በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መግለጫ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከከተማዋ ነዋሪዎች የተሰጠውን ሃላፊነት በውጤታማነት ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በከተማችን ስር የሰደዱና የተወሳሰቡ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም መዋቅራዊ ችግሮችን ያሉበት ሲሆን ችግሮችን ህዝቡን ባሳተፈ አግባብ ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ በዚህም አበረታች ውጤቶች መመዝገብ መጀመራቸውን በሂደቱ ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆነዉ የከተማዉ ህዝብ የሚያውቀውና የሚገነዘበዉ እዉነታ ነዉ፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በከተማ አስተዳደሩ የህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ማሳያ የሆኑ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ የሚኮሩባቸውና የብልፅግና ጉዟችን ስኬታማነት የማይቀር መሆኑን አመላካች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል፡፡ በከተማ ደረጃ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀከቶች ተቀርፀው በፍጥነትና በጥራት ተጠናቀቀው ለሕዝቡ አገልግሎት ከመስጠታቸዉ በላይም የከተማዋንና የአገሪቱን ገፅታ ወደ አዲስ ምዕራፍ ከፍ በማድረግ ደረጃ ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡

ከተማችን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን የአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መዲና እንዲሁም የአለም አቀፍ ተቋማት ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ታርኳንና ሃላፊነቷን የሚመጥን ገፅታ እንድትላበስ፣ ውብ ጽዱ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ለማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጎ የሚያበረታታ ውጤትም የተገኘበት ነው፡፡ ይህ ስራ ከተማችንን እንደ ስሟንና ታሪኳን በሚመጥን ድምቀትና ውበት ላይ እስከምትደርስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በከተማችን እየተካሄዱ ባሉ ሰው ተኮር ፕሮግራሞችም የበርካታ አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን የኑሮ ጫናቸውን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ባለሃብቶችን በማስተባበር በተለያዩ የከተማችን አካባቢዎች ያቋቋምናቸው የምገባ ማዕከሎች በቀን አንዴ እንኳን ምግብ ለማግኘት ይቸገሩ የነበሩ ዜጎቻችን ተመግበዉ እንዲዉሉ መደረግ በመቻሉ የከተማ አስተዳደሩ ለዜጎቻችን ምን ያህል አሳቢ መሆኑን አመላካች ተግባር ነዉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የተማሪዎቻችን ብሩህ አዕምሮ በምግብ እጥረት እንዳይጎዳ በትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራሞች ተቀርፀው ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ እነዚህንና ሌሎች የልማት ስራዎችንና አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፤ ከተማችንን የግጭት ማዕከል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በበኩላቸው የከተማችንን ለውጥ ወደኋላ የሚጎትቱና የህዝባችን የኑሮ ጉስቁልና የሚያባብሱ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን በመፈፀም ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የጥፋት ሃይሎች የሚደግሱትን እኩይ ሴራ የከተማችን ህዝብ በተለይም ህዝባዊ የሰላም ሰራዊቱ ከከተማዋና ከፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ሲያመክንባቸው ቆይቷል፡፡

See also  በእነ ደብረፅዮን የክስ መዝገብ ከተከሰሱ 62 ተከሳሾች መካከል 19ኙ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ በጽሑፍ እንዲደርሳቸው ተደረገ

ከሰሞኑ የከተማችን የፀጥታ ሃይል በደህንነት መዋቅሩና ከህዝቡ በቀረበለት ጥቆማ መሰረት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉ አካባቢዎች ወደ ከተማችን በመግባት ለጥፋት ተልዕኮ ስምሪት ወስደው ሲንቀሳቀሱ በህግ ቁጥጥር ስር አውሏል፡፡ አንዳንድ ወጣቶች በጥፋት ሃይሉ የውሸት ፕሮፓጋንዳና የጥቅም ማማለያ ተታለው ቀደም ሲልና አሁንም ጭምር በትምህር ቤቶች ሳይቀር በተለያዩ ወቅቶች ግጭቶችን በመቀስቀስ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስተጓጎል፤ ብሎም ከተቻላቸው አጠቃላይ የከተማ ነውጥ በመፍጠር የሴራ ፖለቲካቸውን ከዳር ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡የከተማ አስተዳደሩ ባለማወቅ በዚህ የጥፋት ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማሰብ እና ከሀገራዊ ለውጡ እሳቤዎች በመነሳት በሆደ ሰፊነት አጥፊዎችን ሲታገስ ቆይቷል፡፡ አስተዳደሩ አሁንም ችግሮችን በሰከነ ሁኔታ ለመቅረፍ የሚቀጥል ቢሆንም ከጥፋታቸው በማይታቀቡና ሌሎችንም በማሳሳት ወደ ጥፋት መንገድ የሚጋብዙትን በጠንካራ የመረጃና የደህንነት ስራ በመታገዝ እየለየ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ ይወስዳል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ የኑሮ ውድነትና የዋጋ አለመረጋጋት እንዲሁም የትራንስፖርት አቅርቦት የከተማችን ነዋሪ የኑሮ ጫና ያከበዱ ፈተናዎች እንደሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ይገነዘባል፡፡ ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመቅረፍ ምርት በሸማቾች ማህበራት በኩል በብዛት እንዲቀርብ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን ምርት የሚደብቁና ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሬ የሚያደርጉ አካላትን መቆጣጠርና እርምጃ መውሰድ ጀምሯል፡፡ መንግስት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉ እየታወቀ የባለሶስት ጎማ ወይም በተለምዶ አጠራራቸው የባጃጅ አሽከርካሪዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እንዲሁም የተወሰኑት በወንጀል ድርጊቶች ላይ በመሰማራት የከተማችን ነዋሪ የቅሬታ ምንጭ ሆነዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የባጃጅ አገልግሎትን ስርዓት ለማስያዝ የአሰራር ማስተካከያ እያደረገ ሲሆን ይህ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ በከተማችን ሁሉም አካባቢዎች የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቆም ወስኗል፡፡ የተሸርካሪዎቹ ከስራ መውጣት በነዋሪው ላይ የትራንስፖርት ጫና እንዳያሳድርም አስተዳደሩ ሌሎቹ የትራንስፖርት አገልግሎቶች በሙሉ አቅማቸውና በቅንጅት አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል የከተማችን ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ይበልጥ እያረጋገጠ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በአንፃሩ ይህ እንዳይሳካ በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የህዝቡንና የከተማዋን ሰላም አስጠብቆ እንደሚቀጥል እያረጋገጥን የከተማችን ነዋሪም እንደእስካሁኑ ሁሉ ለከተማችን ሰላም መከበርና ለህግ ሉዓላዊነት መከበር ከከተማ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

See also  በአሸባሪው የትህነግ ተጠርጣሪ አባላት ላይ በዚህ ሳምንት ክስ እንደሚመሠረት ተገለጸ።

መጋቢት 1/2015 ዓ.ም
አዲሰ አበባ

Leave a Reply