Site icon ETHIO12.COM

በነዳጅ ድጎማዉ ልክ ህብረተሰቡ አገልግሎት አላገኘም፣ 9.8 ቢሊዮን ወጪ ሆንዋል

ሃገር አቋራጭ: የከተማ አዉቶቡሶች እና ፐብሊክ ባሶች የትራንስፖርት ነዳጅ ድጎማን በመጠቀም ህብረተሰቡን በተሻለ መንገድ እያገለገሉ ቢሆንም ሚኒ ባስ: ሚዲ ባስ: ታክሲዎችና ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ግን በነዳጅ ድጎማዉ ልክ ህብረተሰቡን በአግባቡ እያገለገሉ አለመሆናቸዉ ተገለጸ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የ9.8 ቢሊዮን ብር የትራንስፖርት ነዳጅ ድጎማ የተደረገ ሲሆን ሚኒ ባስና ሚዲ ባስ የተባሉት ተሽከርካሪዎች የ8.2 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ መሆናቸዉ ተገልጿል።

ኮንትሮባንድን ጨምሮ ከነዳጅ አጠቃቀም ጋር ተያይዘዉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ቴሌ ብርን የመሠሉ አስገዳጅ የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ሥርዓቶችን መተግበር እንደሚገባም ተጠቁሟል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭት እና አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ ምክክር እያካሄዱ ነዉ።

በምክክር መድረኩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ እና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገ/መስቀል ጫላን ጨምሮ የፌደራል እና ክልል የንግድ ቢሮ ሃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገ/መስቀል ጫላ ከአሁን ቀደም ሲተገበር የነበረዉ የነዳጅ አጠቃቀም ለብክነት የተጋለጠና ከጎረቤት ሃገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ጋር ያልተጣጣመ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት መንግስት የ194 ቢሊዮን ብር በዕዳ እንዲሸከም አድርጎታል ብለዋል።

የሃገሪቱ የነዳጅ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እና 4 ቢሊዮን ዶላር ላይ መድረሱን የገለጹት ሚኒስትሩ በከፍተኛ በጀት ተገዝቶ ወደ ሃገር የሚገባዉን ነዳጅ በቁጠባ ለመጠቀም በሁሉም ክልሎችና ከተሞች ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ቀስ በቀስ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያ በማድረግ የነዳጅ ድጎማን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑ የገለጹት አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በቀጣይነት ሁሉም ተሽከርካሪዎች ዲጂታል የግብይት ሥርዓትን በመጠቀም ነዳጅ ከማደያዎች እንዲቀዱ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግም ከኢትዮ ቴሌኮም: ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ጉዳዩ ከሚመለካታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ሲሆን ፊንፊኔን ጨምሮ በክልል ከተሞች ቴሌ ብርን የመሠሉ አስገዳጅ የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ሥርዓቶች በቀጣይነት ተግባራዊ እንደሚደረጉ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

OBN ወንድማገኝ አሰፋ

Exit mobile version