Site icon ETHIO12.COM

የጦርነት ናፍቆታችንን ለታዘበ ድሆች አንመስልም !

Image - DW english war in tigray.

የትግራዩ ጦርነት በሁለት አመታት ተገባዷል። እዚያ ጦርነት ውስጥ ሁላችንም ተሳትፈናል – የተሳትፏችን መጠን ቢለያይም። እጃችን ላይ ደም አለ ፣ በይቅርታና ፍትህ ሊተጠብ የሚገባ። አሳዛኙ ነገር የዚህ ጦርነት ሰቆቃ trauma ገና ሳይታከም ቁስሉ ሳይደርቅ ” ጦርነት አውርድ ” እያለ አምላኩን የሚማጸነው ሰው ቁጥር ዛሬም ትንሽ አይደለም። ከስቃያችን ፣ ከደረሰው ውድመትና እልቂት እንዴት መማር አቃተን ?

መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ዋንኛ ጠላት ድህነቷ ነው ይል ነበር። ወዲ ዜናዊ ምናልባትም የድህነታችን ነገር በቅጡ የገባው በስራ ምክንያት ከሀገር ውጪም ሀገር ውስጥም ካደረገው ጉዞ ሳይሆን አይቀርም። የዚህ ዘመን የፖለቲካ ዩቱይበሮች ከወሬ የሚገኘው ገቢ ልቦናቸውን ደፍቶት የድህነታችን ልክ ውልም አይላቸው። ጦርነት በየመንፈቁ ቢነሳ ፣ ሚሊዮኖች ቢፈናቀሉ ግዳቸውም አይደለም ያውም ሌላ የገቢ ምንጭ የሚፈጥር መልካም ዕድል እንጂ። ዲያስፖራ ያለው ቀላል የማይባለው ወገናችንም ” ካልደፈረሰ አይጠራም ” የሚል መፈክር መነቅነቅ ከጀመረ ሰነባብቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ድህነት ክብራችንን ገመናችንን ለመሸፈን በሚደረግ ጥረት ይሸፈናል እንጂ እጅግ ሰቅጣጭ ነው። ኖርዌይ ትምህርቱን PHD ተምሮ ወደ ሀገሩ ከተመለሰው ወዳጄ መሰለ ተሬቻ ጋር ሳወጋ ጀማሪ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ምሳቸውን የሚዘሉባቸው ቀናቶች ጥቂት እንዳልሆኑ አውግቶኛል። በአንጻሩ ናይሮቢና ካምፓላ የሚኖር የቀን ሰራተኛ የተጠበሰ እንቁላል አልያም ዶሮ ከዳቦ ጋር ከመንገድ ዳር ምግብ ቤቶች በልቶ ወደቤቱ መግባት ብዙም እንደማይቸግረው ሀገራቱን እግር ጥሎት የጎበኘ ሁሉ የሚታዘበው ሀቅ ነው። ሌላው ቀርቶ የዩኒቨርስቲ መምህራኖቿን መግባ ማሳደር የማትችል ሀገር እንዴት ዳግም ጦርነት ውስጥ ትግባ ብለን ጦር አውርድ እንላለን ?

የዛሬ አስር ምናምን አመት የፈረንጅ ሀገር ትምህርት እማር በነበረበት ጊዜ የትርፍ ጊዜ ስራ በአንድ የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል እሰራ ነበር። ቁርስና ምሳ ከተበላ በኋላ ታካሚዎቹ ወደ activity centre ይገባሉ። የሚማርም ይማራል ፣ ፑል ምናምን መጫወት የሚፈልግም ይጫወታል ቴሌቭዥን መመልከት የሚፈልግም እንዲሁ። በዚህ ወቅት እጠላው የነበረ ስራ ቴሌቪዥን ከሚመለከቱ ታካሚዎች ጋር መቀመጥን ነበር። የፈረንጅ ሀገር day time TV program ዋንኛ ተመልካች ቤት የሚውሉ አዛውንቶች ናቸው። በእያንዳንዱ የቲቪ ፕሮግራም መሀል water አልያም aid save the children የዕርዳታ ጥሪ ያቀርባሉ። ብዙውን ጊዜ ለምስል የሚጠቀሙት ድህነት ያደቀቃቸውን ኢትዮጵያውያንን ወይም ስደተኛ መጠለያ ያሉ ሶማሌዎችን ምስል ነው። የሌላው አፍሪካዊ ምስልና ስሙ እምብዛም ከድህነት ጋር ተያይዞ አይጠራም። እነዚህ የቲቪ ማስታወቂያዎች ሲመጡ አፍሪካዊም ሆነ የሀገሬዎን ሰዎች የስራ ባልደረቦቼን አይን በዘዴ እሸሻለሁ።

ስለ ጦርነትና ግጭት አጠናን የሚሉ ሰዎች በአሁኑ የአለም ሁኔታ የአንድ የእርስ በእርስ ጦርነት አማካይ ዕድሜ ስምንት አመታት ነው ይላሉ። እንደ መታደል ሆኖ ፣ በሆነ ተአምር ( የምዕራባውያኑ ጡንቻና ጫና ሳይዘነጋ ) የትግራዩ ጦርነት በሁለት አመታት ተገባዷል። እዚያ ጦርነት ውስጥ ሁላችንም ተሳትፈናል – የተሳትፏችን መጠን ቢለያይም። እጃችን ላይ ደም አለ ፣ በይቅርታና ፍትህ ሊተጠብ የሚገባ።

አሳዛኙ ነገር የዚህ ጦርነት ሰቆቃ trauma ገና ሳይታከም ቁስሉ ሳይደርቅ ” ጦርነት አውርድ ” እያለ አምላኩን የሚማጸነው ሰው ቁጥር ዛሬም ትንሽ አይደለም። ከስቃያችን ፣ ከደረሰው ውድመትና እልቂት እንዴት መማር አቃተን ?

ጦርነት ፣ ግጭትን መቆስቆስ ላይ በውጭ የምንኖር ሰዎች የመጨረሻ ተሳታፊዎች ልንሆን ይገባል የሚል እምነት አለኝ። መንግስትን ፣ አገዛዙን መቃወም መሞገት ላይ ከፊት መሰለፍ ይቻል/ይሞከር ይሆናል ነገር ግን የፖለቲካ ችግሮች በጉልበት ይፈቱ ዘንድ መወትወት ላይ ዲያጶራው ከኃላ ሊሰለፍ ቢቻል ከበ*ለውና በሎ*ም ጨዋታ መራቅ አለበት። የመኪና ክላክስ የማይሰማባቸው ሀገሮች ላይ የሚኖር ሰው የመድፍና ዲሽቃ አሩሩች የሚወነጨፉበትን ፣ ሺዎች በደቂቃዎች ህይወታቸውን የሚያጡበትን ጦርነት በምን ሞራልና አመክንዮ ግፋ በለው ሊል ይቻለዋል ?

ትናንት ጦርነት አዳምቀናል ፣ ሰበር ዜና አራብተናል ያ ማለት ከትናንት ስህተታችን አንማርም ማለት አይደለም። ጦርነትን ዳግም አልደግፍም ለኢትዮጵያም ሌላ ዙር መከራ አልመኝላትም !

Samson Michailovich ፌስ ቡክ የተወሰደ

Exit mobile version