Site icon ETHIO12.COM

ሩዋንዳውያን የሆነው ሁሉ ከመሆኑ በፊት እኛን ይመስሉ ነበር!

ስላለፉት ትርክቶች ሂሳብ ማወራረድም ሆነ የታሪክ አርትኦት መስራት የኛ አቅም እና ሃላፊነት አይደለም፡፡ ከትላንታችን ነቀፋ ይልቅ የነጋችን ተስፋ እጅጉን ይልቃል! እጅጉን ይደምቃል!

ይህች ኪጋሊ ናት! By Adisu Arega kitessa

ኪጋሊ ለአዲስ አበባ የምታጫውተው!… አጫውታም የምታስጠነቅቀው! … አስጠንቅቃም ሰከን ብሎ ያለማሰብ ፣ ያለመወያት ፣ ያለመነጋገር እና ያለመደማመጥ ይዞባት የመጣው ብዙ የሰቆቃ ታሪክ እንዳላት በግልጽ የምታሳይባቸው በርካታ ህልው ማሳያዎች አሏት ::

ኪጋሊ እና ሌሎች የሩዋንዳ ከተማዎች በተለይም ለፅንፈኝነት ጠንሳሽ እና ጠማቂዎቹ ‹‹የስልጣን ልቀቅ- ስልጣን ልንጠቅ›› አቀንቃኝ ቡድኖች መማር እስከፈለጉና እስከቻሉ ድረስ ከሩዋንዳ ሰማይ ስር ስክነትን ፣ መደማመጥን ፣ መወያየትን እና መከባበርን የሚያስተምሩባቸው እልፍ ዘግናኝ ታሪኮች አሏቸው!

የሩዋንዳ ዘግናኝ የመተላለቅ ታሪክ መነሻ ቅኝ ገዢዎች ከፈጠሩት ትርክት በላይ የሀገሬው የፖለቲካ ሊሂቃን የወድማማች ህዝቦችን ብዝሃነት ወደ ከረረ ልዩነት ለጥጠው አንዱ ከሌላው የሚበልጥ፣ አንደኛው ወራሪ መጤ፣ ገፊ ፣ዘራፊ፣ ተረኛ ሌላኛውን ደግሞ ባለ በኩር ትርክትና ሀገር አቅኚ ግን ደግሞ ተገፊ፣ ተጨቋኝ አድርገው በመሳል ለፖለቲካ ስልጣን መንገድ ማሰለጫነት ለመጠቀም የሞከሩበት ቀሽም ስሌት ነው።

ሚያዚያ 1987 ዓ.ም ከወራቱ ቀናት በአንዱ ከሩዋንዳ ሰማይ ስር ማረፊያዋን ኪጋሊ አድርጋ ትበር የነበረችው ሄሊኮፍተር ከምድር በተወነጨፈባት እሳት ወደ እቶን አመድነት እየተቀየረች ወደ ምድር ስትምዘገዘግ ያስተዋለ ማንኛውም ሰው ሄሊኮፍተሯ በውስጧ ስለያዘቻቸው ሰዎች ሕይወት ማሰቡ እና መጨነቁ አይቀሬ ነው!

በእርግጥም ሄሊኮፍተሯ ምድር ደርሳ ራሷን እና በውስጧ ያሳፈረቻቸውን ሰዎች ብቻ አልነበረም… አመድ – ትቢያ – አፈር ለማድረግ ቁልቁል የተጣደፈችው… ፤ ይልቁንስ የሩዋንዳን እና የሩዋንዳዊያንን ክብር፣ አብሮነት ፣ ከፍታ እና ሀገራዊ ስንስልም ነበር ከሄሊኮፍተሯ ጋር ቁልቁል የወረዱት!
የወቅቱን የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ጁቬናል ሀቢያሪማናን ፣ የቡሩንዲውን ፕሬዝደንት ሳይፕሪን ንታሪያማን እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን አሳፍራ ኪጋሊን ታነፈንፍ የነበረችው ሄሊኮፍተር ከምድር በተተኮሰ ሚሳኤል ተመታች …. ከሄሊኮፍተሯ ጋር ፍቅር ተመታ! ሰላም ተመታ! አብሮነት ተመታ! ሁቱ እና ቱትሲን ያስተሳሰረው ፣ያጋመደው እና ያቻቻለው የመከባበር ድልድይም በእኩያን በተተኮሰበት አረር ፈረሰ!

