ፎቶ - የመጀመሪያው በረራ ከአዲስ አበባ አስመራ ሲደረግ የነበረውን የህዝብ ስሜት

ኤርትራን መንካት እንደማይታሰብ ኢትዮጵያ አስታወቀች፣ “ውለታን መርሳት ነውር ነው”

” ውለታን መርሳት ነውር ነው” በሚል የመንግስት ቁርጥ ያለ አቋም የተገለጸው “ተቃዋሚ” ፓርቲዎችን በመሰብሰብ “የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ለምን አይወጡም በሚል ተደራራቢ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ነው። “በሦስተኛው ዙር አገሪቱን ለመጨረሻ ጊዜ ለማፍረስ በተካሄደው ጦርነት” አሉ አቶ ሬድዋን፣ “የፌዴራል መንግሥት በቆቦ በኩል ባለው ዳገት ወደ ላይ መውጣት ስላዳገተው፣ ትህነግ ያለውን መልክዓ ምድራዊ ጠቀሜታ ተጠቅሞ ቆቦን ተቆጣጥሮ ነበር” ሲሉ ኤርትራን እንደ ጠላት በማየት ጥያቄ ላቀረቡት ምስላዊ ማብራሪያ ሰጡ።

ይህ ሲሆን ወቅቱ ክረምት መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው ካስታወሱ በሁዋላ ” በዝናብ ምክንያት በምዕራብ በኩል ተከዜን የኢትዮጵያ ሰራዊት ማቋረጥ ባለመቻሉ፣ አቅጣጫ ቀይሮ ያለስጋት በዛላምበሳና በአዲግራት በኩል ተከዜን እንዲሻገር የኤርትራ መንግሥት በመፍቀዱ ጦርነቱ ሊቀለበስ ችሏል” ሲሉ ኤርትራ ክህደት ተፍጽሞበት የታረደውን የኢትዮጵያ አለኝታ ሰራዊት ተቀብላ ከማስተናገዷ በተጨማሪ ያበረከተችውን የማይረሳ አስተዋጾ ገለጹ።

ኤርትራ ባትተባበር ኖሮ ምን ሊፈጠር ይችል እንደነበር ሲገልጹ “ለአጭር ጊዜም ቢሆን በራቸውን ባይፈቅዱልን ኖሮ ይኼንን ጦርነት መቀልበስ አይቻልም ነበር፡፡ እንደ አገር ከባድ ፈተና ውስጥ እንወድቅ ነበር” በማለት “ውለታ መርሳት ነውር ነው” ያሉበትን አንድ ምክንያት ገልጸዋል። ይህንኑ አሳብ በወታደራዊ ቋንቋ ሌተና ጀነራል ባጫ ደበሌ ” በቆቦ በኩል ወደፊት የሚገፋ እብድ የለም። ከተፈጥሮ ጋር ውጊያ አይታሰብም። በሌላ አቅጣጫ እናስኬደዋለን” ማለታቸው ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ የደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን መንግስት ኤርትራ ላይ የያዘውን አቋምና የአቋሙን አግባብነት የሚያሳይ ማብራሪያ ከሰጡ በሁዋላ፣”የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ይውጣ የሚሉት አካላት ለኢትዮጵያ አዝነው አይደለም” ሲሉ ወቅሰዋል። ወቀሳቸውን ሲያጠናክሩ “ኤርትራ ትውጣ የሚሉ አካላት ሱዳን 50 ኪሎ ሜትር አልፎ ድንበር ወሮ በነበረበት ወቅት አፋቸውን ዘግተው ነበር” ሲሉ ስለ ብሄራዊ ጥቅምና አገር መውደድ የሚገለባበጠውን የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቋም ለማሳየት ሞክረዋል።

ከሃምሳ በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በተገኙበት ስለ ሰላም አተገባበርና አካሄድ መረጃ ለመስጠት በተካሄደ ውይይት ላይ “ኤርትራ ትውጣ” በሚል ለተነሳው ጥያቄ አቶ ሬድዋን መልሳቸው ከላይ በተገለጸው ምክንያት ብቻ አላቆሙም። ግብጽን አንስተው የትርምስ ገመዱንና እቅዱን በማሳየት ” ይህ ሁሉ ሲሆን የት ነበራችሁ?” ሲሉ ሞግተዋቸዋል።

See also  ከተከዜ ግድብ "ተመቷል" ዜና ጀርባ ያለው ደባ !

