እስከሌለ ድረስ በውሃ ሀብቷ መጠቀም አጠያያቂ አይሆንም። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያበላሽ አይመስለኝም:: ለጊዜው ፕሮፓጋንዳው የሚያሳስት እንኳ ቢሆንም አገሮች በራሳቸው ነፃ በሆነ መንገድ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ያስገባሉ የሚል አተያይ አለኝ:: እነሱም ቢሆኑ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ከኢትዮጵያ ጋር ጠላትነት የሚፈልጉ አይመስለኝም:: ስለዚህም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት የሚያበላሽና ዘለቄታ ያለውን ስህተት ግብጽ ልትሠራ የምትችል አይመስለኝም::

አዲስ ዘመን፡- ይህ የግብጽ አካሄድ፣ በተለይ ቀደም ብሎ የተቀመጠውን ‹‹ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ›› የሚለውን መርህ የሚጻረር ነው። በመሆኑም ግብጽ በኅብረቱ ያለመተማመኗ ምክንያት ምን ይሆን?

ዶክተር ያዕቆብ፡- እንደሚታወቀው ግብጽ ምንም እንኳ በመልክዓምድራዊ አቀማመጧ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም በባህልም ሆነ በኢኮኖሚ እንዲሁም በታሪክም ሆነ በፖለቲካ ተያያዥነቷ በአብዛኛው ወደ አረቡ አተኩራ የምትሠራ አገር ናት። በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ አገሮች ግብጽ ላይ የሚያመጡት ተጽዕኖ ከባድ ነው ብላም ስለማታስብ ልክ እንደማናቸውም የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ አገራት ሁሉ አፍሪካውያን መፍትሔ ማምጣት አይችሉም የሚል አተያይ ስላላት ይሆናል:: በተለይ የአፍሪካ የፖለቲካ መሪዎች የአፍሪካን ችግር መፍታት የሚያስችል ቁመና ያላቸው ናቸው ብላ ስለማታምንም ጭምር ነው:: ስለዚህ አፍሪካዊት አገር እንደመሆኗ የውሃ ሀብቷ ከአፍሪካ ውሃ አመንጪ አገሮች ጋር የሚያያይዛት መሆኑን እንኳ ብትረዳ ተጽዕኖ ለመፍጠር ከአፍሪካ ውጪ ካሉ ኃይሎችና አገሮች ጋር በአፍሪካ ላይ ለመሥራት እንደዋና አማራጭ አድርጋ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች::

በዚህ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በግብጽ በኩል ብዙ ተቃውሞ ተነስቶ በኢትዮጵያ በኩል ብዙ ማብራሪያዎች የተሰጡበት ከመሆኑም በተጨማሪ ብዙ ሰነዶችም እየቀረቡ ውይይትም እየተደረገባቸው ነው። ይህ ባለበትም ጊዜ ከዓለም መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እና ከአፍሪካ ውጪ ካለው ሒደት ኢትዮጵያ ሐሳብ አቅርባ የአፍሪካ ጉዳይ መፈታት ያለበት በአፍሪካ ነው ብላ ወደ አፍሪካ ማምጣት ችላለች:: ይሁንና ኢትዮጵያ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ መድረክ ካመጣችው ወዲህ ግብጽ በአፍሪካ መድረክ ላለመገኘት እግሯን እየጎተተች ቆይታለች:: በመሆኑም ከኢትዮጵያ ጋር አግባብነት ያለው ውይይት አሊያም ረብ ያለው ንግግር አድርጋ ‹‹ችግሬ ይህ ነው፤ መፍትሔውም ይህ ነው›› ብላ ልታቀርብ አልቻለችም።

