Site icon ETHIO12.COM

የመጥፋት ውሳኔ በኢትዮጵያ ህግ “የጠፋው ሰው ልክ እንደሞተ ይቆጠራል”

የሰው ልጅ በአንድም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ከሚኖርበት ስፍራ በራሱ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የሚሄድበት እና በዛም አጋጣሚ በሚፈልጉት ሰዎች ይኑር ይሙት የማያውቁበት አጋጣሚ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተሰቡ እና በስሩ የሚገኙ ንብረቶች ለማን እንዴት እንደሚደረግ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በዚህ አጭር ርእስ ስለመጥፋት ውሳኔ ትርጓሜ፣ የመጥፋት ውሳኔ በማን እና እንዴት እንደሚሰጥት፣ የመጥፋት ውሳኔ የሚያስከትለው ውጤት እንዲሁም የመጥፋት ውሣኔን ውጤት ቀሪ የሚያደርጉ ምክንያቶች እንዳስሳለን፡፡

አንድ ሰው ጠፋ የሚባለው መቼ ነው

በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 154(1) መሰረት አንድ ሰው ጠፋ የሚባለው ከጠፋ እና ከሁለት አመት ወዲህ ወሬው ያልተሰማ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥ በማናቸውም ባለጉዳይ ሊጠየቅ ይችላል፡፡

የመጥፋት ውሳኔ በማን እና እንዴት ይሰጣል

የመጥፋት ውሳኔ የሚሰጠው የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥበት የተጠየቀበት ሰው ዋና መኖሪያ አድርጎ በሚኖርበት ቦታ የሚገኝ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ማንኛውም ባለጉዳይ የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሲያቀርብ ማስታወቂያ ይወጣል፡፡ ማስታወቂያውም ፍርድ ቤቱ በሚወስነው ሁኔታ እና የጠፋው ሰው በመጨረሻ ዋና መኖሪያነት ይኖርበት በነበረበት ቦታ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ማስታወቂያው ይጠቅማል ብሎ በሚያምንበት ቦታ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠፋው ሰው መሞት በሚመስል መልኩ መጥፋቱ ከተሰማው የመጥፋት ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ውሳኔውን በሚሰጡበት ወቅት ግን የነገሩን አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ጠባይ እና መጥፋቱ የተገመተው ሰው ለንብረቱ አስተዳዳሪነት ወኪል ማስቀመጡ እንዲሁም ግለሰቡ ወሬው እንዳይሰማ የከለከሉ ምክንቶችን መመርመር ይጠበቅበታል፡፡ የሚሰጠው የመጥፋት ውሳኔ እስከ 1 አመት ማቆየት ወይም ወይም ስለ መጥፋቱ የሚሰጠው ፍርድ ውጤቱ የሚኖረው ውሳኔው ከተሰጠ ከ1 አመት በኋላ እንዲሆን መወሰን ይችላል፡፡ በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ውሳኔ የጠፋው ሰው የመጨረሻ ወሬዎች የተሰሙበትን ቀን መወሰን ይችላሉ፡፡

የመጥፋት ውሳኔ የሚያስከትለው ውጤት

የመጥፋት ውሳኔ በውርስ እና በጋብቻ ላይ ውጤትን የሚያስከትል ነው፡፡ የመጥፋት ውሳኔን ዳኞች ሲወስኑ ጠፋ የተባለው ሰው የሞተ የሚመስልን ማስረጃ ካረጋገጡ በኋላ በመሆኑ የጠፋው ሰው ልክ እንደሞተ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ጋብቻ ለሚፈርስባቸው ምክንያቶች አንዱ በሞት ምክንያት ስለሆነ እና የመጥፋት ውሳኔም የጠፋው ሰው እንደሞተ የሚቆጠር በመሆኑ ጋብቻ ይፈርሳል፡፡ ስለውርስ የሚደነግገው አንቀፅ ስር ውርስ የሚከፈተው አውራሽ ከሞተ በኋላ በመሆኑ የመጥፋት ውሳኔም እንዲሁ የጠፋውን ሰው እንደሞተ ስለሚያስቆጥረው ውርሱ ይከፈታል፡፡