ተጨማሪ ይህን ያንብቡ

“… ግብፅ በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ መድባ ለጋምቤላ፣ ለኦነግ ሸኔና ለትህነግ ጭምር በአየርና መሬት ወደ ኢትዮጵያ መሳሪያ እያስገባች ስታስታጥቅ፣ ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች ምንም አላላችሁም” ሲሉ ፈትነዋቸዋል። አክለውም “ይህ [የተቃዋሚዎች አቋም]የሚያሳየው እንቅስቃሴው መንግሥትን የሚያዳክም ሲሆን ዝምታ፣ መንግሥትን የሚያግዝ ሲሆን ደግሞ ጩኸት ማብዛት የሚወዱ በመኖራቸው ነው” ሲሉ የሁከቱና የመንግስት መዳከምን መሰረት አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ ነግረዋቸዋል።

ሬድዋን “ኤርትራ እኛን አስቸገረን ካላልን ምን አሳሰባቸው?” ሲሉ ጠይቀው፣ “ኤርትራ ባስቸገረን ጊዜ እኛ ራሳችን በቃን እንላለን፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ካሳሰባችሁ ሱዳን ትውጣ ብላችሁ መግለጫ አውጡ” ሲሉ መንግስትና ኤርትራ ተናበው እንደሚሰሩ፣ ይህ የማይናወጥ አብሮነት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ፍትሃዊ አቋም ማራመድ ሲጀመሩ “ኤርትራ ትውጣ ብትሉ እኛ መረዳት እችላለን” ሲሉ ጉዳዩ ላይ ያለው መንሸዋረር እንዲጠራ አሳስበዋል። መክረዋል።

ግልጥ ያለውን የመንግስትን አቋም ሲያስታውቁ “በእኛ [ኢትዮጵያን] አስታኮ የኤርትራ መንግሥትን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም፡፡ ቢያንስ ከተፈጠረው የሰላም ስምምነት አንፃር እኛ እንዳንፈርስ አግዘውናል” ብለዋል። ከዚህ ቀደም ትህነግ መንግስትንና ኤርትራን ለማጣላት ሂሳብ እያሰላ የመንቀሳቀስ ስልት እንደሚከተል ገልጸን መዘገባችን የሚታወስ ነው። የኤርትራ መንግስት ደግሞ “ትህነግ ስጋት እስከሆነ ድረስ ለደህንነታቸው ሲሉ ከገቡበት ለቀው እንደማይወጡ ሲያስታውቁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።


” … አብይ አሕመድ በብርሃን ፍጥነት ኤርትራ የዘለቁትና አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ዓለምን ጉድ ያሰኘ የፖለቲካ እርቅ በማካሄድ የመቻላቸው ሚስጢር ቁልፍ ዛሬ ላይ የሆነውን በማየትም የማይገባቸው ካሉ ችግር ነው። እሳቸው ኢትዮጵያን ሲረከበቡ ምን ምን አስቀድመው እንደሚፈጽሙ ተረድተው ስለጀመሩ ነው ብዙ ጊዜ ‘ልንሰራ ያሰብነውን ከማንም በላይ የሚረዱት ጠላቶቻችን ናቸው የሚሉት። ሰሞኑንንም ‘ ለማድረግ አስበን የተነሳነውን ሌሎች የአፍሪካ አገራት ይከተሉታል በሚል መከራችን የሚበዛው ጉዟችን ወዴት እንደሆነ ስለተረዱት ነው’ ብለው ሰፊ መግለጫ ሰጥተዋል። ኤርትራ ሲገቡም ለምን እንደገቡ ከነ ሙሉ አስፈላጊነቱ፣ ወዳጅነቱንም ከነ ሙሉ እመነቱ ያደረገጉት ለዚህ ነው” ከማህበራዊ ገጽ ግርጌ የተወሰደ