ስለዚህ የአፍሪካ መድረክ ለግብጽ የሚመች አይደለም። ምክንያቱም ግብጽ የምትፈልገው ሌሎች ዜሮ እርሷ ደግሞ ሙሉውን ማግኘት ነው:: ስለዚህ የአፍሪካ መድረክ ለግብጽ አመቺ አይሆንም። ምክንያቱም የአፍሪካ አገሮች ትክከለኛውን ነገር አመዛዝነው የኢትዮጵያ መብትና ጥቅም እንዲታይ፣ ግብጽም በከፋ መንገድ ያልተጎዳች ስለመሆኗ አመዛዛኝ የሆነ ነገር መመልከታቸው አይቀርም ብላ ታስባለች:: ደግሞም በአፍሪካ መድረክ የሕዳሴ ግድብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከግብጽ በኩል የረባ ማስረጃ በማቅረብ የተጎዳችበትን ማሳየት ስላልቻለች እሷ የምትፈልገው ውሳኔና ድጋፍ ከአፍሪካ መድረክ እንደማይገኝም አውቃለች:: ስለዚህ አጽንዖት ሰጥታ አረብ አገራት ወዳጆቼም ዘመዶቼም ናቸው በማለት ከእነርሱ ጋር ለመስራት ትፈልጋለች::

አዲስ ዘመን፡- በአገራቱ መካከል በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያለውን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የተሻለው አማራጭ ምንድን ነው ይላሉ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ውሃ የሚጋሩ አገሮች ውሃውን በየአገሩ አግባብነት ባለው መንገድ መጠቀሙ መልካም ነው:: የአገሩ፣ የመሬቱና ውሃውን ለማልማት ያለው አመቺ መልክአምድራዊ አቀማመጥ ከግምት ውስጥ ገብቶ ቢሠራበት የተሻለ ይሆናል:: የአየር ሁኔታውም በሚያመች መንገድ ስትራቴጂክ የሆነ እቅድ አውጥተውና ሥራ ተከፋፍለው ቢሠሩ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው:: ለምሳሌ አንዱ አገር በውሃ ልማት ላይ ቢያተኩር፤ ሌላው አገር ደግሞ በኃይል ማመንጨቱ ቢሠራ ጥሩ ነው። እያንዳንዱ አገር በውሃ ልማት የሚገኝ ጥቅም በተለያየ አመቺ በሆነ መንገድ፤ አገሮች በገበያ መርም ሆነ በሌላ በኩል ሊዳረሳቸው በሚችል አካሄድ ለመጠቀም ቢያቅዱ ጠቀሜታ ያለው ነገር ነው::

ኢትዮጵያ የመብራት ኃይል ለማመንጨት የመሬት አቀማመጧና የውሃ ፍሰቷ በጣም አመቺ ስለሆነ የሕዳሴ ግድብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ግድቦች መሥራት ትችላለች:: ከዚህ ቀደም በዋቤ ሸበሌም ላይ እንዲሁም በዓባይ ላይ በርካታ ልማቶች ተሠርተዋል:: በኦሞም፣ በግቤ ላይም እየተሠራ ነው ያለው:: በዓባይ ገባርና በተከዜም ላይ እንዲሁ እየተሠራ ይገኛል:: ይህ ሁሉ የመብራት ኃይል የመሬቱ ሁኔታ አመቺ ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ስለመሬቱ ሁኔታም ስለ ውሃ ፍሰቱም ብዙ አዋቂዎች የደረሱበት ጉዳይ ነው:: እናም አሁን በጀመረችበት እውቀትና ልምድ የበለጠ ብታመርት ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ታዳሽ ኃይል እና በተሻለ ዋጋ የሚገኝ ኃይል ከማግኘቷ በተጨማሪ ለግብጽም፣ ለሱዳንም ሊዳረስ ይችላል::