 ጋብቻን በተመለከተ፡- የጠፋ ሰው ጋብቻ የሚፈርሰው መጥፋት ማስታወቂያ ፍርድ የመጨረሻ በሆነበት ቀን ነው ሲል የፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ 183 ይደነግጋል፡፡ የመጨረሻዎቹ ወሬዎች ከተሰሙበት በኋላ የተፈፀሙት የወንዱ ወይም የሴቲቱ ጋብቻ ጠፋ የተባለው ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊቃወም እንደማይችል አንቀፅ 183(2) ያስረዳል፡፡ ነገር ግን የመጥፋት ማስታወቂያ ክስ በተጀመረበት ቀን ጠፋ የተባለው ሰው በህይወት መኖሩን ዓቃቤ ህግ ካረጋገጠ በፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ አንቀፅ 183(3) መሰረት መቃወሚያ ሊያቀርብ ይችላል፡፡

 ውርስን በተመለከተ፡- ጠፋ የተባለው ሰው የመጨረሻዎቹ ወሬዎች ከደረሱ በኋላ በህይወት ቢኖር ኖሮ እርሱ ሊወርስ በሚችለው የአወራረስ ስርአት መሰረት ለእርሱ ሊደርስ የሚቸለውን ድርሻ ግምት ውስጥ ሳይገባ የውርስ ስርአቱ ይፈፀማል፡፡ ከፍትሀብሔር ህግ አንቀፅ 184(1) ሀሳብ የምንረዳው ነገር ጠፋ የተባለው ሰው ምንም እንኳን በቦታው ባይኖርም የውርስ ድርሻው ይቀመጥለታል ማለት ነው፡፡ ለዚህም አብሮ ወራሽ የሆኑት ጠፋ ለተባለው ሰው ድርሻ መብቶች መድህን እንዲያሲዙ ፍርድ ቤት ሊያዛቸው ይችላል፡፡ የጠፋ ሰው ላይ እዳ፣ ውርስ የመሳሰሉት መብቶች ያላቸው እንደሆነ መጥፋትን በሚወስነው ፍርድ መጨረሻ ከሆነበት ቀን አንስቶ እንደሞተ ተቆጥሮ የመብቶቹ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በአንቀፅ 185(1) ስር ተደንግጓል፡፡ ጠፋ የተባለው ሰው መብት ተካፋይ ብቻ ሳይሆን የሚያወርሰው ነገርም ሊኖረው ሲችል ጠፋ የተባለው ሰው ኑዛዜ ያለው እንደሆነ ውርሱ የሚከፈተው የመጨረሻ ወሬው በተሰማበት ቀን ባለጉዳዮቹ (ወራሾቹ) በሚያነሱት ጥያቄ መሰረት ኑዛዜ ይፈሳል (ያነገራል)፡፡ ጠፋ የተባለውን ሰው የውርስ ንብረቶችን አጠቃቀም በተመለከተ እንደ መልካም ቤተዘመድ አባት ሆኖ ጠፋ የተባለው ሰው ሊመለስ ቢችል እንኳን በሚል ተመላሽ ስለሚሆን የንብረቶቹን ዋስ እንዲጠራ ወይም ማረጋገጫ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቶች ሊያስገድድ ይችላል፡፡ የጠፋውን ሰው ንብረት ባለይዞታ የሆነ ሰው በሶስት ወር ውስጥ የተቀበላቸውን ንብረቶች በስራ ላይ ማዋል እንዳለበት እንደተጠበቀ ሆኖ ንብረቱ የጠፋውን ሰው ልጅ ለማቋቋም ከሆነ በስጦታ ማስተላለፍ ይቻላል፡፡