የወቅቱን የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ጁቬናል ሀቢያሪማናን እና ወዳጆቻቸውን ያሳፈረችው ሄሊኮፍተር ከመኖር ወደ አለመኖር ስትለወጥ ፤ ያን ግዜ የእልቂት ደመና እንደ ሲላ አሞራ ያሩዋንዳዊያንን የጠራ ሰማይ ይዞረው ጀመር፡፡

ይህ ታሪክ ለሩዋንዳዊያን እውነት ለእኛ ለትዮጵያዊያን እና ለመላው የዓለም ህዝቦች ደግሞ ትምህርት ሆኖ የታሪክ ሰሌዳ ላይ ለዘላለም ተክትቦ ይኖራል።

የሀገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል !

አብሮነት ፣ ትህትና ፣ መከባበር እና አንተ ትብስ እኔ እብስ ይሉት የኑሮ ይትባህል በጸኑ በሚሰበክባት፤ ኣዛን እና ቅዳሴ ከንጋት እስከ ንጋት ሰማይዋን በሚሸፍንባት – ምድሯን በሚከድንባት ውብ ሀገር ውስጥ ትዕቢት ፣ እብሪት ፣ ትምክህት ፣ ራስ ወዳድነት እና እኔ እበልጣለሁ ባይነት እዚህም እዚያም ሲበቅል ፣ ሲያቆጠቁጥ እና ክፋት ሲያፈራ አያለሁ፡፡

እናም የሀገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል!

በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ ብዙ የመገንቢያ እና የማሰቢያ አማራጮች እንዳሉ እሙን ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዝሃነት ባህሪያቸው ላይደለ ይልቁኑስ ተፈጥሯቸው ለሆነ ሀገራት ደግሞ የአግላይነትም ሆነ የጠቅላይነት አማራጭ በፍጹ የሚመከር አይደለም፡፡

የብዙ ሀገራትን የፖለቲካ መስመር እና አንደ ሀገር የቆሙበትን ዋልታ እና ማገር ስንመረምር በእርግጥም በአንድ ቋንቋ፣ በአንድ ገዢ ትርክት፣ በአንድ ባህል እና በአንድ የፖለቲካ ርዕዮት መሰረታቸውን ለመቃኘት የሞከሩ እንዳሉ እንረዳለን፡፡ በውጤቱም የሰመረላቸው የመኖራቸውን ያህል ያፈረሳቸውንም ሀገራት እዚህም እዚያም እናገኛለን፡፡

የአንድን ሀገርን ህዝብ በአንድ ሁለንተናዊ ክበብ ውስጥ ቀንፎ አንድ ሀገር ለመገንባት የሚደረግ ጥረት በእኛ ሀገርም ለረዥም ግዚያት የተሞከረ ቢሆንም ብዙ ነጻ አውጪ ግንባሮችን ከመፍጠር የዘለለ ብዙ ውጤት እንዳላስገኘ ከእኛ የሚቀድም እማኝ በፍጹም አይገኝም፡፡

አሁን የጊሶዚ የኪጋሊ የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ሙዝየም ምድረ ግቢ ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ሊታረቁ በሚችሉ ልዩነቶች ዘግናኝ በሆነ መተላለቅ እስከወዲያኛው ባሸለቡ ዕልፍ አዕላፍ ነፍሳት መንፈስ ተከብቤ ሩዋንዳን እያየሁ ሀገሬን አስባለሁ፡፡ በአንድ በኩል ያሰብኩትን ላለማሰብ ፤በሀገሬ ቢሆንስ? በሚል ዘግናኝ መንፈስ ላለመተብተብ እና ይህንን ሟርት አሻግሬ ማየትን ላለመድፈር እጥራለሁ፡፡

ቢሆንም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ በእኔ እበልጣለሁ ድርቅታ ዘገር የሚነቀንቁ ጀብደኞችን እያሰብኩኝ አብዝቼ አስባለሁ፡፡

