ETHIO12.COM

በበይነ መረብ የሚሸጡ የመዋቢያ ምርቶች ጥራት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

በኢትዮጵያ በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሸጡ የመዋቢያ ምርቶችና መድኃኒቶች ጥራት እና ደህንነት ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የቁጥጥር ቡድን መሪ ሳሙኤል ማሪ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ በበይነ መረብ (ኦንላይን) የሚሸጡ ምርቶች ጥራት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጸው የምርቶቹ ሽያጭም ህጋዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የመድኃኒቱም ሆነ ኮስሞቲክስ ደህንነት፣ ፈዋሽነት ወይም ውጤታማነት ላይ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል የኢንተርኔት ሽያጭ እንደሚከለከልና ከህግ ማዕቀፍ አኳያ ተቀባይነት እንደሌላቸው አመላክተዋል፡፡

የመድኃኒቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት ህጋዊ ሂደት በግልጽ የተቀመጠ እንደሆነ ሁሉ፤ የመዋቢያ ምርቶችም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበት ሥርዓት ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ህጋዊነት ባልተከተለ መልኩ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ምርቶች ስለምርቱ ገላጭ መረጃዎች እና ሌሎች አስፈላጊ ማሳሰቢያ እና አጠቃቀም መረጃዎች የሏቸውም ያሉት ባለሙያው በመሆኑም ምርቶቹ በማህበረሰቡ ላይ ከባድ የጤና ችግር ከመፍጠራቸው ባሻገር ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ሻጮቹን በህግ ለመጠየቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በኦንላይን የሚሸጡ ምርቶች ቋሚ አድራሻ እና ምርቱን ተከታትሎ ማስረጃ ለመሰብሰብም አዳጋች እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የኢንተርኔት ሽያጭን አሳሳቢ ያደረገው መድኃኒቶችም ጭምር እንደመዋቢያ ምርትነት በኢንተርኔት ለሽያጭ እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም በኦንላይን ከሚሸጡ አጠራጣሪ እና ጎጅ ምርቶች ተጠቃሚዎች የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በአንዳንድ መዋቢያ ምርቶች እና መድኃኒቶች መካከል ያለው ልዩነቱ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ተጠቃሚዎች ስለሚገዟቸው ምርቶች ምንነት በቂ እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባና አጠራጣሪ ምርቶች ሲኖሩ ለባለስልጣኑ መጠቆም እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ባለስልጣኑ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝና ለጥቆማ የሚያገለግል ነፃ የስልክ መስመር እንዳዘጋጀ እንዲሁም ከህግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ  ጠቁመዋል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ ዋልታ ኢንፎርሜሽን

Exit mobile version