ETHIO12.COM

የህዳሴ ግድባችን፤ ከመጋቢት 24/2003 ዓ.ም እስከ ዛሬ

ዓመታዊ አማካይ የውሃ ፍሰት 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በሆነው አባይ ላይ የተመሰረተው ታላቁ የህዳሴ ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉራዊ የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ ትርጉም የሚሰጠው ነው። በጥናት እንደ ተረጋገጠው . . . ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተለይም ለሱዳን ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚኖረው ይሆናል። በግብርናው ዘርፍ ሱዳናውያን በዓመት ሦስቴ እንዲያመርቱ፣ በሱዳን ከተሞች የሚደርሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመቀነስ እና በዋነኝነት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የግድቡ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

አጠቃላይ መረጃ

• ግድቡ የሚገኝበት ቦታ – ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ ጉባ ወረዳ

• የግድቡን ግንባታ የሚያከናውነው ሥራ ተቋራጭ – የጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ

• የሚያመነጨው የሃይል መጠን – 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት

• ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ መጠን – 80 ቢሊየን ብር (የመሰረት ድንጋዩ ሲጣል፣ ከ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ)

• የሃይል ማመንጫ ዩኒቶች ብዛት – 13

* እያንዳንዱ ዩኒት የሚያመነጨው የሃይል መጠን – 6ሺህ 450 ሜጋ ዋት

* የዋናው ግድብ ከፍታ – 145 ሜትር

* የዋናው ግድብ ርዝመት – 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር

* የዋናው ግድብ ውፍረት – የግድቡ ግርጌ 130 ሜትር ሲሆን የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል 11 ሜትር፤

* ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን – 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር

* ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት – 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር

* ሲጠናቀቅ ውሃ የሚተኛበት መሬት ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር

* ግንባታው አሁን ላይ 84 በመቶ ደርሷል።

(ምንጭ፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት)

ነባሩን የቅኝ አገዛዝ እሳቤ መንፈስ፣ የውኃ ጂኦፖለቲካ ወዘተ ላይመለስ የደረመሰው የህዳሴ ግድብ ሙሌቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ70 በላይ (40 ያህሉ ብቻ ከ10 ሄክታር በላይ ይሸፍናሉ) ደሴቶች እንደሚኖሩት፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ግዙፍ የመዝናኛ ስፍራ እንደሚሆን ከወዲሁ እየተነገረለት ያለ ሲሆን፣ ጉዳዩን ከመነሻው ያብራራ፣ የግንባታው ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ያዘጋጀው 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ጳጉሜ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዶ ነበር፡፡

በእለቱ የ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ እቅድ ለጉባኤተኞቹ ቀርቦ በጥልቀት ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በጉባኤውም “የተለያዩ የልማት ስራዎችን በአንድነትና በትብብር ከሰራን ኢትዮጵያ የማታድግበት ምንም ምክንያት የለም” (የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ) የሚል መሰረታዊ ሀሳብ ተላልፎበታል።

ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ለአረንጓዴ ልማት ያነሳሳው፤ የአገራችንም ስነ ምህዳር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሻሻል፤ ለቴክኖሎጂም ሽግግር እገዛ በማድረግ ዜጎች በተግባር የተደገፈ ሰፊ እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ፤ እንዲሁም ቴክኖሎጂና ልምድ እንዲቀስሙ (የግድቡን ዲዛየን በማሻሻል እና የተርባይኖች አቅም በማሳደግ የግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም ከ5ሺህ 250 ወደ 6ሺህ 450 ያሳደጉት ዜጎች መሆናቸውን ልብ ይሏል) ያደረገው፤ የአገር ውስጥና የውጪ ቱሪዝምን በተለየ ሁኔታ የሚያበረታታው የህዳሴ ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎቻችን (በሸቀጣሸቀጥ፣ ምግብ፣ ትራንስፖርት በማቅረብ ተጠቃሚ የሆኑትን ሳይጨምር፤ ከ13ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን፤ እንዲሁም፣ ከ400 በላይ ለሚሆኑ የውጭ ዜጎች – ከዚህም ሊበልጥ ይችላል) የስራ ዕድልን የፈጠረውን፤ የ3ኛውን ዙር ሙሌት መጠናቀቅን ተከትሎ አባይ ከባሕር ጠለል በላይ ከ600 ሜትር ከፍታ ላይ ይፈስ ዘንድ ያስቻለው መሆኑንና የመሳሰሉት የ2014 ወሳኝ ክንውኖች መሆናቸው ከላይ በጠቀስነው 14ኛው መደበኛ ጉባኤ (ጳጉሜ፣ 2014 ዓ.ም) ላይ መገለፁ የሚታወስ ነው።