ሱዳን ውስጥ ደግሞ ሰፊ የእርሻ ቦታ አለ። እነዚህ ቦታዎች ደግሞ ውሃ አጠር ናቸው:: የሚያመርቱት ሰብልና ከእርሻ ጋር የተገናኙ ብዙ ነገሮች በገበያ መርህ ለኢትዮጵያም ለግብጽም ሊዳረስ ይችላል:: ስለዚህ የትኛው የውሃ አጠቃቀም የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል፤ በምን ዓይነት አደረጃጀት ቢሆን የተሻለ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል የሚለው የመተሳሰብ መንገድ መሆን የሚችል ነው:: ስለዚህ የሥራ ክፍፍል (ዲቪዥን ኦፍ ሌበር) የሚባለው ወይም ደግሞ እያንዳንዱ አገር የሚሠራውን የውሃ ልማት አንጻራዊ ጥቅማቸውን (ኮምፓራቲቭ አድቫንቴጅ) ጠብቀው ከሠሩ አንዱ አገር የሌላው አገር የውሃ ልማት ደጋፊ ነው እንጂ ተጻራሪ አይሆንም::

ከእያንዳንዱ አገር የሚገኝ የውሃ ልማት ፋይዳ ለሌሎች አገሮችም ሊዳረስ የሚችልበትን መንገድ አብሮ ማቀድ እና አብሮ መተሳሰብ፤ ይህንንም የበለጠ ከፍ ለማድረግ በተቻለ መጠን ስትራቴጂ ተዘርግቶ ለዚህም የሚሆን እውቀት፣ ስልጠና በቅርብ እየተመካከሩ ልማቱን ሊያሳልጡ ይችላሉ። በመሆኑም ዘለቄታ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው በዚህ ዓይነት አግባብ ሲሠራ ነው አገሮች በውሃ ሀብቱ አብረው ሊጠቀሙ የሚችሉት። ግጭት በሌለበት መንገድ እየተስማሙ እየተመካከሩ የሚጠቀሙት በዚህ ነው::

በጋራ ውሃ የጋራ አስተዳደርም ያስፈልጋል። በጋራ የሚያስተሳስር የሕግ መሠረትም ያስፈልገዋል:: እነዚህ ደግሞ በስምምነት የሚደረጉ እንጂ አንዱ አገር ‹‹ይኸውላችሁ! ሕግ ሠርቻለሁ፤ እናንተንም ይገዛል›› ሊል አይችልም:: ወይም ደግሞ ‹‹ይኸውላችሁ! ውሃ የሚተዳደርበትን ተቋም አበጅቻለሁ፤ ለእናንተም ጥሩ ነው›› ሊል አይችልም:: አሊያም ደግሞ ‹‹በውሃ እውቀት እኔ እስካሁን ሠርቼበታለሁ፤ እናንተ በዚህ ሥሩበት›› ብሎ ሊያዝ አይችልም:: እነዚህ ነገሮች ሁሉ በመመካከርና በመተሳሰብ እውቀትንና ፍላጎትን በማቀናጀት የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው:: በመሆኑም አገሮች ለወደፊት ተፈጥሮ በአንድ ላይ በውሃ አማካይነት ያስተሳሰራቸው እንደመሆናቸው መጠን ልማታቸውም መሆን ያለበት በትብብር ነው:: አገሮች ሌላውን አገር በመግፋት ለራሳቸው ብቻ በሚጠቅም መንገድ መጓዝ አይችሉም። የሚያስኬደው ይህ ዓይነት ሁኔታ ሳይሆን በአንድ ላይ በትብብር የሚሠሩበትን መድረክ በማመቻቸት ነው::