አቶ ሬድዋን ይህንኑ የኤርትራን አቋም ግንዛቤ ውስጥ በመክተት፣ ከዛም በላይ በመናበብ እንደሚሰሩ ግልጽ በማድረግ ዲፕሎማሲያዊ ሃረግ አክለዋል። “የጋራ ጠላት የነበረን ቢሆንም” አሉ የደህንነት አማካሪው፣ “ትጥቁን የፈታ የትህነግ ታጣቂ ግን ኢትዮጵያዊ ነው”ሲሉ ትህነግ ካልታጠቀ ስጋት እንደማይሆን አስታውቀዋል። ትጥቅ መፍታቱ ኤርትራናም ሆነ በትግራይ ዙሪያ ያሉትን ወገኖች ሰላም እንደሚሰጥ ከስምምነቱ በሁዋላ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር። በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው “… ስለዚህ አቅማችን ባለበት እስኪጠናከር ትህነግ መጀመሪያ ትጥቁን መፍታት ይጀምርና እንደማንወጋ ስናረጋግጥ፣ ከጀርባችን ያለው አካል ማንም ይሁን ማን ይውጣልን ማለት እንችላለን” ሲሉ አመክንዮ የተሞላው ምላሽ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የደንነትና ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

See also  የአምነስቲ " ሽንቁረ ብዙ" ሪፖርት የተከፋዮች የቲውተር ዜና ድምር

ወልቃይትን አስመልክቶ ከግራና ቀኝ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ እንዲሆን ባስበ መልኩ ይመስላል አቶ ሬድዋን የተናገሩት። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የሱዳን መውጪያ በርም ልክ እንደ አሰብ ሁሉ እንዳይወሰድ በሚል ስጋታቸውን ጨምረው ላነሱት “ከጅምሩ የጦርነቱ ዓላማ ወልቃይትን ማስመለስና ትህነግን ማጥፋት አልነበረም” ሲሉ ነው አቶ ሬድዋን ያስታወቁት። የጦርነቱ ዋና ዓላማ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማስፈን እንደነበር አሳስበው፣ “ትህነግን እንደ ፖለቲካ ኃይል የማጥፋት ዓላማ ያለው ሰው ይኖራል፣ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱ ዓላማ አይደለም” ሲሉ ትህነግን ማቀፍም ሆነ መግፋት የትግራይ ህዝብ ውሳኔ እንጂ የሌሎች አካላት እንዳልሆነ አመላካሽ ምላሽ ሰጥተዋል። ከላይ እንደገለጹት ትጥቅ የፈታ ትህነግ ኢትዮጵያዊ ነውና።

ወልቃይት በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ያለ ፀብ በመሆኑ በሁለት ክልሎች መካከል ያለው ፀብ ደግሞ የሚፈታው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚመራው ሥርዓት በህግና ህግ ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል። የፌደራል መንግስት ባለው የህግ አግባብ የህግ ጨዋታውን ገለልተኛ ሆኖ ማስፈጸም እንጂ ሌላ ተልዕኮ ሊኖረው እንደማይችል ባለሙያዎችም ሲናገሩ ነበር።

“የፌዴራል መንግሥትን አቅም ተራ በተራ ጡንቻ እየተፈታተን አንዳችን ሌላችንን ማንበርከክ ይቁም” ሲሉ ጉልበት መፍትሄ እንደማያመጣና አንዱ ሲደክም ሌላው ሲበረታ፣ የሚገኝ ድል አስተማማኝ እንደማይሆን ገልጸዋል።

“ወልቃይትን ከዚህ ቀደም ትህነግ ጡንቻ ስለነበረው በጉልበት ወስዷል” ሲሉ ያለፈውን አካሄድ ፍትሃዊ እንዳልነበር ያወሱት አቶ ሬድዋን፣ ዛሬ ትህነግ ሸብረክ ሲል ጡንቻ ያለው አካል ይውሰድ ካልን መጪው ትውልድ 20 ዓመት ጠብቆ ድንገት ጡንቻ ካገኘ ዳግም ይወስደዋል። ስለዚህ ዘላቂው መፍትሔ ጡንቻ ሳይሆን ሕግና ሥርዓት ነው” ሲሉ ጉዳዩ በህግ አግባብ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ የመንግስታቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ ወታደሮች ከሽሬና አክሱም ለቀው ወደ ራሳቸው ድንበር መጠጋታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ሮይተርስ እንዳሻው የሚያገኛቸውን አቶ ጌታቸው ለማረጋግጫ ፈልጎ እንዳላገኘ በዜናው ጠቅሷል። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ተጠይቀው ማረጋገጫም ሆነ ማስተማመኛ እንዳልሰጡት፣ ነገር ግን ዕርዳታ ሰራተኞች እንደነገሩት ገልጾ ሮይተርስ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ይህ የትህነግ ወዳጅ ለሆኑንና “ኤርትራ ሰራዊቷን ታስወጣ” ለሚሉ ሁሉ ከቢድ ዜና በመሆኑ ትህነግ እውቅና ሊሰጠው እንደማይፍለግ እምነታቸው የሚገልጹ አሉ።

