Site icon ETHIO12.COM

በኬንያ በረሃብ ከሞቱ አማኞች የሰውነት የውስጥ የአካል ክፍል መጥፋቱ በምርመራ ተረጋገጠ

በኬንያ የባሕር ዳርቻ ግዛት ኪሊፊ ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈት እና መጥፋት ምክንያት ከሆነው የእምነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአስከሬኖች ላይ በተደረገ ምርመራ የአንዳንዶች የውስጥ አካል መጥፋቱ ተነገረ።

የእምነቱ ተከታዮች እራሳቸውን በጾም በማድከም ከሞቱ መንግሥተ ሰማያት እንደሚገቡ በእምነቱ መሪ በመሰበካቸው፣ ህጻንትን ጨምሮ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች አስከሬን በፖሊስ ተፈልጎ መገኘቱ ይታወቃል።

ለጊዜው ተቋርጦ የነበረው የተቀበሩ ሟቾችን የመፈለጉ ሥራ ማክሰኞ ዕለት መልሶ የተጀመረ ሲሆን፣ ተጨማሪ 21 አስከሬኖች ተገኝተው በቁፋሮ ወጥተዋል።

በዚህም ሳቢያ ከዕምነት ቡድኑ አስተምህሮት ጋር በተያያዘ ሞተው አስካሁን በፍለጋ የተገኙት ሰዎች አስከሬኖች አሃዝ ወደ 133 ከፍ ብሏል።

የደረሱበት ያልታወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስላሉ ፍለጋው አሁንም ቀጥሏል።

ይህንንም ተከትሎ ጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ ያለው የኬንያ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ባቀረበው የአስከሬን ምርመራ ውጤት ሰነድ ላይ፣ ተቆፍረው ከወጡ አስከሬኖች ላይ ያልተገኙ የውስጥ የአካል ክፍሎች እንዳሉ ተመልክቷል።

“በአስከሬኖች ላይ የተደረጉ ምርመራዎች ከሞቱት ሰዎች መካከል በተወሰኑት ላይ አንዳንድ የውስጥ ከፍሎች በቦታቸው እንዳልተገኙ ሪፖርት ተደርጓል” ሲል በፖሊስ ኃላፊው ማርቲን ሙኔኔ ለናይሮቢ ከተማ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ሰነድ ላይ ጠቅሰዋል።

ሰነዱ ጨምሮም “የሰዎች የውስጥ አካል ንግድ እጅግ የተቀነባበ እና በውስጡም በርካታ ወገኖች ይሳተፉበታል ተብሎ ይታመናል” ሲል ገልጿል።

ይህ የአስከሬን ምርመራ ይፋ ያደረገው ውጤት የእምነት ቡድኑ አባላት ከገጠማቸው ሞት በተጨማሪ፣ ለሌሎች ሰዎች ሊተላለፉ ይችላሉ የሚባሉ የውስጥ የአካል ክፍሎችን የማውጣት እና የማዘዋወር ወንጀል ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።

በእምነት ቡድኑ ይዞታ ውስጥ ተቆፍረው በወጡ 112 አስከሬኖች ላይ የተደረገውን ምርመራ በተመለከተ የምርመራው መሪ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የውስጥ አካል ስርቆት አልተከሰተም ብለው ነበር።

ነገር ግን አሁን ለፍርድ ቤት የቀረበው ሰነድ በተወሰኑት አስከሬኖች ላይ ያልተገኙ የውስጥ አካል ክፍሎች እንዳሉ ተገልጿል። ነገር ግን የትኞቹ የአካል ክፍሎች እንደጠፉ የተባለ ነገር የለም።

የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ኪቱሬ ኪንዲኪ በአስከሬን ምርመራው መጥፋታቸው ታውቋል የተባሉትን የውስጥ አካላትን በተመለከተ “ምርመራው አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ ይህም ትኩረት የሚደረግበት ጉዳይ ነው። ስለዚህም ባለሙያዎች ምንም ነገር ቀድሞ ከማናገር እንድንቆጠብ ተነግሮናል” ብለዋል።

በአስከሬኖች ላይ በተደረገው ምርመራ ህጻናትን ጨምሮ አብዛኞቹ ሰዎች የሞቱት በመራብ ምክንያት ሲሆን፣ ነገር ግን የተወሰኑት ታንቀው፣ ተደብድበው ወይም ታፍነው ለህልፈት መዳረጋቸውን ባለሙያዎቹ አመልክተዋል።

የእምነት ቡድኑ መሪ እና የክስተቱ ዋነኛ ተጠርጣሪ የሆነው ፓስተር ፖል ማኬንዚ፣ ተከታዮቹ ወደ መንግሥተ ሰማያት በቶሎ በመሄድ ኢየሱስን ለማግኘት እንዲችሉ እየጾሙ እንዲሞቱ ሲያበረታታ ነበር ተብሏል።

በእስር ላይ የሚገኘው የእምነት ሰባኪው ግለሰብ ቀደም ሲል ተከታዮቹ እስከሞት ድረስ እንዲጾሙ አስገድዷቸዋል ተብሎ የተከሰሰ ቢሆንም፣ እሱ ግን ይህንን ክስ አስተባብሏል።

የኬንያ የባሕር ዳርቻ ግዛት በሆነችው ኪሊፊ ውስጥ ሻካሆላ በሚባለው አካባቢ ባለው የፓስተር ማኬንዚ ሰፊ ጫካ ባለበት ይዞታ ውስጥ አሁንም የተቀበሩ አስከሬኖችን ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ ቀጥሏል።

የኬንያ ቀይ መስቀል እንዳለው ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ 360 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁ ሪፖርት እንደተደረገለት አሳውቋል።

የኬንያ ባለሥልጣናት አስካሁን አስከሬናቸው ከተገኙት ሰዎች በተጨማሪ በጾም ላይ የነበሩ ቢያንስ 60 በሕይወት ያሉ ሰዎች በፖሊስ ተገኝተው ከአካባቢው እንዲወጡ መደረጉን አመልክተዋል።

‘ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቸርች’ መሪ የሆነው ፓስተር ማኬንዚ፣ ተከታዮቹ እራሳቸውን አስርበው እንዲገድሉ አዟል ተብሎ የተከሰሰ ሲሆን፣ በእስር ላይ ሆኖ ጉዳዩን እየተከታተለ ነው።

በመጥፎ የአየር ፀባይ ምክንያት የእምነቱ ተከታዮች ተሰባስበው በቆዩበት የሻካሆላ ጫካ ውስጥ የጠፉ ሰዎችን የመፈለጉ ሥራ እንዲዘገይ አድርጎት ቆይቷል።

ዘገባው የቢቢሲ ነው

Exit mobile version