Site icon ETHIO12.COM

ክንፈ ዳኘው በቀረበባቸው ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተባሉ

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ከ11 ራዳሮች ግዢ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ የጥፋተኝነት ፍርዱን ያስተላለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

በፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ/ም ላይ ጥራቱን ያልጠበቀ 11 ራዳር በ214 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በመግዛት በመንግስት ላይ ጉዳት ደርሷል በሚል በአራት ተከሳሾች ላይ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኃን የመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ተከሳሾቹ 1ኛ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው፣2ኛ ሌተናል ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት፣ 3ኛ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ እና 4ኛ የስነምግባርና የሕግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሃን አብርሃ ሲሆኑ ÷ክሱ ከቀረበ በኃላ ግን የሜጀር ጀኔራል ክንፈ እና የኮሎኔል መሐመድ ብርሃን መዝገብ ብቻ ሲቀጥል የሌሎቹ ክስ በተለያዩ ምክንያቶች እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ይህም÷ በወቅቱ ቀርቦ የነበረው ክስ ላይ ተከሳሾቹ የብረታ ብረታና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ፣ በኮርፖሬሽኑ የሃይቴክ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ የቦርድ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የኮርፖሬሽኑ የሥነ-ምግባርና የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከግዢ መመሪያ ውጭ ጥራታቸውን ያልጠበቁ 11 ራዳሮችን ከ214 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመግዛት በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ በከባድ የሙስና ወንጀል በሚል ነበር ክሱ የቀረበው።

ተከሳሾቹ በ2004 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ የግዢ መመሪያ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የግዢ ፈፀሚው አካል ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ጥራት ባለው በተቀላጠፈና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በተወዳዳሪ ዋጋ በጨረታ መፈፀም ሲገባቸው መመሪያውን ወደ ጎን በመተው ያለጨረታ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የግዢ ፍላጎት ሳይጠየቅ ሴሌክ እና አሊት ከተባሉ የቻይና ኩባንያዎች ተመሳሳይነት ያላቸውን 11 ራዳሮች መግዛታቸውን እና ራዳሮቹ አገልግሎት ሳይሰጡ መቀመጣቸው በክስ ተብራርቷል።

ከኮርፖሬሽኑ የግዢ መመሪያ ውጪ ያለጨረታና ያለግዢ ፍላጎት 2ኛ ተከሳሽ ሴሌክ ከተባለው ኩባንያ ጋር የገባውን ውል እንዲጸድቅ ለ1ኛ ተከሳሽ ደብዳቤ የጻፈ በመሆኑ እና 1ኛ ተከሳሽ ውሉን በማጽደቅ በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች በኩል የተፈረሙት ውሎች ጨረታ ሳይደረግ እና የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የግዢ ፍላጎት ሳይጠይቅ የተፈጸመ መሆኑ፣ እንዲሁም ውሉ ያለአግባብ እንዲፀድቅ መደረጉ በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ የቀረበውን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ክሱን በችሎቱ ላይ በንባብ አሰምቶ እንደነበር ተገልጿል።

ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው በበኩላቸው በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው÷ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን 8 የሰው እና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ካቀረበ በኋላ ችሎቱ የምስክር ቃልን እና ማስረጃዎችን መርምሮ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው በተከሰሱበት በወንጀል ህግ አንቀጽ 32 /1 ሀ እና አንቀጽ 411 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ እንደነበር ተመላክቷል ፡፡

በዚህም መሰረት ሜጀር ጀኔራል ክንፈ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳልኝ እና የቀድሞ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሳሞራ የኑስን ጨምሮ ከ5 በላይ የሰው የመከላከያ ምስክሮችን እና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበው ነበር።

በተከሳሹ የቀረቡ የመከላከያ ማስረጃዎችን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹ የዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸውን አብራርቷል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል። ።

በዚህም ፍርድቤቱ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 149/1 መሰረት የጥፋቸኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅም ለሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በተመሳሳይ የራዳር ግዢ የሙስና ክስ በ5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩት የሜቴክ የሕግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሃን አብርሃ የቀረበባቸውን ክስ በተገቢው ተከላክለዋል በሚል ከሁለት ሳምንት በፊት በነጻ መሰናበታቸው ይታወሳል።

EPD.

Exit mobile version