Site icon ETHIO12.COM

ሀሰተኛ ደረሰኝ በማተም እና በማሰራጨት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በገቢዎች ሚኒስቴር የአዳማ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በከተማዋ ሀሰተኛ ደረሰኝ በማተም በማሰራጨት በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ግለሰቦችን በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ደርቤ ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦቹ በከተማዋ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው በተሰማሩ ድርጅቶችና እና ሆቴሎች የንግድ ስም በመጠቀም ግብይት ባልተፈፀመበት ግብይት እንደተፈፀመ አስመስለው ሀሰተኛ ደረሰኝ በማተም እና በመሸጥ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን አክለው ገልጸዋል፡፡

በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ለሁለት ወራት ያክል በተደረገ ክትትል በተለያዩ 35 በሚሆኑ ህጋዊ ድርጅቶች ስም የታተመ ሀሰተኛ ደረሰኝ የተያዘ ሲሆን ዋነኛ የድርጊቱ ተጠርጣሪዎችን እጅ ከፈንጅ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡ በዚህም ደራ ማተሚያ ቤት በሚል የድርጅት ስም ሕገ-ወጥ ደረሰኞችን እና ሌሎች ሰነዶችን ሲያዘጋጅ እና ሲያሰራጭ የነበረ ግለሰብ ከግብረአበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው ህገ-ወጥ ግለሰቦች መሰብሰብ ያለበትን ግብር በመሰወርና ሀገር ልታገኝ የነበረውን ገቢ ከማሳጣት ባለፈ ኢኮኖሚው ላይ ቀውስ በመፍጠር በሀገር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ሲያደርሱ መቆየታቸውንም አብራርተዋል፡፡

በተለይም ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ከሀሰተኛ የወጪ እና የገቢ ደረሰኝ ህትመት እና ስርጭት ባለፈ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የነዋሪነት መታወቂያና ሌሎች ሀሰተኛ ሰነዶችንም ጭምር በማዘጋጀት ከገቢው ባሻገር ዘርፈ ብዙ ለደህንነት ስጋት የሚሆኑ ወንጀሎችን ሲሰሩ መቆየታቸው ተደርሶበታል፡፡

ህጋዊ የንግድ ፈቃድ በማውጣት እየሰሩ ያሉ ግለሰቦች ወይም የድርጊቱ ሰለባዎች ውስጥ የወሰን ማተሚያ ቤት እና ግሬስ ሆቴል ባለቤቶች በበኩላቸው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ባደረገው ክትትል ህገ-ወጥ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ማዋሉ በድርጅታቸው ላይ ሊደርስ የነበረውን ተጨማሪ ኪሳራ ማስቀረት መቻሉን አንስተዋል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱ ወንጀል እና የሀገር ክህደት ጭምር በመሆኑ አስተማሪ ቅጣት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

/የገቢዎች ሚኒስቴር

Exit mobile version