Site icon ETHIO12.COM

“መጪው ዘመን በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ምክንያት አስፈሪ ሆኗል” ጀፍሪ ሒንተን

ቻትጂፒቲን የመሰሉ ፈጠራዎች የሰው ልጅን መልሰው ሊቆጣጠሩት እንደሚችሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አባት የሚባሉት ጀፍሪ ሒንተን ፍንጭ ሰጡ።

የ75 ዓመቱ ጀፍሪ ሒንተን ይህን የተናገሩት ጉግል ኩባንያን በለቀቁበት ወቅት ነው።

እኒህ ሳይንቲስት ለኒውዮርክ ታይምስ በጻፉት ሐተታ፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙርያ በሠሯቸው ሥራዎች አሁን ላይ ጸጸት እንደሚሰማቸው ጠቅሰዋል።

ሳይንቲስቱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ እንዴት አንዳንድ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራዎች ‘አስፈሪ እና አደገኛ’ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተንትነዋል።

‘ሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራዎች ለጊዜው ከሰው ልጅ በላይ አልሆኑም፤ በጊዜ ሂደት ግን የሰው ልጅን ይቆጣጠሩታል ይመስለኛል’ ብለዋል።

የዶ/ር ሒንተን በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ልህቀት ዙርያ ያደረጓቸው ጥናት እና ምርምሮች ቻትጂፒቲን ለመሰሉ ትልልቅ ሥራዎች መፈጠር መሠረት የጣሉ ናቸው።

የብሪታኒያ እና ካናዳ ጥምር ዜጋ የሆኑት ሳይንቲስቱ፣ የአስተውሎት ሥነ ልቡና (cognitive psychologist) እና የኮምፒውተር ሳይንስ ዝነኛ ተመራማሪ ናቸው።

ከጉግል መልቀቃቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቻትቦት በቅርብ ጊዜ የሰው ልጅ አእምሮ ሊሸከመው የሚችለውን መረጃ በተሻለ ሊሰንድ ይችላል ብለዋል።

”ለምሳሌ አሁን ጂፒቲ በጠቅላላ ዕውቀት ዙርያ ካየነው የሰው ልጆችን በሙሉ ይበልጣል። በምክንያታዊነት እና ሚዛናዊነት ካየነው ገና ከሰው ልጅ አቅም አልደረሰም። ነገር ግን ምክንያታዊነት እና አመክንዮን ቀስ በቀስ ተምሮ የሰው ልጅን ሊልቅ ይችላል” ብለዋል።

ሳይንቲስቱ ዶ/ር ሒንተን ጨምረውም፣ ‘አሁን ባለው ፍጥነት የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ልጅን አስተውሎት በልጦ ለመገኘት ብዙ ዘመን አይወስድበትም’ ብለዋል።

በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ደግሞ ዶ/ር ሒንተን ይህን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራ በጎ ላልሆኑ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ የሚያውሉ አካላትን ወቅሰዋል።

የሰው ልጆችን እና ቻትቦትን በማወዳደር አደገኛነቱን ሲያስረዱም፣ 10 ሺህ ሰዎችን ለማሰልጠን እና አንድ ቦታ ለማድረስ የሚወስደውን ዘመን በማሳያነት በመጥቀስ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ግን አንድን መረጃ አንድ ጊዜ ከተማሩት በኋላ በቅጽበት 10 ሺህ ማሽኖች አወቁት ማለት ነው። ይህ ለሰው ልጅ ስጋት ነው ብለዋል።

ዶ/ር ሒንተን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ እየተሠራ ያለው ነገር አሳስቧቸው ሥራ መልቀቃቸውን ቢጠቅሱም ሌሎች ምክንያቶችም ሥራ ለመልቀቃቸው ምክንያት መሆናቸውን አልሸሸጉም።

“አሁን ዕድሜዬ 75 ደረሰ። ጡረታ ጊዜዬ ነው። ስለ ጉግልም በጎ ነገሮችን መናገር አለብኝ፤ ለጉግል እየሠራሁ ስለ ጉግል በጎ ነገር ባወራ አያምርብኝም፤ መልቀቅ ነበረብኝ’ ብለዋል።

ዶ/ር ሒንተን ጉግል የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በተመለከተ ኃላፊነት የሚሰማው ድርጅት እንደሆነ መስክረዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

Exit mobile version