አዲስ ዘመን፡- 12ኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የዓባይ ግድብ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። በእስካሁኑ ሒደት ያጋጠመው ተግዳሮት ሰፊ እንደሆነም ይነገራል። በእርስዎ አተያይ በጣም ከባድ ተግዳሮት ነበር የሚሉት የትኛውን ነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡– እኔ እንደተከታተልኩት ከሆነ በታቀደበት መሠረት ሊሠራ እንዳይችል በመካከል አደናቃፊ የሆኑ ሁኔታዎች ተፈጥረውበት ነበር:: ስለዚህ ተስተጓጉሎ በመቆየቱ በጊዜም ሆነ በሀብት፤ እንዲሁም ደግሞ ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ ባመጣው በሞራልም የሚጎዳ ነገር ነው ያጋጠመው:: ይህ ትልቅ ችግር ይመስለኛል:: ነገር ግን ያ በመሃል የመጣ ተግዳሮት በኋላ ላይ ተደርሶበት በተለይ በለውጡ አስተዳደር አማካይነት ማስተካከያ ተደርጎበት እንደገና ማንሰራራት መቻሉ የሚዘነጋ አይደለም:: በአዲስ ጉልበት በቴክኒክ የነበሩ ችግሮች ተስተካክለው በገንዘብም የነበረው ክፍተት ከግምት ገብቶ እንደገና በተጨማሪ ወጪና በጀት የኅብረተሰብም እርዳታ ታክሎበት በአሁኑ ሰዓት ጥሩ መስመር ለመያዝ በቅቷል። ወደ ማጠናቀቂያውም እየተቃረበ መሄዱ የሚያስደስት ነው::

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ ‘በዓባይ ግድብ ዙሪያ ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው የማለቷ አካሄድ እንደማስፈራሪያ የሚቆጠር ነው’ የሚሉ አሉ፤ የግብጽ አካሄድ ይህ ከሆነ ደግሞ ሦስቱም የተፈራረሙትን የመርሆዎች ስምምነት፣ እንዲሁም የአፍሪካን ህብረት ድንጋጌ የሚጥስ አይሆንም?

ዶክተር ያዕቆብ፡- በየጊዜውና በየዘመኑ ግብጽን ለማስተዳደር የሚመጡ መሪዎች የኖሩት ውሃ አመንጪ አገሮችን፣ በተለይ ኢትዮጵያን ‹‹ውሃውን ከነካሽ ወየውልሽ›› ሲሉ ነው:: ኢትዮጵያ ትልቅ ግድብ እየገደበች እነሱ ደግሞ ግድቡን የሚያስቆሙ እየመሰላቸው እዚህ መድረስ ተችሏል:: ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ግድብ የሚጠቅመኝ ስለሆነና ልማቴን ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ በገዛ ግዛቴ ውስጥ ብሎም በገዛ ገንዘቤ የምሥራው ግድብ ስለሆነ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነኝ እያለች ነው:: በተለይ ማንንም በከፋ ሁኔታ ሳልጎዳ እያካሄድኩ ያለሁት ግድብ ስለሆነ ግብጽም ሆነች ሌሎቻችሁ ይህንን ካልተረዳችሁ እንድትረዱ እጠይቃለሁ በማለት ላይ ናት። ከተረዳችሁ ደግሞ የማይሆን ጨዋታ ውስጥ አትግቡ ስትልና ስትመክርም ቆይታለች::

ስለዚህ ግብጾች አሁን ብቻ ሳይሆን ሁሉም አማራጭ ጠረጴዛ ላይ ነው ያለው በማለት ቆይተዋል:: እንዲሁም ሁሉም አማራጭ በእጃችን ነው ያለው፤ ሁሉንም አማራጭ ከመጠቀም ወደ ኋላ አንልም ሲሉ ሰንብተዋል። ባለፉት 12 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር በተቻለ መጠን ለመወያየት ተሞክሮ ስምምነት ባይኖርም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የቆየችው እየተነጋገረች ነበር:: በእርግጥ ሱዳን አንዴ ኢትዮጵያ ዘንድ አንዴ ደግሞ ግብጽ ዘንድ ወዲህ ወዲያ እያለች ብትቆይም ኢትዮጵያ ግን እየተወያየች እዚህ ደርሳለች::