በሩዋንዳ ሁቱዎችም ቱትሲዎችም የሚበልጡባት ፣የሚያብቡባት ፣ የሚፈኩባት ሩዋንዳን ያለ ምንም እልቂት እና ፍጅት መፍጠር እየቻሉ ቃታ ስለተሳሳቡት ፤ ሳንጃ ስለተሞሻለቁት ሰይፍ ስለተማዘዙት አፍሪካዊያን ወንድሞቼ እያነባሁ የሀገሬን እጣ ፈንታ አሻግሬ እማትራለሁ፡፡

በእርግጥም ስለ ህዝቤ እና ስለ ሀገሬ እብሰለሰላለሁ !
የሆነው ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሩዋንዳ ላይ የሆነው ሁሉ አልሆነም ነበር! ፤ ካለመሆን እስከ መሆን ያለው እርቀት እጅጉን ቅርብ እንደሆነ ይህ ሙዚየም ምስክር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ምስቅልቅ እና ውል አልባ ውጥንቅጥ መነሻው እና መድረሻው ‹‹የኔ ገዢ ትርክት አንተንም በግድ ይግዛህ!›› የሚል ፉክክር እንደሆነ ግልጽ ነው ፡፡

ሩዋንዳዊያን የሆነው ሁሉ ከመሆኑ በፊት ጥቂት ቆም ብለው የሚያስቡበት ፣የሚነጋገሩበት ፣ የሚወያዩበት እና የሚበጀውን የሚያነጥሩበት እድል ፈጥረው ቢሆን ኖሮ ሰማያቸውን የዞረውን የሞት አሞራ ከሰማያቸው ላይ እንደ ጉም ማብነን በቻሉ ነበር- ግን አልሆነም!

ታላቂቷ አፍሪካዊት ሀገር ሩዋንዳ ልጆቿን ከበላው የግብዝነት መንፈስ እና በምድሯ ካከማቸቻቸው ለሚሊዮን ጥቂት ፈሪ ከሆኑ አጽሞች ጋር ቁጭትን አዝላ እየተብሰለሰለች፤ በእሷ የሆነው በሌሎች እንዳይሆን ከእኔ ተማሩ ትላለች!
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በ100 ቀናት አካባቢ ብቻ የቱትሲአናሳ ጎሳ አባላት እንዲሁም አንዳንድ ለዘብተኛ የሁቱ እና የትዋ ጎሳ አባላት በታጠቁ ሁቱ ሚሊሻዎች ተጨፍጭፈዋል።

በወቅቱ በነበረው ጭፍጨፋ በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ በፍፁም ሊታወቅ አልቻለም፡፡
በብዙዎች ተቀባይነት ያለው መረጃ በሩዋንዳ ጄኖሳይድ በመቶ ቀናት ብቻ እስከ 800 ሺ የቱትሲ እንዲሁም ለዘብተኛ የሆኑ የሁቱ እና የትዋ ጎሳ አባላት መገደላቸውን የሚጠቁም ሲሆን ጥቂት የማይባሉ የመረጃ ምንጮች የሟቾቹን ቁጥር እስከ አንድ ሚሊዮን ያደርሱታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ 2004 የተመረቀው የጊሶዚ የኪጋሊ የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ሙዚየም ከ250,000 በላይ የቱትሲ እንዲሁም ለዘብተኛ የሆኑ የሁቱ እና የትዋ ጎሳ አባላት አጽም ያረፈበት የመቃብር ስፍራም ጭምር ነው። ይህ መታሰቢያ ሙዚየም በቱትሲዎች ላይ የተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዴት መልክ እንደያዘ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የታየውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመዘከር የሚረዳ ነው።
ይህን መሰል የመታሰቢያ ሙዚየም ከኪጋሊ በተጨማሪ በሌሎች የተለያዩ ቦታዎችም ይገኛሉ፡፡
የብዙዎቹ ተጎጂዎች ስሞች ገና አልተሰበሰበም ፤ አልተመዘገበም ! ብዙዎቹ በመቃብር ውስጥ ያረፉ ተጎጂዎች ስም እንኳ አይታወቅም!
ይህን ማየት ያማል !
ይህን መስማት ያሰቃያል!
ጸጸት ለይቅርታ እና ለእርምት መሰረት የሚሆን በጎ ነገር ቢሆንም ክፋቱ ግን የሆነው ነገር ከሆነ በኋላ የሚመጣ መሆኑ ነው ! ክፋቱ የጠፉ ነፍሶችን መመለስ አለመቻሉ ነው!

