ETHIO12.COM

በካርቱም በጦር ሠራዊቱ እና በሚሊሻዎች መካከል የተቀሰቀሰው ውጊያ ተባብሷል

ከቀለም ጋር አግባቦት የላቸውም የሚባሉት የሱዳን ፈጥኖ ደረሻ መሪ በቅጽል ስማቸው ሄምቲ፣ ዋና ስምቻእው ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ከሱዳን መንግስት ቁጥጥር ስር አድርገው ያደራጁት ጦራቸው በካርቱም የተለያዩ ስፍራዎችና የተመረጡ ተቋማት ላይ ጥቃት ከፍቷል። ይህ ዓለምን በቅጽበት የናኘ ዜና በየሰዓቱ ተለዋዋጭ መረጃ እየተሰማበትም ነው።

በሱዳን በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና በተጽእኖ ፈጣሪው ፈጥኖ ደራሽ ሚሊሻ መካከል በዋና ከተማዋ ካርቱም የተቀሰቀሰው ውጊያ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ጎን ለጎን የተለዩ አገራት ስጋታቸውን በመግለጽ ውጊያው እንዲቆም እየጠየቁ ነው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ውጊያውን አውግዘው ” የውጭ ሃይል እጅ አለበት” በማለት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ማን እንደሆነ አላመለከቱም። በቅርቡ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ከሱዳን መንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት አስተካክላ የህዳሴ ግድብ ላይ ሱዳን ከግብጽ ጋር አብራ ኢትዮጵያ ላይ የጀመረችውን ደባ ማቆሟን ተከትሎ ነበር ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ አስመራ ያቀኑት። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሱዳን የቅርብ ወዳጃቸው እንደሆነች ይታወቃል።


የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የተባለው የመንግስት ጦር የጦር በማጥቃት ትንኮሳ ፈፅሞብኛል፣ ስለዚህም የካርቱምን አየር ማረፊያ፣ የብሄራዊ ቲቪና ሬዲዮን፣ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር መቀመጫ የካርቱም ሪፐብሊካን ቤተመንግስትን ተቆጣጥሬያለሁ በማለት አስታውቋል።

ካርቱም በከፍተኛ ተኩስና ፍንዳታ እየተናጠች እንደሆነ አልጀዚራ በየደቂቃው በሚሰጠው መረጃ አመልክቷል። የሀምዳን ፈጥኖ ደራሾች አውሮፕላን ጣቢያውን እንደተቆጣጠሩ ይፋ ሆኗል። የመንግስት መቀመጫ ፓላሱና የብሄራዊ ቴሌቪዥን ማሰራጫውን ለመያዝ ተኩስ እየተካሄደ ነው።

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚሉት የፍጥጫው ምክንያት በወታደራዊ አስተዳደር ስር የቆየችውን ሱዳን ወደ ሲቪል መንግሥት እንድትሸጋገር በቀረበው ንድፈ አሳብ ይህ ሃይል ወደ አገሪቱ መከላከያ እንዲጠቃለል የሚል አግባብ በመቀመጡ ነው። በዚሁ መነሻ ሳይገባቡ መክረማቸው ታውቋል። ምክንያቱም ሃይሉን የሚመራው ማን ነው? የሚለው የጡንቻ ማስከበር ጉዳይ ላይ ፈቃደኛነቱ ባለመኖሩ ነው።

ቢቢሲ ከተለያዩ ሚዲያዎች ያሰባሰበውን መረጃ ከስር ያንብቡ

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የተኩስ ድምጽ መሰማት የጀመረው በማዕከላዊ ካርቱም ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ነው። አርኤስኤፍ የሚባለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንዳለው በዋና ከተማዋ በስተደቡብ ከሚገኙት ካምፖቹ መካከል አንዱ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። የሱዳን ጦር ሠራዊት ደግሞ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች የጦር ኃይሉን ዋና መሥሪያ ቤት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።

“የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተዋጊዎች በካርቱም እና በሌሎች የሱዳን ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ የጦር ሠራዊት ካምፖች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል” ሲሉ የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ናቢል አብዳላህ መናጋረቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ጨምረውም “ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ጦር ሠራዊቱ አገሪቱን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው” ብለዋል።

