Site icon ETHIO12.COM

የአማራ ክልል የነብሮ ልዩ ሃይል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንን መርጦ ስልጠና ጀመረ

Made with LogoLicious Add Your Logo App

ሀገር ፈተና ውስጥ ሳለች ብርቱ ክንዶቻቸውን ጋሻ አድርገው ሀገር እና ሕዝብን ከውርደት ታድገዋል፡፡ እንደ አባቶቻቸው ክተት ሲባሉ ከትተው ግንባራቸውን ለአሩር፣ ደረታቸውን ለጦር እግሮቻቸውን ለጠጠር ሰጥተው ታሪክ እና ሀገርን አስጠብቀው አቆይተዋል፡፡ ታሪክ የማይረሳ እና ትውልድ በየዘመኑ የሚያስታውሰው ጀብዱ የሰሩት የዘመኑ አናብስት የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት፡፡

የክልል ልዩ ኃይል አባላትን በላቀ ደረጃ መልሶ ማደራጅት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ወደ ሥራ ከተገባ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ምንም እንኳን ይላሉ የልዩ ኃይል አባላቱ “ጦሩን በላቀ ደረጃ መልሶ ለማደራጀት የተሰጠው ጊዜ አጭር በመኾኑ በቂ ውይይት አለመደረጉ ተፈጥሮ ለነበረው አለመግባባት ምክንያት ቢኾንም፤ በቀጣይ የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመፈጸም የሚያስችል ዝግጅት እያደረግን ነው” ብለዋል፡፡

የልዩ ኃይል አባላቱ በፌዴራል እና በክልል የጸጥታ ተቋማት ውስጥ እንደየፍላጎታቸው እና ምርጫቸው እንዲሰማሩ አሠራር ተዘርግቶ እየተተገበረ ነው፡፡ ከቀረበላቸው ምርጫዎች መካከል የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንን ከመረጡት ኮሚሽኑ የሚሰጠውን የተሃድሶ ሥልጠና ከሚወስዱ አባላት መካከል ረዳት ኢንስቴክተር ከፍያለው ደጀንን እና ሃና ደገፉን አሚኮ አነጋግሯቸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ክልሉ እና ሀገሪቱ ከነበሩበት የህልውና ሥጋት አንጻር በተለያዩ ግንባሮች የአማራ ሕዝብ እና መንግሥት የሰጡንን አደራ በብቃት ለመወጣት ሞክረናል ያለን የነብሮ ክፍለ ጦር የሕግ ክፍል ኃላፊ የነበረው ረዳት ኢንስፔክተር ከፍያለው ደጀን በቀጣይም የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት የሰጡኝን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ጥረት አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት የተለየ የራሱ ተግባር እና ኃላፊነት አለው ያለን ረዳት ኢንስፔክተር ከፍያለው የኮሚሽኑን አሠራር ለመገንዘብ የሚያስችል የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳችን ተገቢ ነው ብሏል፡፡

በአማራ ልዩ ኃይል የነበልባል ክፍለ ጦር አባል የነበረችው ሃና ደገፉ ከቀረቡላቸው አማራጮች መካከል የማረሚያ ቤት ኮሚሽንን መምረጧን ገልጻ በቀጣይም የተሰጣትን ተግባር እና ኅላፊነት በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡

የአማራ ልዩ ኃይል በቆይታው የክልሉን ሕዝብ በላቀ ብቃት አገልግሏል ያሉት አባላቱ የተሰው እና ጉዳት የደረሰባቸውን የሠራዊቱን አባላት እና ቤተሰቦች በዘላቂነት ማቋቋም የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡ ሀገር እና ሕዝብ በፈለገቻቸው ጊዜ በየትኛውም ግዳጅ ለመሳተፍ ዝግጁ እንደኾኑም ተናግረዋል፡፡

የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምርጫቸው ያደረጉ የልዩ ኃይል አባላት ኮሚሽኑ የነበሩበትን ክፍተት ለመሙላት ጉልበት ይኾናሉ ያሉን ደግሞ የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ ናቸው፡፡ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት በተለየ የሕግ ታራሚዎችን የማረም፣ የማነጽ፣ የማጀብ እና የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ውቤ ለዚህ ተልእኮ ብቁ የሚያደርግ ተጨማሪ የተሃድሶ ሥልጠና መሥጠት አስፈላጊ ነበር ብለዋል፡፡

በአዲስ ኮሚሽኑን የተቀላቀሉ የልዩ ኃይል አባላት ክብራቸውን፣ ጥቅማቸውን እና ደረጃቸውን የሚመጥን ስምሪት ይሰጣቸዋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የነበራቸውን ወታደራዊ ልምድ፣ እውቀት፣ ሥነ-ምግባር እና ክህሎት በመጠቀም የኮሚሽኑን አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው አሚኮ

Exit mobile version