የሕዝብ ተሳትፎ

በህዝቦች አስተሳሰብ ውስጥ የቁጠባ ባህልን እንዲዳብር እድል የፈጠረ፣ ቁጠባን ባህል ወደ ማድረግ (ግድቡ ሲጀመር አካባቢ የአገራችን የቁጠባ ባህል 5 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ አገራዊ ቁጠባችን 25 በመቶ አካባቢ ደርሷል) የመራው የህዳሴው ግድብ የሁሉን ድጋፍ ያተረፈ ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የፖለቲካ አመለካከት፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ የመኖሪያ ቦታ (ከአገር ውስጥም ይሁን ከውጭ) ርቀት ሳይገድበው፣ የብሄር፣ የዕድሜ ወይም የጾታ ልዩነት ሳይታይበት ሁሉም በአንድነት ሁሉአቀፍ ድጋፉን ችሮታል። “ለዚህ ግድብ ድጋፍ ያላደረጉት ኢትዮጵያዊያን በማህጸን ያሉ ህጻናት እና በመቃብር ያሉ ሙታኖች ብቻ ናቸው” እስኪባል ድረስ ሁሉም የሚችለውን ሁሉ አድርጓል።

ከዚህ አኳያ፣ እኛ ኢትዮጵያውን ተደራራቢ ችግሮችን አልፈን ፕሮጀክቱ ዛሬ ላይ ለደረሰበት ደረጃ ማድረሳችን በብዙዎች በአድናቆትና አግራሞት እየተነገረ መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው። የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎችም ሆኑ መንግስት ሕዝቡ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ እንደሚያደርግ እምነታቸውን ሁሌም በመግለፅ ላይ መሆናቸውም እንደዛው።

8ሺህ ኪ.ሜ የሚሸፍን 2ኛው ዙር “የህዳሴ ግድብ ጉዞ 2” የሚል ስያሜ ያለው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተጀምሮ በመካሄድ ላይ መገኘቱም ይህንን ህዝባዊ ተሳትፎ ከማጠናከር አኳያ ሲሆን፣ ስለሁኔታና ሂደቱ ከሚያትቱ ዘገባዎች መረዳት እንደተቻለው መርሀ ግብሩ በጥሩ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ሕብረተሰቡ ለዚህ ያለምንም የውጭ አገራት ብድር እና ዕርዳታ እየተከናወነ ለሚገኘው፣ አገራዊ ፕሮጀክት ያለውን አጋርነት የማጠናከር እና ገቢ የማሰባሰብ አላማ ያለው ይህ የጉዞ መርሐ ግብር (በመርሀ ግብሩ 200 ሚሊዮን ብር በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮች ለመሰብሰብ ታቅዷል) በከፍተኛ ደረጃ ህዝባዊ ንቅናቄ የተካሄደበት ሲሆን፣ በዚሁ ፕሮግራም (ለምሳሌ ያህል ማለት ነው) በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብቻ በአንድ ቀን ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ተፈፅሟል።

የመርሀ ግብሩ ጉዞ 200 ከተሞችን የሚያዳርስ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ የሚያደርገው ፕሮግራም (የህዳሴ ግድብ ቱር 2፣ ኃብት ማሰባሰቢያ መረሃ-ግብር) ወደ አገሪቱ ሰሜን አቅጣጫ እንደሚያቀናም በወቅቱ መገለፁ የሚታወስ ነው። (የካቲት 2ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው ይህ ፕሮግራም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እና በኢትዮጵያ ታሪክ ባህል እና ቅርፅ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት የተዘጋጀ ነው።)

ከሶስት ዓመታት በኋላ (በ2017 ዓ.ም) ተጠናቆ የሚጠበቅበትን 6 ሺ 450 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚጀምረውና የአገሪቱን 40 በመቶ የሃይል አቅርቦት የሚሸፍነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት መጋቢት 2003 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ከሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች በአጠቃላይ 17 ቢሊዮን 188 ሚሊዮን 444 ሺህ 565 ብር መሰብሰቡም ታውቋል፡፡

13 ተርባይኖች ያሉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪ ጽህፈት ቤት በማህበራዊ (ፌስቡክ) ድረ-ገጹ (Grand Ethiopian Renaissance Dam) ላይ ኦገስት 24 2022 ለንባበብ እንዳበቃው ከሆነ፣ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ብቻ 273 ሚሊየን 132 ሺህ 427ብር ተሰብስቧል፡፡ አርሶ አደሩም በጉልበቱ ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር እንደሚበልጥ የሚገመት ድጋፍ አድርጓል።

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ በ27/6/2015 እንዳስታወቀው “የቦንድ እና የፒን ሽያጭ በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን ሕዝቡም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የቀረውን ግንባታ ለመጨረስ እስከ መጨረሻው ድጋፉን እንደሚቀጥል ቃል” ገብቷል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!!!” ማለታችን ትክክል መሆኑን ነውና፣ በነካ እጃችን ሌሎች ግድቦችንም እንደምንቀጥል ከበቂ በላይ የሆነ ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተካ እንደተናገሩት (ፌብሯሪ 22፣ 2023፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ቀን ጀምሮ ማህበረሰቡን በማስተባበር ከ17ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ከ868 ሚሊያን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም አያይዘው መግለፃቸውን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር በ2014 ብቻ በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያዎች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከኅብረተሰቡ መሰብሰቡን ስናክልበት ደግሞ የሕዝቡ ተሳትፎ ከ“ተአምር”ም ባለፈ ሰማይ ጠቀስ መሆኑን እንገነዘባለን።