See also  ኢሳያስ የትህነግ ወደ ሸዋ ማቅናት ከውትድርና አንጻር እብደት መሆኑን፣ ውሳኔው የአለቆች አምልኮ ውጤት መሆኑንን አስታወቁ

የትህነግ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን ባስረከቡ መጠንና ለማናቸውም የአገሪቱም ይሁን የጎረቤት መንደሮች ስጋት መሆናቸው በተመናመነ ቁጥር ኤርትራ ወታደሮቿን እንድትስብ ከመንግስት ጋር በስምምነት እንደሚሰራ ገልጸን መዘገባችን ይታወሳል። በዚህ ዜናችን የኤርትራና ኢትዮጵያ ወታደሮች ሰላምታ በመቀያየር ምሽግ መረካከባቸውን ነበር የገለጽነው።

“የእኛ ወገን የምንላቸው የትህነግ ሰዎች ለሰላሳ ዓመታት ታገልኩለት ያሉትን ሕዝብ ለሰላሳ ዓመታት እየቀለበ፣ እየጠበቀ፣ አብሮ እየሠራና እያረሰላቸው የኖረውን ሠራዊት ከጀርባው አርደው ሜዳ ላይ ሲጥሉት የታደጉት እነዚህ [ኤርትራን ማለታቸው ነው] ሰዎች ናቸው፡፡ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ውለታን መርሳት ነውር ነው” ሲሉ አቶ ሬድዋን ኤርትራ ላይ እጃቸውን ለሚቀስሩ ማሳረጊያ ሰጥተዋል።

ከሰላም ስምምነቱ ዜና ደስታና ፈንጠዝያ ጎን ለጎን “መላከላከያን ያረዱ፣ ያሳረዱና የተባበሩ ላይ ፍትህ ሊበየን ይገባል” የሚሉ ድምጾች የተሰሙትም ለዚሁ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ፣ በአፋርና አማራ እንዲሁም በተዘዋዋሪ በሌሎች አካባቢዎች በንጹሃን ላይ ጭፍጨፋ የፈጸሙና ያስፈጸሙ፣ የህዝብ ንብረትና ማህበራዊ መገልገያዎችን ያወደሙ፣ የጅምላ ግድያ ያስፈጸሙ ወዘተ ላይ ብሄር፣ ሰፈር፣ ቋንቋና ማንነት ሳይለይ ህግ እንዲጸናባቸው ፍትህ ወዳድ ዜጎች እየጠየቁ ነው።

ድንገት ወደ መቀለ ባመራው የመንግስት ልዑክ አካላት ውስጥ የፍትህ ሚኒስትሩና የእርቅ ኮሚሽን አባላት መካከታታቸው በህግ ተጠያቂነት አግባብ ከትህነግ አመራሮች ጋር ለመነጋገር እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች እየገለጹ ነው። ይህን ለማድረግ ቅሬታ ቢኖር እንኳን ” ወንጀለኞች በህግ አይጠየቁ” የሚል መከራከሪያ በማንሳት ዓለም አቀፍ ጫና ሊነሳ እንደማይችል የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በሰላም ውሉም ላይ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል ይህ ፍትህ አንዱ ነው።

በዜናው የተጠቀሱት አቶ ሬድዋን ያተናገሩት ከሪፖርተር ዜና ላይ ቃል በቃልና የተወሰደና በዝጅት ክፍሉ አባሪ መረጃዎ እንደገና የተጻፈ ዜና ትንታኔ ነው ።

Leave a Reply