ሩዋንዳዊያን አሁን ላይ ሰላምና እርቅን አውርደዋል! የጠፋውን መመለስ ባለመቻላቸው ፣ መነጋገር ፣ መግባባት ፣ እኔ ትብስ አንተ ትብስ አለመባባላቸው በጸጸት እና በቁጭት አለንጋ ቢገርፋቸውም የዘር ማጥፋት ርዕዮተ ዓለምን ለመዋጋት ቆርጠዋል ተነስተዋል!

ብልሆች ከሌሎች ስህተት ተምረው ዛሬያቸውን እና ነጋቸውን የሚሰሩ ሲሆን ጅሎች ግን እስኪደርስባቸው ድረስ የሚሆንባቸውን ይጠብቃሉ፡፡
እኛ ከብልሆቹ ወገን ነን!
ከሩዋንዳ ብዙ – እጅግ በጣም ብዙ እንማራለን!
ሩዋንዳውያን ትላንት በሆነባቸው ነገር ሁሉ ዛሬ ይቆጫሉ ያዝናሉ ፤ የሆነው ሁሉ ባልሆንን ምን ነበር እያሉ ይብሰለሰላሉ፤ ነገር ግን በትላንትና ጠባሳ ቸው ላይ ተቸንክረው ዛሬያችንን ሳያበላሹ ሌላ ገጽ ላይ ተስለዋል ሌላ ገጽ ላይ ተኩለዋል፡፡

ታላቅ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ኢኮኖሚ ያላት ሩዋንዳን መፍጠር ችለዋል፤ ኪጋሊ በአፍሪካ ጽዱ ከተማ በመባል የዓለም ተምሳሌት መሆን የቻለች ለዙዎቹም ትምህርት የሆነች ከተማ ናት፡፡
በኢንደስትሪ ፣በኢንቨስትመንት ፣ በመሀበራዊ አገልግሎት ፣ በህዝቦቿ መቀራረብ እና ህብራዊነት ዓለም አይኖቹን ወደ ሩዋንዳ ያማትራል፡፡ ��
በሙዚየሙ ቅጥረ ግቢ ውስጥ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ከሰሜን ወደ ደቡብ ያልኩኝ የሩዋንዳን ዘግናኝም እልቂት አሻግሬ እያየሁ እብሰለሰላለሁ ፤ እተክዛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ለሩዋንዳ ያላትን አጋርነት እና በግዜ ያልተገደበ ወዳጅነት ለማሳየት ሩዋንዳ በተገኙበት ወቅት ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እስከ ተራው ህዝብ ድረስ ኢትዮጵያ ለሩዋንዳ የዋለችውን ውለታ ያሳየችውን አጋርነትና ወታደሮቿ ሩዋንዳ ከትመው የሰሩትን ጀብድ እያነሱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ያመሰግናሉ ያከብራሉ፡፡

ከፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ እስከ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ድረስ ሲያገኙኝ የሰጡኝ ፍቅር እያሳዩኝ አክብሮትና ትህትና በልቤ ላይ ታትሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ ገና በለጋ በወጣትነት ዕድሜያቸው ሩዋንዳውያን በሳንጃ ሲሞሻለቁ ፣ ጦር ሲማዘዙ እና ቃታ ሲሳሳቡ ወደዚያ ተጉዘው ለነፍሳቸው ሳይሳሱ ሩዋንዳ እንደገና ሩዋንዳ እንድትሆን በሀገሪቱ የሰላም አየር እንዲነፍስና ሰላሟ እንዲመለስ የከፈሉትን መስዋዕትነት እያነሱ በርካታ ሩዋንዳዊያን ያመሰግናሉ ፤ ‹‹ጠቅላይ ሚንስትራችሁ የዋለልንን ውለታ መቼም አንረሳውም፤ እዚህ ነበሩኮ›› እያሉ ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ ያነሳሉ ያመሰግናሉ ያከብራሉ፡፡