ኣሳሳቢው የሱዳን ሁኔታ

የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በሱዳን የተከሰው ውጥረት እና ግጭት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሱዳን ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

ለሥራ ጉብኝት ቪዬትናም የሚገኙት ብሊንከን በውጥረቱ ውስጥ የሌሎች አካላት እጅ ሊኖርበት ይችላል ብለዋል።

የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በካርቱም የግጭቱ መባባስ በእጅጉ አሳስቦኛል ያለ ሲሆን፣ ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ መጠየቁን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በተመሳሳይ ሩሲያ በግጭቱ መባባስ ስጋት ገብቶኛል ብላለች። በሱዳን ያለው የሩሲያ ኤምባሲ የተኩስ አቁም ተደርጎ ድርድር እንዲደረግ ጠይቋል።

ብሪታኒያም ደግሞ ሱዳን ውስጥ ያሉ ዜጎቿ ከቤታቸው እንዳይወጡ አሳስባለች። በሱዳን የብሪታኒያ ኤምባሲ ዜጎቹን ወደ ውጭ ከመውጣት ተቆጥበው የጉዞ መረጃዎችን እንዲጠባብቁ አሳስቧል።

የምስሉ መግለጫ,የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የሚመሩት ጀነራል ዳጋሎ

ሮይተርስ የዜና ወኪል የዐይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው በሰሜናዊቷ የሱዳን ከተማ ሜሮዌ ውስጥ ተኩስ ይሰማ ነበረ ብለዋል።

አልአረቢያ ቴሌቪዥን ጣቢያም ከአንድ ወታደራዊ ሰፈር ውስጥ የተነሳ ጭስን ሲያሳይ እንደነበረ ሮይተርስ ዘግቧል።

ከሁለት ዓመት በፊት በሱዳን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ የጦር ጄኔራሎች ሉዓላዊ ምክር ቤት የሚባል አካል አቋቁመው አገሪቱን እየመሩ ይገኛሉ።

አርኤስኤፍ የተባለው ፈጥኖ ደራሽ ሚሊሻ በኃያሉ ጄኔራል እና የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራ ነው። የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን ደግሞ የአገሪቱን ጦር ኃይል ይመራሉ።

ሱዳንን ወደ ሲቪል መንግሥት ለማሸጋገር የቀረበው ዕቅድ የአርኤስኤፍ ኃይሎችን ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር በማዋሃድ የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከስምምነት ሳይደረስበት ቆይቷል።

አርኤስኤፍ ውህደቱ በአስር ዓመታት እንዲዘገይ ፍላጎት ያለው ሲሆን፣ የአገሪቱ ሠራዊት ግን በሁለት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈልጋል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ውጥረት በተካረረበት ጊዜ አርኤስኤፍ ኃይሎቹን ሐሙስ ዕለት ሜሮዌ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ኃይሎች አቅራቢያ አሰማርቷል።

ጄኔራል ቡርሃን በሚቋቋመው ሲቪል መንግሥት ውስጥ የሚመሠረተውን የተዋሃደ የአገሪቱን ጦር ማን መምራት አለበት በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ከጄኔራል ዳጋሎ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።

ምዕራባውያን እና የአካባቢው አገራት መሪዎች ሁለቱ ጄኔራሎች የተፈጠረውን ውጥረት አርግበው ሲቪል መንግሥት ለመመስረት ወደ ሚያስችለው ንግግር እንዲመለሱ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

አርብ ዕለትም የተፈጠረው ችግር መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል የሚያሳዩ መልክቶች ነበሩ።

ለሦስት አስር ዓመታት ያህል ሱዳንን ያስተዳደሩት ኦማር ሐሰን አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ሲቪሎች እና ወታደሮች ሥልጣን ተጋርተው አገሪቱን ለምርጫ እንደሚያዘጋጁ ተስማምተው ነበር።

ነገር ግን ከአንድ ዓመት በፊት ጄኔራል ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት አድርገው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመራው ሲቪል መንግሥት ፍጻሜ ሆኖ ሱዳን በወታደራዊ መሪዎች ስር ትገኛለች።

ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት እና አስተዳደር የሚቃወሙ አፍቃሪ ዲሞክራሲ ሱዳናውያን በመደበኛ ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።

Exit mobile version