የመጥፋት ውሳኔ የተሰጠበት ሰውን ንብረት በማንኛውም ሁኔታ በስጦታ ማስተላለፍ እንደማይቻል ተደንግጓል፡፡

የመጥፋት ውሣኔን ውጤት ቀሪ የሚያደርጉ ምክንያቶች
ጠፍቷል የተባለው ሰው መመለስ(የመጣ) እንደሆነ፣
ጠፍቷል የሚባለው የፍርድ ማስታወቂያ ከወጣ በኋላ በህይወት ለመኖሩ አስረጂ የተገኘ እንደሆነ፣
የመጨረሻ ወሬዎቹ የተሰሙበት ተብሎ ከተወሰነው ግዜ በሌላ ጊዜ መሞቱ አስረጂ የተገኘ እንደሆነ መሆኑን በፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ 170 ስር ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡
ጠፋ የተባለው ሰው ስለመመለስ
በፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ 171 መሠረት ጠፋ የተባለው ሰው በተመለሰ (በመጣ) ጊዜ ንብረቶቹን በሚገኙበት አኳኋን መልሶ የመረከብ እንደዚሁም የተሸጡትን ንብረቶች ዋጋ የማግኘት መብት እንዳለው በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ይህን የህግ ሀሳብ በሚያስረግጥ ሁኔታ ጠፋ የተባለው ሰው ንብረት መሸጡ ከተረጋገጠ ከተጠቀሰው ድንጋጌ አኳያ ሊረከብ የሚገባው የተሸጠውን ንብረት ሣይሆን የሽያጩን ዋጋ ነው በማለት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 30298 አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ ነገር ግን በተንኮል እና በክፉ ልቦና ካልሆነ በስተቀር ጠፋ የተባለውን ሰው ንብረት ገቢዎች በይዞታቸው ስር አድርገው ሲጠቀሙ የነበሩትን ገቢ እንዲመልሱ አይጠየቁም፡፡

በአጠቃላይ በአንድ ሰው በመጥፋቱ ምክንያት በቤተሰብ እና በንብረቶች ላይ ውጤት ያለው በመሆኑ በዳኞች የመጣፋተ ውሳኔ ሲተላላፍ ከፍትሀብሔር ህጉ መንፈስ አንፃር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ እንዲሁም ጠፋ የተባለው ሰው ሊመለስ የሚችልበት አግባብ ስለሚኖር ለንብረቶቹ ዋስትና ማስያዝ ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ስለዚህ አንድ ሰው ከዋና መኖሪያ ከጠፋ ማንም ሰው የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥ ለማመልከት ይችላል፡፡ የመጥፋት ውሳኔን ለመስጠት ዳኞች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ከህጉ የምንረዳው ነው፡፡ ለዚህም የሰውየውን መጥፋት ለመረዳት ዳኞች ከዓቃቤ ህግ ጋር በመተባበር በማናቸውም ቦታ ይልቁንም የጠፋው ሰው የመጨረሻ ይኖርበት ከነበረው ቦታ እና በመጨረሻ መኖሩ የታየበት ቦታ ጠፋ የሚባለው ሰው ስለመኖሩ ምርመራ እንዲደረግ በማዘዝ እንደሆነ የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 156 ስር ተደንግጓ እናገኘዋለን፡፡ ይኸውም ዓቃቤ ህግ ስለመጥፋቱ የቀረበውን ማመልከቻ እና ማስረጃዎች ፍርድ ቤቱ ወደ ትክክለኛ ውሳኔ ለመድረስ የሚያስችለውን ማስረጃ ዓቃቤ ህጉን ተቃርኖ የበለጠ እንዲረጋገጥ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ዳኞች የጠፋው ሰው አጠፋፍ ‹መሞት የሚመስል› መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ መጥፋቱን ከተረዱት በፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ 157 መሰረት የመጥፋት ውሳኔ የመጨረሻ ወሬዎቹን የተሰማበትን ቀን በመጥቀስ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ በሌላ በኩል ዳኞቹ ያገኙት ማስረጃ ወደሞት የሚያመዝን መስሎ ከታያቸው ‹የሞት ማስታወቂያ› ፍርድ ይሠጣሉ ሲል የፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ 157(1) ደንግጓል፡፡ ዳኞች እንደነገሩ ሁኔታ የመጥፋት ውሳኔውን ወይም የመጥፋት ውሳኔ ማስታወቂያን ለአንድ አመት መቅጠር የሚችሉ ሲሆን ነገር ግን የመጥፋት ውሳኔው ከተጠየቀ ከአንድ አመት በኋላ ወይም ሰውየው ከጠፋ አምስት አመት በኋላ የመጥፋት ውሳኔ መሰጠት አለበት፡፡

በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Exit mobile version