Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ የእርዳታ ምግብ ገበያ ላይ በብዛት በመታየቱና ለጊዜው የምግብ እርዳታ ተቋረጠ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ክላውድ ጂቢዳር በአገሪቱ ላሉ አጋር ድርጅቶች በጻፉት ደብዳቤ “በአንዳንድ ገበያዎች የታየው መጠነ ሰፊ የሆነው የእርዳታ ምግብ ሽያጭ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ስጋት እንዲገባው አድርጎታል” ማለታቸውና ከሽራሮ መቶ ሺህ ሰዎችን ሊቀልብ የሚችል እህል መዘረፉን አስመልክቶ ምርመራ መጀመሩ ተገልጾ ነበር። ከዚሁ ጋር ተያያዞ ነው የዓለም ድርጅት በትግራይ የእርዳታ አቅርቦቱን ለጊዜው ማቋረጡ ተገልጸ።

ቢቢሲ ሙሉ ዘገባ – የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ውስጥ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ማቋረጡን የረድኤት ሠራተኞች ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናገሩ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ የሚያካሂደውን የእርዳታ አቅርቦት ያቋረጠው ከሳምንታት በፊት ለተረጂዎች በሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ስርቆት ለማጣራት ውሳጣዊ ምርመራ ለማካሄድ እንደሆነ አራት የእርዳታ ሠራተኞች ገልጸዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለሁለት ዓመት በአውዳሚ ጦርነት ውስጥ በቆየችው የሰሜን ኢትዮጵያ ክልል ትግራይ ውስጥ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከሌሎች አጋሮቹ የሚገኘውን የምግብ እርዳታ ለተረጂዎች የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት አካል ነው።

አራት የእርዳታ ሠራተኞች ለአሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደገለጹት የእርዳታ ምግብ ተገቢ ላልሆነ አላማ እየዋለ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ድርጅቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ትግራይ የሚያደርገውን የእርዳታ አቅርቦት በጊዜያዊነት አቋርጧል።

ይህንንም መረጃ ሌሎች ሦስት የእርዳታ ሠራተኞች ለዜና ወኪሉ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ሁሉም በጉዳዩ ላይ ለጋዜጠኞች መረጃ የመስጠት ፈቃድ ስለሌላቸው ስማቸው እንዲጠቀስ እንዳልፈለጉ ኤፒ ገልጿል።

ከሳምንታት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በሚያካሂደው የሕይወት አድን የእርዳታ ሥራ ላይ የተፈጸመ የምግብ አቅርቦት ስርቆትን እየመረመረ እንደሚገኝ ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

ይህንንም አስመልክተው የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ክላውድ ጂቢዳር በአገሪቱ ላሉ አጋር ድርጅቶች በጻፉት ደብዳቤ “በአንዳንድ ገበያዎች የታየው መጠነ ሰፊ የሆነ የእርዳታ ምግብ ሽያጭ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ስጋት እንዲገባው አድርጓል” ብለዋል።

ዳይሬክተሩ ለእርዳታ የተባሉ ምግቦች ለገበያ መቅረባቸው በተቋሙ ስም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳደሩም በላይ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ የማሰባሰብ አቅም ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ስለዚህም በአገሪቱ በእርዳታ የሚሰጥን ምግብ “አላግባብ መጠቀምን እና ከታለመለት ዓላማ ውጪ መውሰድ በአስቸኳይ ማስቆም እጅግ ወሳኝ ነው” ብለዋል።

ጂቢዳር መጋቢት 27/2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አጋር ድርጅቶች በጻፉት ደብዳቤ፣ አጋር ድርጅቶች የእርዳታ ምግብ ባልተገባ ሁኔታ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ አልያም ስለመወሰዱ የሚያውቁት ካለ መረጃ እንዲያጋሩ ጠይቀዋል።

ከሳምንታት በፊት ኤፒ የእርዳታ ሠራተኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው በእርስ በእርስ ጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ሽራሮ ከነበረ መጋዘን ውስጥ ለ100 ሺህ ሰዎች ሊበቃ የሚችል የእርዳታ ምግብ መጥፋቱን ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመት ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በቆመው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች የምግብ እርዳታ በመዝረፍ እና ለተዋጊዎቻቸው በማቅረብ ሲከሰሱ እንደነበር ይታወሳል።

Exit mobile version