Site icon ETHIO12.COM

የኢሳያስ መንግስት ለኤርትራንና ኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነት ጥንቃቄ ያድርግ!!

ችግር ካለ በሰለጠነ መንገድ መነጋገር፣ ህዝብ እንዲፈርድ ማሳወቅና ቀናውን መንገድ መከተል እንጂ ሴራ የትም አያደርስም። ጊዜውን፣ ስልጣኔውን፣ ወቅቱን ማገናዘብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት አገሮች በመሆናቸው የጉርብትና መርህ መከበር አለበት። ከምንም በላይ ሁለቱን የተጣበቀ ህዝብ ወደ መከራ በሚነዳ ተግባር መሳተፍ “ሲያልቅ አያምር” ከማሰነቱ በስተቀር ሌላ ትርፍ አያስገኝም። ዘመን፣ ትናንት፣ ከምንም ጊዜ በላይ ዛሬ አስተምሮናልና በድራማ መኖር አይቻልም። ይህ ሃቅ የሚያስቀይማቸው ካሉ በኢትዮጵያ ማህጸን ውስጥ ሆኖ ማሰብ እውነቱን ይገልጥላቸዋል ብለን እናስባለን። ኢትዮጵያ እናታችሁ የሆነች ሁሉ ቀናዋን ተመኙ። ወይም ተዋት!! አመድ አፋሽዋ ኢትዮጵያ “ተውኝ” ትላለች!!

በግልጽ ቋንቋ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ህዝብ ነው። በቀላል ቋንቋ ከዚህም ከዚያም ፖለቲከኞች ለፍላጎታቸው ቀጫጭን ጉዳዮችን አፋፍተው ለዩት እንጂ የአንድ ማህጻን ህዝብ ነው። አዋጉት እንጂ አንድ ጡት የጠባ ህዝብ ነው። ቂም ዘሩበት እንጂ በምንም የማይፈላለግ ምስኪን፣ ሃይማኖተኛ፣ አንቺ ትብስ፣ አንተ ትብስ ብሎ የሚኖር ህዝብ ነው። ይህን ሃቅ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ግንኙነት ዳግም ሲጀመር በግልጽ አይተነዋል። ምን ያደርጋል እንዲሉ አልቀጠልም። የጨነገፈ ይመስላል።

ኤርትራ አገር ከሆነች ጀምሮ “አገር ነን” የሚለው ፍላጎት ” ኢኮኖሚውን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን እንሾፍረው” ከሚል ጣምራ ፍላጎት ጋር ተቆራኝቶ ነበርና “የጨዋታው ህግ ልክ አይደለም” በሚል ጉዳዩን የሚከታተሉ ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ። ጉዳዩ ከሁለት የተለያዩ አገሮች ግንኙነት ዘሎ መርህ በጣሰ መልኩ ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በመነከሩ በባድመ የተሰባበ ጦርነት ተነሳ።

በዚህ መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ በበላ ጦርነት ነጹሃን ተማገዱ። ከሁሉም ወገን በዘመቻ ስም ዘፈን እየተዘፈነ የሰው ልጆች አለቁ። መጨረሻ ላይ መሪዎቹ ተጨባበጡ። ህዝብ ንብረቱን፣ ሃቁን፣ የለፋበትን በገፋፊዎች ተነጠቀ። ታፍሶ በረሃ ተበተነ። የወርቅ ጥርስ ሳይቀር ተነቅሎ፣ ጥሪት ሃብት ሳያስቀሩለት ዘርፈው አባረሩት። ወደብ ላይ ያለ ንብረት ተዘረፈ። ነጋዴዎች ከሰሩ። ከሁሉም በላይ ግን ሻዕቢያ ጦርነት እንዲቆም መሳሪያ እንዲያቆለቁል ሲታዘዝ፣ ትጥቅ በፈቱ የኢትዮጵያ ልጆች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ማድረጉ ማንም ሊያስተባብለው የማይችል ጠባሳችን ነው።