ከላይ በጠቀስነውና በሸራተን አዲስ በተካሄደው ጉባኤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል። “የጋራ መገለጫ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችንን በማጠናቀቅ አሸናፊነትን ለትውልድ እናውርስ!፡፡” ለሚለው ጥሪም ሁላችንም ፈጣን ምላሽ ልንሰጠው ይገባልም ተብሏል። ይህም የህብረተሰቡ ያልተቋረጠ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ያሳያልና “እንደ ጀመርነው እንጨርሰዋለን!!!” የሚለው እዚህም ይደገማል ማለት ነው።

አስተያየቶች

ኢትዮጵያ ስታስረዳ እንደ ቆየችው፣ ግድቡ ለጎረቤት እና እህትማማች አገራት ሁለንተናዊ ትስስር መጠናከር ወሳኝ ነው። የዓባይ ውኃ የተፋሰሱ አገራት የውጥረት ምክንያት ሳይሆን የልማት እና የትብብር መሆን ይገባዋል። አገራት በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው ከተንቀሳቀሱና የጋራ ተቋማዊ አደረጃጀት ከፈጠሩ የመልማት እድላቸው ሰፊ ነው። (ተቀማጭነቱን በሱዳን ካርቱም ያደረገው የአፍሪካ የአስተዳደር፣ ሰላም እና ሽግግር ጥናት ማዕከል ዋና ጸሐፊ ዶክተር ማህሙድ ዘይንላብዲን)

ባለፈው ነሀሴ የህዳሴ ግድቡን የጎበኙት ሱዳናውያን ምሁራን “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የትብብር እንጂ የንትርክ መንስኤ ሊሆን አይገባም።” ማለታቸው በየሚዲያዎች የተስተጋባ ሲሆን፤ የሌሎች ምሁራን ተመሳሳይ አቋምም እንደዚሁ ለአየር በቅቶ ሰምተናል።

ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በተፋሰሱ አገራት መካከል እንዲነግስ የሚያደርገው፤ ከአገራት ጋር የመተማመንና የመተባበር ዲፕሎማሲን እንዲፈጠር ምቹ መደላድል የሚፈጥረው፤ ኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ አመለካከትን የተላበስን መሆናችንን ለዓለም ለማሳወቅ ጥሩ አጋጣሚን የፈጠረው፤ የአገራችንንም የመደራደር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ያጎለበተው፤ የአገራችንን ገጽታ በመቀየሩ በኩል የማይተካ ሚናን የተጫወተው፤ ግብፅን ጨምሮ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ለውይይት እና ምክክር በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ ያስቻለው፤ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሃብታቸውን በትብብር እና በመደጋገፍ ከመጠቀም ውጪ ሌላ አማራጭ እንደማይኖራቸው በግልፅ ያሳየው፤ አይቻልምን በይቻላል የቀየረው፤ ሲጠናቀቅ ከ1ሺህ 680 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት የሚሸፍነው፤ በዓመት ከ10ሺህ ቶን በላይ ዓሳ የማምረት አቅምን የሚፈጥረው፤ ለሌሎች ታዳጊ አገራት ደግሞ በተፈጥሮ ሃብታቸው እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ መንገድን ያመላከተ (ያነቃቃም ጭምር)፤ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ፤ እንደመርግ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ ሁለተኛውን ኃይል ማፍለቅ የቻለው . . . ወዘተርፈ ታላቁ የህዳሴ ግድባችን በርካታ ውጫዊ መሰናክሎች ገጥመውት የነበረ ቢሆንም፣ ሁሉንም በጣጥሶ በማለፍ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ሊገኝ የቻለ ተአምረኛ ግድብ ነው።

ይህንን ሁሉ መሰናክል በማለፉም የበርካቶችን አድናቆት ሊያተርፍ የቻለ አኩሪ የሚሊኒየሙ ስኬት ለመሆን የበቃ ሕዝባዊ ኩራትና ብሔራዊ አርማ መሆኑም በበርካቶች ተመስክሮለታል።

የግድቡ አሁናዊ ይዞታ

የግድቡ ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ኃይል የማመንጨት ሥራን ለማስጀመር በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንደገለፁት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ወደ 83 ነጥብ 3 በመቶ፤ የግድቡ የሲቪል ሥራዎች ግንባታ 95 በመቶን፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ግንባታና እና ተከላ ወደ 61 በመቶ፤ የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎችን ደግሞ 73 በመቶን የተሻገሩት ባለፈው ነሀሴ ወር ነው።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version