Site icon ETHIO12.COM

ከጅቡቲ ተላልፎ የተሰጠው ጎበዜን ጨምሮ ስድስት ተጠርጣሪዎች በሽብር ወንጀል ተከሰሱ

ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸውና ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ከጅቡቲ ተላልፎ ተሰጠ የሚለው ዜና ሃሰት እንደሆነ የተለያዩ የአክቲቪስት ሚዲያዎችና ማህበራዊ ገጾች ቢገልጹም ጠበቃውም ሆነ ራሱ ጎበዜ ከጅቡቲ ተላልፎ መሰጠቱን በፍርድ ቤት አላስተባበሉ።

ማክሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ ም ፍርድ ቤት የቀረበው ጎበዜ ከሌሎች አምስት ግለሰቦች ጋር በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ መከሰሱን መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ህገ መግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ፣የፖለቲካ አላማን ለማሳካት፣ ኢ- መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር የወታደራዊ ስልጠና ክንፍ እና የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ክንፍ በማዋቀር የሽብር ወንጀል ድርጊት ለመፈፀም በመመጋገብ ሲንቀሳቀሱ እነደነበር የሚያሳይ የጥርጣሬ መነሻ ነጥቦችን ዘርዝሮ ለችሎት አስረድቷል። በዚሁ መነሻ ተጨማሪ ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮና የክስ ጭንጥ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ተቃውመዋል። ” ፖሊስ ከዚህ በፊት ሁከትና ብጥብጥ ወንጀል በሚል ተጠርጣሪዎችን ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቅርቦ በነበረበት ወቅት ባቀረበው መልኩ ተመሳሳይ ይዘት ያለው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያት ነው ያቀረበው ” በማለት ተቃውሟቸውን አብራርተዋል።

በተለይም ጎበዜ ሲሳይን በሚመለከት የተጠረጠረው በሙያው ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩ ሊታይ የሚገባው በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሲሳይ አውግቸው ስም የተከፈተውን የክስ መዝገብ የሚያየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ባስቻለው በዚህ ችሎት ጎበዜን የወከሉት ጠበቃ አዲሱ አልጋው፤ ፖሊስ ማን በየትኛው የወንጀል ድርጊት የተሳተፈ እንደሆነ የገለጸው ነገር አለመኖሩን ተናገረዋል። የተጠርጣሪዎች የወንጀል ተሳትፎ ፖሊስ በጽሁፍ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ አለመገለጹንም አስረድተዋል። አቶ አዲሱ አክለውም ደንበኛቸው “ጥፋት ፈጽመዋል ከተባለ እንኳን በሚዲያ ስራቸው አማካኝነት ነው። ስለሆነም የምርመራ ሂደቱ መመራት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ነው” ሲሉ ሞግተዋል። ጎበዜ ሲሳይ ከጅቡቲ ተላፎ መሰጠቱን ሃሰት ነው በሚል ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲገለጽ እንደሰነበተው ማስተባበያ ይቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም የተባለ ነገር የለም።

መርማሪ ፖሊስ “ጋዜጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ተጠርጥረው የተያዙት [ግን] ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር ተያይዞ አይደለም” ብሏል። የፌደራል ፖሊስን ወክለው ችሎት የተገኙት መርማሪ ፖሊስ አክለውም፤ “የጋዜጠኝነት ሙያን እንደሽፋን ተጠቅመው ሲሰሩ ነበር” የሚል ውንጀላን በጋዜጠኛ ጎበዜ ላይ በማቅርብ የጠበቃውን መከራከሪያ ተቃውመዋል።

የስድስቱም ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ አለልኝ ምህረቱ፤ “ተጠርጣሪዎቹ የትኛውን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት እንደተንቀሳቀሱ መርማሪ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ላይ አልገለጸም” ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል። መርማሪ ፖሊስ ለችሎት ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ፤ ተጠርጣሪዎቹን “ራሳቸውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ለማራመድ በማሰብ ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመቀየር” ወንጅሏቸዋል፡፡ ጠበቃ አለልኝ ግን “የፖለቲካ ድርጅት ሳይቋቋም የፖለቲካ ዓላማ በግለሰቦች በተናጥል የሚፈጸም አይደለም” የሚል መከራከሪያን አቅርበዋል።፡

በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አማካኝነት የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ “በጥብቅ” የተቃወሙት መርማሪ ፖሊስ፤ “የፖለቲካ ድርጅት ባይኖርም ‘ድርጊቱ ሽብር እስከሆነ ድረስ የሽብር ወንጀል ነው’ የሚል ጭብጥ ይዘን ነው [የቀረብነው]” ሲሉ የመልስ መልስ ሰጥተዋል፡፡ መርማሪው አክለውም ተፈጸመ የተባለው ወንጀል፤ “እጅግ ከባድ እና ውስብስብ” እንዲሁም “የሀገር አንድነት ላይ ችግር የሚፈጥር” በመሆኑ የዋስትናው ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አንድ ሰዓት ገደማ የፈጀውን የግራ ቀኝ ክርክር ካደመጠ በኋላ፤ በቀረበው የዋስትና እና የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ረቡዕ ግንቦት 2፤ 2015 ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዛሬው የችሎት ውሎ ስድስቱም ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸውን በአካል ተገኝተው ተከታትለዋል፡፡ 

ዜናው የተቀናበረው ከኢትዮ ኢንሳይደርና ፋና ነው።

Exit mobile version