ግብጽ ኢትዮጵያ ሌሎች ግድቦችንም በዓባይ ላይ እንዳትሠራ፤ የሠራችም እንደሆነ ግብጽን እያስፈቀደች እንዲሆን ነው ምኞቷ:: ይህንን ምኞቷን በጉልበት ለመጫን ብዙ ፍላጎት አላት:: የቅርብ ጊዜ አባባሏ ትርጉሙ በሌላ አገር ላይ «ሁሉም አማራጭ አለ» ሲባል ጦር ማዝመትንም ይጨምራል እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ እስካሁን ሊደረግ አልተቻለም:: ቢደረግም አይቻልም:: አይገባምም:: ሐሳቡም ጭምር የተሳሳተ ነው:: ስለዚህም ልማዳዊ አባባል ነው የሆነባቸው:: እንኳን ይህንን ግብጾች መረር ያለ ቀልድ ሲያምራቸው ሁሉም አማራጭ በእጃችን ነው ይላሉ:: ነገር ግን ሁሉም አማራጭ በእጃቸው እንደሌለ የታወቀ ነው፤ ለወደፊትም አይኖራቸውም ብዬ አስባለሁ::

የጋራ ውሃ ላይ የምታደርጉት ልማት ይጎዳናል ካሉ ጉዳቱ የሚደርስ መሆኑ ከተረጋገጠ ያንን ጉዳታቸውን ማሳየትና ለእሱ መፍትሔ በሚሆን ነገር ላይ መነጋገር ያሻል:: ስለዚህ እንዲያ ማለቱ ኢትዮጵያን የሚያሸማቅቃት አይደለም:: ግብጾች፣ የሕዝባቸውን ጥቅም ለማስከበር ኢትዮጵያ ውሃ ላይ የምትሠራውን ፕሮጀክት ተቃውመዋል፤ አሁንም እየተቃወሙ ነው:: ሲፈልጉም የግብጽን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ሁሉንም አማራጭ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ይናገራሉ:: ይህ ለሕዝባቸው የሚያቀርቡት ፕሮፓጋንዳ ይመስለኛል። የሚፈጽሙትና ሊፈጽሙት የሚገባ ነገር አይመስለኝም::

የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ መመሪያው አገሮች ጉዳያቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከሌሎች አገሮች ጋር በመመካከር እና አስፈላጊም ሲሆን በመደራደር መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ እንጂ አንዱ ሌላውን በማስፈራራት እንዲሆን የሚል መንፈስ የለውም:: ሌላው ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን እኤአ በ2015 ካርቱም ላይ የፈረሙት የመርህ ፊርማ ነው:: ይህ የመርህ ፊርማ አንደኛ ኢትዮጵያ ግድቧን እንዳትገነባ የሚከለክል ምንም ዓይነት ሕግ ፊርማው ውስጥ የለም:: ሁለተኛ ኢትዮጵያ ግድቧን ግንባታውን እያካሄደች መሙላት ትችላለች የሚል በመርህ ስምምነቱ ውስጥ አለ:: ሌላው በመካከላቸው ለምሳሌ ግብጾች ተጎዳንበት የሚሉት ነገር ካለ በጉዳዩ ዙሪያ በመመካከር እና በመስማማት ይጨርሱት እንጂ ከዚያ ውጪ በሆነ መንገድ አገሮች እርምጃ እንዲወስዱና አንዱ ሌላውን እንዲያስፈራራ የሚያመላክት ምንም ነገር የለም::

ስለዚህ፣ ግብጾች አሁን የሚያደርጉት ማስጠንቀቂያ እና ዛቻ ያንን መርህ ጭራሽ ወደ ጎን የተወና የአፍሪካ ኅብረትም አገሮች በሰላማዊ መንገድ ጉዳያቸውን ከሌሎች አገሮች ጋር በመከባበር ይፈጸማሉ የሚለውንም ወደ ጎን የገፋ ነው:: በመሆኑም፣ በማስፈራራት የሚፈጽሙት ነገር የለም የሚል መርህ አለ:: ግብጽ ግን ከዚህ ሁሉ መርህ ውጪ ናት ብሎ ማሰብ ይቻላል:: ግብጽ በቅርቡ ያሰማችው ዛቻ ሕገ ወጥም ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ያልተከተለ ብሎም ወዳጅነትን የማያከብር እንዲሁም ጉርብትናንም ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ የተሳሳተ ይመስለኛል::

 አስቴር ኤልያስ አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015

Exit mobile version