Site icon ETHIO12.COM

ዶናልድ ትራምፕ በቁጥጥር ሥር ውለው በቀረበባቸው ሰላሳ አራት ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ

ትራምፕ ይህ ክስ የተመሰረተባቸው በ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ለመሆን እየተሰናዱ ባሉበት ወቅት ነው።

ትራምፕ የቀረቡባቸው ከንግድ ማጭበርበር ጋር የተያያዙት 34 ክሶች ከ2016ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት የወሲብ ፊልም ተዋናይዋን ዝም ለማሰኘት በጠበቃቸው በኩል ከከፈሉት 130 ሺህ ዶላር ጋር የተያያዙ ናቸው።

ትራምፕ ለስቶርሚ ዳንኤልስ የከፈሉት ገንዘብ ምርጫው ከመካሄዱ 12 ቀናት በፊት መሆኑ ተገልጿል።

ከፍርድ ቤት ውሎ በኋላ ትራምፕ ወደ መኖሪያ ግዛታቸው ፍሎሪዳ ያቀኑ ሲሆን በመዳረሻቸውም ተሰብስብው ሲጠብቋቸው ለነበሩት ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር የቀረቡባቸውን ክሶች አጥብቀው አጣጥለዋል።

የቀረቡት ክሶች ምንድናቸው ?

ስቶርሚ ዳንኤልስ ከትራምፕ ጋር እአአ 2006 ላይ የወሲብ ግንኙነት መፈጸሟን ትገልጻለች፣ ትራምፕ ግን ይህ እውነት አይደለም ይላሉ።

ትራምፕ ያሸነፉበት የ2016 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመካሄዱ ከቀናት በፊት ዳንኤልስ ስለ ግንኙነታቸው ምንም እንዳትል በጠበቃቸው ማይክል ኮሀን አማካይነት ከትራምፕ 130ሺህ ዶላር መቀበሏን ዳንኤልስ ተናገራለች።

በግለሰቦች መካከል ወይም በግለሰብ እና በድርጅት መካከል ግንኙነት ከተቋረጠ በኋላ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዳይሰጥ ከፍያ መፈጸም ወንጀል አይደለም።

ይሁን እንጂ ትራምፕ ችግር ውስጥ የገቡት ጠበቃ ኮሀን ለስቶርሚ ዳንኤልስ የከፈሉትን ገንዘብ ትራምፕ ለመተካት ለጠበቃው ገንዘብ ሲከፍሉ ገንዘቡ ወጪ የተደረገው ለሕጋዊ ጉዳዮች ብለው ማስመዝገባቸው ነው።

ትራምፕ ላይ ክስ የመሰረተው ዐቃቤ ሕግ ከምርጫው በፊት ትራምፕ ስማቸውን ሊያጠፋ የሚችል መረጃን ከአሜሪካውያን ድምጽ ሰጪዎች ለመደበቅ ሕጋዊ ያልሆነ ተግባር ፈጽመዋል ብሏል።

ትራምፕ ምን አሉ?

ከፍርድ ቤት ውሎ በኋላ ወደ ፍሎሪዳ ከተመለሱ በኋላ የቀረቡባቸው የንግድ ማጭበርበር ክሶች “ለአገራችን ስድብ ናቸው” ብለዋል።

ትራምፕ ክሱ የቀረበባቸው ፖለቲካዊ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ነው ከማለታቸው በተጨማሪ ዐቃቤ ሕጉ ገለልተኛ አይደሉም ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ በተከሰሱት ጥፋተኛ ቢባሉ ሊታሰሩ ይችላሉ?

የዚህ የፍርድ ሂደት መጨረሻ ትራምፕ ጥፋተኛ ተብለው የገንዘብ ቅጣት ሊጣልባቸው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። ይሁን እንጂ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የእስር ቅጣትም ሊተላለፍባቸው ይችላል።

በአሜሪካ ሕግ ብዙውን ግዜ ንግድ ማጭበርበር ቀላል ወንጀል ተደርጎ ቢታይም በክሱ ውስጥ በከባድ ወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉ ክሶች ተካተዋል።

ሕግ አዋቂዎች ግን ትራምፕ የእስር ግዜ እንዲያሳልፉ የመወሰኑ ዕድል በጣም ጠባብ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትራምፕ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ መሆን ይችላሉ?

አዎ። ትራምፕ ምንም እንኳ በይፋዊ መንገድ ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበው በወንጀል ክስ ቢመሰረተባቸውም በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ የሚከለክላቸው አንቀጽ የለም።

ክስ ተመስርቶባቸው ብቻም ሳይሆን ቢታሰሩ እንኳ ከማረሚያ ቤት ሆነው ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ የሚችሉበት አጋጣሚ አለ።

ይሁን እንጂ ትራምፕ በወንጀል መከሰሳቸው እና የተጓተት የፍርድ ሂደት በፖለቲካዊ ሕይወታቸው እና በምርጫ ቅስቀሳ ሥራዎቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።

BBC Amharic

Exit mobile version