Site icon ETHIO12.COM

የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ለ7 ቀናት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከነገ ሚያዚያ 25 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የተነገረው።

በሱዳን የሰላም ስምምነት እንዲደረስ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የተሾመው ቡድን መሪው የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲይት ትናንት ከሁለቱም ጀነራሎች ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
በዚህም ተፋላሚዎቹ ወገኖች የሰባት ቀናት ተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

በተኩስ ማቆም ሳምንቱ ተፋላሚዎቹ ፊት ለፊት የሚደራደሩበትን ጊዜና ቦታ እንዲሁም ተደራዳሪዎቻቸውን ይፋ ለማድረግ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም መግለጫው ያሳያል።
ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ከጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ጀነራሎቹ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተጠቅመው በፍጥነት የድርድር ሂደቱን እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል።

የሱዳን ጊዜያዊ የውጭ ጉዳይሚኒስትር ከግብጽ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ካናዳና ብሪታንያ አቻቸው ጋር ግጭቱ በሚበርድበት፣ የውጭ ዜጎች ከሱዳን በሚወጡበትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል።
በሱዳን ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስና የጀነራሎቹን ልዩነት በንግግር እንዲጠብ ከጀነራል አልቡርሃን እና ጀነራል ዳጋሎ ጋር በቅርበት መስራቷን እንደምትቀጥል ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ተናግረዋል።

ጁባ ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ደቡብ ሱዳን ለገቡ ሱዳናውያን አለማቀፉ ማህበረሰብ እያደረገ ስለሚገኘው ድጋፍ አመስግናለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በሱዳን በተነሳው ግጭት ሳቢያ 800 ሺህ የሚደርሱ ሱዳናውያን ሀገራቸውን ለቀው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

እስካሁንም ከ73 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ወደ ቻድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ግብጽ እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
በሱዳን ከሶስት ጊዜ በላይ የተደረሱ የ72 ስአት የተኩስ አቁም ስምምነቶች ወዲያውኑ እየተጣሱ ጦርነቱ ሶስተኛ ሳምንቱን ይዟል።
(Al ain)

Exit mobile version