እኔ የጠቅላይ ሚኒስትሬ እና የፓርቲዬ ፕሬዝደንት ስም በበጎ በመነሳቱ ፤ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ሩዋንዳ ድረስ ተገኝቶ ለዋሉት ውለታ ሲሞካሹ እና ሲሞገሱ ልቤ ወዲህ በኩራት … ወዲያ ደግሞ አገሬ ውስጥ ያለውን ‹‹የስልጣን ልቀቅ -ስልጣን ልንጠቅ›› ትርክቶች ማቆጥቆጥን እያሰቡኩኝ በስጋት ከሩዋንዳ ሰማይ ስር እየመሸ ይነጋል … እኔም የሀገሬን ጉዳይ አብሰለስላለሁ!

በሩዋንዳ የሆነው ሁሉ ከመሆኑ በፊት ፤ የተከሰተው ዘግናኝ እልቂት ከመከሰቱ በፊት … እልቂቱን የመሩት የወቅቱ የፖለቲካ ሊሂቃን ነን ባዮች እንዲሁም እልቂቱን ያቀጣጠሉት ሚድያዎች የእኛን ‹‹ስልጣን ልቀቅ-ስልጣን ልንጠቅ›› ባይ ፖለቲከኞች እና ይህንን የሚለፍፉ ሚድያዎችን ይመስሉ ነበር!

ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ለማውረድ ይቸግራል ይሉት ብሂል ዛሬ ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ እጅጉን ይሰምራል፡፡ የማያውቁትን ህዝብ እናውቅልሃለን የሚሉ የጥፋት አበጋዞች በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ቁጭ ብለው የሚሰቅሉ እና ኋላ የሰቀሉትን ለማውረድ እንደሚቸገሩ የማያንሰላስሉ የጥፋት አበጋዞች በየስርቻው ተኮልኩለዋል፡፡
እንዲሆን ከሚፈልጉት እልቂት ማንም ምንም እንደማያተርፍ ዘንግተዋል፡፡ ሩዋንዳ ዛሬ ሌላ ገጽ ላይ ነች! ያለፈችውን ስቃይ ሰርክ እያስታወሰች በህዝቦቿ መሀል ፍቅር ትዘራለች! የመከራዋ ጥንስስ የተጠነሰሰው ፣ የተጠመቀው እና የተጠጣው በጽንፈኝነት ‹‹እኔ እበልጣለሁ!›› ትርክት እንደሆነም ለዓለም ታውጃለች፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የቱም ብሔር ከየትኛውም አይበልጥም! ፤ የትኛውም ሐይማኖት ከየትኛውም አያንስም! ፤ የትኛውም ባህል ከየትኛውም እሴት እና ወግ አይተናነስም አይበላለጥም! ፤ ሁሉም ስለ ሁሉም በሕብር የተሰናሰለ የሀገር መሰረት እና ካስማ እንደሆነ በፍጹም መዘንጋት የለበትም! ፡፡ ማንም ቢሆን ከመኖር የሚቀድም ዓላማ ሊኖረው አይችልም ፡፡ እንደ ሀገር የምንሞትለት ፣ የምንኖርለት የጋራ ታሪክ እና በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና እንድናደርግ ያስቻለን እልፍ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን፡፡
ስላለፉት ትርክቶች ሂሳብ ማወራረድም ሆነ የታሪክ አርትኦት መስራት የኛ አቅም እና ሃላፊነት አይደለም፡፡ ከትላንታችን ነቀፋ ይልቅ የነጋችን ተስፋ እጅጉን ይልቃል! እጅጉን ይደምቃል!

ይህ ተስፋችን እውን እንዲሆን ከትላንት ስህተት ተምረን ጥንካሪያችን ላይ ሌላ ጥንካሬ ደርበን ወደ ፊት የምንራመድ የመደመር ትውልድ ነን! አብሮ የሚያኖረን እና የሚያሻግረን ይሄው ነው!፡፡

Exit mobile version