Site icon ETHIO12.COM

ሿሿ – ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ያስረዳል። እነዚህ የተደራጁ ዘራፊዎች በሚኒባስ ሆነው ተሳፋሪን “የት ነህ” ብለው ይጠይቁና አስገብተው ከቻሉ አዋክበው፣ ካልቻሉ አስገድደው የሚዘርፉ ማጅራት መቺዎች ናቸው። ፖሊስ እንዳለው ከሆነ ዘርፊያው የአክሲዮን ይዘት አለው።

ወንጀል ፈፃሚዎቹ በቀን እስከ 35ሺ ብር ተቀማጭ እንደሚያደርጉ በምርመራ መረጋገጡን ፖሊስ አስታውቋል። በዘረፋ በቀን እስከ 35 ሺህ ብር የሚቆጥብ ማጅራት መቺ ያለባት አዲስ አበባ ብዙ ጉድ ለመሸከሟ ማሳያ ነው።

በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ አያጣራ መሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሲያስታውቅ ይፋ እንዳደርገው ፊልም ከሆነ ከዘራፊዎቹ መካከል አንዷ ነብሰ ጡር ናት።

በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብን ለምሬት ከዳረጉ የወንጀል ድርጊቶች መካከል በተለምዶ ሿሿ የሚባለው ወንጀል አንዱ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀሉን ለመከላከልና ወንጀለኞቹን ህግ ፊት ለማቅረብ በጥናት ላይ ተመስርቶ ባከናወነው ተግባር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ አያጣራ መሆኑን ሲያመለክት እንዳለው ማጅራት መቺዎቹ ” ስራ” እያሉ ነው ወንጀሉን የሚጠሩት።

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ኃይል በመጠቀም ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ/ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አንበሳ ጋራዥ አካባቢ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኦሮ 86853 ነጭ ሚኒባስ በመጠቀም ከአንድ ግለሰብ ላይ 10ሺ ብርና ግምቱ 14 ሺብር የሚወጣ ሞባይል ስልክ ሰርቀው ይሰወራሉ፡፡

ፖሊስ ጠንካራ ክትትል በማድረግ ወንጀል ፈፃሚዎቹን ከእነ ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር በማዋልና ምርመራ በማስፋት ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የሚፈፅሙ 14 ወንጀል ፈፃሚዎችንና የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 ኦሮ 79184 ሚኒባስ ተሽከርካሪን ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ /ም ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ አስታውቀዋል፡፡

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ግለሰቦች በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ በየካ ክፍለ ከተማና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወንጀሉን መፈፀማቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ወንጀል ድርጊት ተሳትፎ ያላቸው 19 ወንዶችና 6 ሴቶች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሁለት ሚኒ-ባስ መኪናዎች፤ ግለሰቦቹ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው 4 ልዩ ልዩ ተሸከርካሪዎች፣ 82 ሺ 680 ጥሬ ብር፣ 14 ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስማርት ስልኮችና የቀን ተቀማጭ የሚያስቀምጡበት ደብተር በኤግዚቢትነት እንደተያዘ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ አስረድተዋል፡፡

ግለሰቦች ምንም አይነት ህጋዊ ገቢ የሚያገኙበት ስራ የሌላቸው ቢሆንም ከፍተኛው በቀን 35 ሺ ብር አነስተኛው 5ሺ ብር የቀን ተቀመጭ ሲያደርጉ እንደነበር በኤግዚቢትነት ከተያዘው ሰነድ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተፈፀመባቸው ግለቦች አዲስ አበባ ፖሊስ ጉለሌ ክፍለ በመቅረብ በኤግዚቢትነት ከተያዙ ስልኮች መካከል መምረጥ እንደሚችሉ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ አስታውቀዋል፡፡

በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን ወንጀል የሚፈፅሙ ወንጀለኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው ወንጀሉን እንደሚፈፅሙና ተሳፋሪውን የትነው የምትሄደው የሚል ጥያቄ እንዲሚያቀርቡ ህብተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስበዋል።

Exit mobile version