ይህን ያልነው ዛሬ ላይ ማሰብን የሚጠይቁ በርካታ ጉዳዮች በመፈጠራቸው ነው። ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ ቂሙ፣ ክፋቱ፣ ክፉ ምኞቱ ቀርቶ በዘንባባ ዝንጣፊ የተጀመረው ግንኙነት፣ የተለያዩ ቤተሰቦችን ያገናኘ፣ እንባ ያራጨ፣ ሰማይን ዘልቆ ጸቦኦት የሚገባ ምስጋና ለፈጣሪ የፈሰሰበት አዲስ ጅማሬ መዳፈኑ ሳይሳዝነን ዛሬ ላይ ደስ ወደማይል ጎዳና እያመራን ነው። በርካታ ምልክቶች አሉ። ሳይቃጠል በቅጠል …

ዛሬ ኢሳያስ ከአንድ ክልል ሚሊሻ እየመለመሉ በማስለጠንና በማስታጠቅ ተጠምደዋል። ይህ ሃቅ ነው። “ንቃት በቅቷል። አሁን የተግባር ስራ ይጀመራል። የብልጽግና መንግስትን መነቀያው ደርሷል። አብይ አህመድ ከመሸሽ፣ እጅ ከመስጠት ወይም ከመሞት ውጭ አማራጭ የለውም” በሚል በቅርቡ ዘመቻ እንደሚጀመር አውስትራሊያ ላይ ይፋ ካደረጉት ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ጋር ገጥመዋል። እድሜ የተጫናቸው ሻለቃ ዳዊት፣ ለጊዜው ስማቸው ከማይጠቀሱ ጋር ኢሳያስ ስለምን አብረው ኢትዮጵያ ላይ እሳት ለመለኮስ እንዳሰቡ ግልጽ አይደለም። ይህ ተጨባጭ መረጃ የሚቀርብለት እውነት ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ መንግስት የሚያስለጥነው የኤርትራ ተቃዋሚ ሃይል የለም። ኤርትራዊያን እንዲያውክና እንዲረብሽ ኢትዮጵያ ጦር እየመለመለች አይደለም። ኤርትራዊያን በኢትዮጵያ ያለ አንዳች ልዩነት በሚፈልጉት ስራ ተሰማርተው እየኖሩ ነው። አንዳችም ዓይነት ሮሮ ሲያሰሙ አልተደመጠም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከበፊት ጀምሮ ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዳጠሉ የሚኖሩበት ምክንያት እውነት ለመናገር ምክንያት የሚቀርብበት አይደለም። በአፋቸው የሚናገሩት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ነገር ሲኖር ውይም ሲከወን ተነስተው የአዛኝ ቅቤ አንጓች የሚሆኑበት ስልት ጊዜው ያለፈበት ነውና እንዲያቆሙ እንማጸናለን። በተለይ ወንድም የሆነው የኤርትራ ህዝብ ይህን ድርጊት ይብቃ ማለት አለበት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የኢትዮጵያ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማናቸውም ሰዎች ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ እኩል ልጆች ናቸው። ትግራይ ኢትዮጵያ ናት። ትግራይና ትህነግ አንድ አይደሉም። በጋራ ትግል የተካሄደው የትግራይን ህዝብ አግቶ ከነበረው የትህነግ ጥጋብና ትምክህት ጋር እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር አይደለም። አሁን ጦርነቱ አብቅቷል። ሰላም ሰፍኗል። ነገሮች ወደ ቀድሞ መላካቸው እንዲቀየሩ እየተሰራ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። ኢሳያስን አይመለከትም። የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ በሚደጎሙ ሚዲያዎች ማብራሪያና ጥርጣሬ ለመንዛት ኢሳያስም ሆኑ ሌሎች ተግባራቸው ሊሆን አይገባም።

