Site icon ETHIO12.COM

“እስኪ ማነው እሱ?”

ማነው እስኪ የእንብቆቅላ ህጻናቱን ጉንጭ በአባታዊ ፍቅር መሳም ብርቅ ሆኖበት ሳለ ናፍቆቱን ዋጥ አድርጎ ከልጆቼ ሀገሬ ትበልጥብኛለች የሚል መንፈሰ ብርቱ?

እኮ ማነው? በአእምሮው የገነነችበት የኔ የሚላት በፍቅር የተጣመረችው ሄዋናዊ አጋሩን የ “ናልኝ እንጂ መቼ ነው የምትመጣው? በጣም ናፍቀኸኛል” የሚልን የነጋ ጠባ ጥሪ ችሎ የሀገሩ ኢትዮጵያን ፍቅር አልቆ የታገሰ?

ኸረ ማነው? የነገ ኑሮና ህይወቱን አሳሳቢነት ቸል ብሎ የአፍላ ወጣትነትን ውብ ጊዜ ሰውቶ፣ሙሉ ጊዜውን ዕውቀቱንና ጉልበቱን አልፎም ነፍሱን ለህዝቤ በሚል ከብረት በጠነከረ ዲሲፕሊን በሞያዊ ብቃት ያለውን ሁሉ ለሀገሩ አሳልፎ የሰጠ?

ከግል ደህንነቱ በላይ የሀገሩ ሰላም ውሎ ማደር በእጅጉ የሚያስደስተው ቆይ ማነው ትላላችሁ?

የቆላ ሃሩር ቢያግለው፣የደጋ ውርጭ ቢያንዘፈዝፈው፣ በጋ ቢሆን ክረምት ወቅት ሳይመርጥ ከሰማይ ጠቀስ ተራራ እስከ ጭው ያለ ጸሃይ ንዳድ ያንቀለቀለው ሜዳ፣ጥቅጥቅ ካለ ጫካ… ብቻ የኢትዮጵያችንን መልክዓ-ምድርና አየር ጸባይ ሁሉ ድካምን ፊት ነስቶ ላብ ወዙን ማንጠፍጠፍ የማይሰለቸው?

በጣራ አልባ ሰማይ ስር ማደር ግድ ሳይለው ኮከብን ሳይሆን የኢትዮጵያን መጻኢ ተስፋና የህዝቡን መልካም ወደፊታዊ ዕድል እየቆጠረ ስለ ሀገሩ ከራስ ጋር በመጨዋወት ፍገጋ ችግር መከራን የሚዘነጋ ጽኑ ማነው?

አእምሮ ወ ልቦናው ሳያቋርጥ ለሀገር በማሰብ ዕምነት ተሞልቶ ስለሰላም ያለእረፍት በመስራት ትጋት የሚባትል ራሱን ትቶ ስለሌሎች ኗሪው ማን ይመስላችሁዋል?

ይህ የጽናት፣የጀግንነት፣የአደራ አክባሪነትና የቃል ታማኝነት ተምሳሌት፤ የሀገሬ የሀገርሽ የሀገራችን ሰላም ዋስ ጠበቃ፣የህዝቡ ደህንነትና እፎይታ መድህን፣ለኢትዮጵያችን መጽናት ያለመታከት ዘብ ቋሚ ጀግናው ወታደር ነው።የእያንዳንዱ ወታደር ጽናትና ሞያዊ ብቃትም ተዓምራዊ ውህደትን ፈጥሮ ተቋማዊ ውብ ቀለምን የፈጠረ ሃያል የሀገር አቅምን ሰርቶ ይገኛል።

እግረኛ ኮማንዶና ሜካናይዝዱ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በምድር እያካለለ፣አየር ሃይሉ “ሰማዩም የኛ ነው” በሚል መርህ በየጊዜው እየዳበረ በቀጠለ ቴክኖሎጂ የአየር ክልላችንን እያስከበረ፣ባህር ሃይሉ ለነገ በሰነቀው ቀጠናዊ ሚናን በምርጥ ብቃት የመወጣት አቅሙን በውሃ አካላት እየገነባ፣የሳይበር ሃይሉ ዘመን በዋጅ ችሎታና ብቃት የተወዳዳሪነት እውቀቱን እያነጸ በአስገራሚ አገነባብ ቀጥለው የሀገርና ህዝብ አለኝታነታቸውን አስመንድገዋል።

በሳይንስና ጥበብ የደረጀው ተቋማዊ የአመራር ጠገጋዊ ቅንጁቱም እያንዳንዱን ወታደር ባናበበ ውህደት ግሩም ድንቅ አቅም ተበጅቷል።

የመከላከያ ተቋም የገዘፈና የደረጀ ሀገራዊ አስተማማኝ ሃይልነት ውህድ ድንቅ አቅም የተቀመረው ከማቴሪያል ባሻገር በእያንዳንዱ ወታደር ጽናት፣ዲሲፕሊን፣ሀገራዊና ህዝባዊ ፍቅር፣አስደናቂ የአሸናፊነት መንፈስ፣ሞያዊ እውቀትና ክህሎት፣ጀግንነትና ልበ-ሙሉነት ወደ አሃዳዊ የጋራ አቅምና ብቃት ተዳምረው ነው።

“እኔ እንዲህ አስባለሁ” በሁሉም የሙያ መስኮችና ተቋማት የተደራጁ ከታችኛው እስከ ከፍተኛው ሞያዊ እርከን የሚገኙ ግለሰቦች ልክ እንደ መከላከያ ተቋም እያንዳንዱ ወታደር “ከራስ በፊት ለሀገርና ህዝብ” ብሎ በጽናት፣በታማኝነትና በቅንነት የበኩሉን ቢወጣ የሀገራችን ከፍታና የሚገባት የክብር ስፍራ ላይ የመገኘት ጊዜዋ ፈጣን እጅግ በጣም ቅርብ የሚሆን አይመስላችሁም?

ግን እንደ ወታደር ለሌሎች የመኖር መሰጠትን ይጠይቃል።

“ክብር ለሰላማችን ዘብ ጀግናው ወታደር”

አስቻለው ሌንጫ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚያዚያ 22 ቀን 2015

Exit mobile version