በመግቢያና መውጫ ኬላ ቁጥጥር በማድረግ በተገኙ ግኝቶች መሰረት 238 ሚሊዮን ብር የሚገመት ህገ-ወጥ የምግብ፣ የመድኃኒትና የመዋቢያ ምርቶች ወደ ህብረተሰቡ እንዳይሰረጩ ተደረገ፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የሞጆ መግቢያና መዉጫ ኬላ ከሞጆ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት ግምታቸዉ 238 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ህገ-ወጥ የምግብ፣ የመድኃኒትና የመዋቢያ ምርቶች በቁጥጥር የተገኙ ሲሆን ወደ ህብረተሰቡ እንዳይሰራጩ መደረጉ ታዉቋል፡፡

የባለስልጣን መ/ቤቱ የሞጆ መግቢያና መዉጫ ኬላ አስተባባሪ አቶ ቦንሳ ጃለታ እንደገለጹት በሞጆ ወደብና ተርሚናል በተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የምግብ፣ የመድኃኒትና የዉበት መጠበቂያ ምርቶች ተወርሰዋል።

ባለፋት አምስት ወራት በተደረጉ የቁጥጥር ስራዎችም ግምታቸዉ 238 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ህገ-ወጥ የምግብ፣ የመድኃኒትና የመዋቢያ ምርቶች ወደ ህብረተሰቡ እንዳይሰራጩ በማድረግ በጤና ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ህገ-ወጥ የምግብ፣ የመድኃኒትና የመዋቢያ ምርቶች፤የመጠቀሚያ ጊዜያቸዉ ያለፈ፣ የገላጭ ጹሑፍ ችግር ያለባቸዉ፣ የአስተሻሸግ ችግር ያለባቸዉ፣ በላቦራቶሪ ምርመራ የወደቁ፣ በአጓጓዝ ወቅት የተበላሹ አንዲሁም አስመስሎ የተሰሩ ምርቶች መሆናቸዉን አቶ ቦንሳ ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት143 ሚሊዮን ብር የሚገመት ህገወጥ የምግብ ምርት፣ 25 ሚሊዮን ብር የሚገመት ህገወጥ የመድኃኒት ምርትና 70 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመዋቢያ ምርቶች በአጠቃላይ 238 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ህገ-ወጥ የምግብ፣ የመድኃኒትና የመዋቢያ ምርቶች በህብረተሰብ ጤና ችግር እንዳያደርሱ በመግቢያና መውጫ ኬላው መቆጣጠር ተችሏል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህብረተሰቡ ጥራታቸው እና ደህንነታቸው የተጠበቁ የምግብና የጤና ግብዓት ምርቶች እንዲደርሰው በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና መግቢያና መውጫ ኬላዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቁጥጥር ስራውን በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። Via (ኢ.ፕ.ድ)

Leave a Reply