ትህነግ የአገር መከላከያን ሲክድ ኤርትራ እንደ ህዝብ፣ እንደ አገርና እንደ አጋር ላደረገችው ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች። ጥቁሩ ጠባሳ በታሪክ እንደተቀመጠ ሁሉ ይህ ድንቅ ታሪክም በወርቃማ ቀለም ተከትቦ ለትውልድ ይተላለፋል። ግን ይህ ማለት በውለታ ስም በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ ማንቦጫረቅን ፈቃድ ማግኛ አይደለም።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ አንድ ስንጥር ያለ ህግ አግባብ እንደማትነካ ሁሉ፣ ኤርትራም ጉርብትና በሚከበርበት፣ መርህ ሳይጣስ፣ ህግና ደንብ ተከብሮ ካልሆነ በስተቀር ስንጥር መንካት አይፈቀድም። ለጊዜው ዝርዝር ውስጥ መግባት ባያስፈልግም በርካታ ህገወጥ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው። ነገሩን የሚከታተሉ ” መንግስት ሆይ የት ነህ?” እያሉ ነው። ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የመዳከር አዝማሚያው ፈር እየለቀቀ ነው። ኮንትሮባንዱና ዶላር አጠባው ብቻ ሳይሆን ከጠብ መንጃ ጋር የተገናኘው ጣልቃ ገብነት እየባሰና እየናኘ ነው። ነገሩ ሳይበላሽ መስመር ማስተካከሉና አቅምን ተረድቶ በህግ አግባብ ጥሩ ወዳጅ መሆኑ ያዋጣል። ከዚህ የተረፈው ጨዋታ “ተረኛ ነሽና..” የሚለውን ዘፈን ከማስታወስ አይዘልም።

ዛሬ ኢትዮጵያ በመከላከያ አቅሟም ሆነ በኢኮኖሚ ጡንቻዋ ለኢሳያስ የምትሸነፍ አትመስልም። በውጭ ግንኙነትም ሆነ አሁን ባሉት የኢትዮጵያ መሪዎች እሳቤ እንደ ቀድሞው ብልጣ ብልጥ መሆን የሚቻልበት ቀዳዳ የሚኖር አይመስለንም። በዚህ ላይ ብዙ የሚጠዘጥዝ ቁስል ያለባቸው ዜጎች እንዳሉ መረሳት የለበትምና ኢሳያስ እጅዎትን ከኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ይሰብስቡ። የስከዛሬው ይበቃልና!! ኢትዮጵያዊ ሆናችሁ ከኢሳያስ ጋር አብራችሁ የምትሰሩ ከግምትና ከፍርድ አታመልጡምና ይቅርባችሁ። የሁላችሁም ሩጫ ለኤርትራና ኢትዮጵያ የተዋሃዱ፣ የአንድ ዘር ልጆች መከራን እንጂ ሌላ በጎ ትሩፋት አታመጡምና አደብ ግዙ፤ የኤርትራ ህዝብና የሻዕቢያ ደጋፊዎችም ምን እየሆነ እንደሆን በመርመር መስመራችሁን አጥሩ። ብሄርን ከብሄር በመከፋፈል የሚገኝ የፖለቲካ ጨዋታ እንዲቆም

ኢትዮጵያ ጦርነት ቋቅ ብሏታል። ኢትዮጵያ እብሪተኞች ጦርነትና ሴራ ባመረቱ ቁጥር ብረት ማንሳት ሰልችቷታል። በእርግጠኛነት የኤርትራ ህዝብም ጦርነትን አይመኝም። ሁላችንም ከሰላም እንጂ ከጦርነት አናተርፍም። በደን ስላየነው በእሳት ዳግም አንጫወትም። ስለዚህ መንግስት በያዘው ሆነ ሰፊነት ህግን እያስከበረና ኮንትሮባንድን እየተከላከለ እንዲቀጥል እንመክራለን። ኢሳይስንም ዘመንዎትን ለትውልድ ሰላምና ስጋት የሌለው ህይወት በማጎናጸፍ እንዲጠቀልሉ እናሳስባለን። የእሳካሁኑ ስለሚበቃው በመጪው ትውልድ ጊዜ፣ ህይወት፣ ኖሮ፣ ጉርብትና፣ እምነት፣ … ተስፋ ላይ እሳት እንዳያነዱ አበክረን እነግርዎታለን።

ይህ የኢትዮ12 አቋም ነው

Read more stories.

Exit mobile version