በኦሮሚያ ስልጣናቸውን በመጠቀም በተጭበረበረ ሰነድ በሰንሰለት በሲሚንቶ ሌብነት በተያዙ ላይ ፍርድ ተሰጠ

  • ከባንክ፣ ገቢዎች፣ ከአስተዳደ፣ ከጸጥታ፣ ንግድ ቢሮ፣ ገንዘብ ጽህፈት ቤት .. በሌለ ማህበር ስም በሰነሰለት የባለስልጣንን ስም በመጠቀም የሃሰት ማስረጃ በማደራጀት ሲሚንቶ ከማምረቻ በማውጣት ሌበነት ሲፈጽሙ የቆዩ ናቸው

የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሲሚንቶ ንግድ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ስም ጭምር የሙስናና የማጭበርበር ወንጀል በፈጸሙ ተከሳሾች ላይ የቅጣት ዉሳኔ አስተላልፏል።

ኦቢኤን መጋቢት 29/2015 – ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ ከአንድ አመት እስከ 20 አመት የሚደርስ የእስራት ዉሳኔ እና እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት አስተላልፏል።

ተከሳሾቹ የተከሰሱት ስልጣንን በአግባቡ ባለመጠቀም: የመንግስትን ስራ አግባብ ባልሆነ መንገድ በመምራት: ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት እና በማታለል ወንጀል ሲሆን አንደኛ ተከሳሽ አቶ አዲሱ አንጋሳ በአራት ወንጀሎች ተከሷል።

ተከሳሹ የኦሮሚያ ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ የደህንነት ክትትል ሠራተኛ ሆኖ ሲያገለግል በነበረበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ስም የተለያዩ የማጭበርበር ወንጀሎችን ሲፈጽም እንደነበረ የክስ መዝገቡ ያመላክታል።

የክስ መዝገቡ ከሚሊኪ የሲሚንቶ አከፋፋይ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ጋር የተያያዘ ሲሆን ተከሳሹ በ2013 ዓ.ም በዱከም ከተማ ኮትቻ ቀበሌ ያለምንም ህጋዊ ፈቃድ: ስራ አጥ እና የቀበሌዉ ነዋሪ ያልሆኑ ግለሰቦችን በማደራጀት ሚሊኪ የሲሚንቶ ማከፋፈያ የተባለ ህገ ወጥ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር
መስርቷል። ተከሳሹ የማህበሩ አባል ባልሆነበት በማህበሩ ስም እና በራሱ ፊርማ ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሲሚንቶ ሲገዛ ቆይቷል።

በሚሊኪ የሲሚንቶ አከፋፋይ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ስም የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰቢያ ደረሰኝ በማሳተም መንግስትን 5 ሚሊዮን ብር የታክስ ገቢ እንዲያጣ አድርጓል።

ተከሳሹ ሁለት ግለሰቦችን በመቅጠር ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ17 ሚሊዮን ብር የ53 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ግዢም ፈጽሟል።

ከሲሚንቶ ሽያጭ ሲገኝ የነበረዉን ትርፍ በግል የባንክ አካዉንቱ ገቢ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በዚህም ወደ 11.8 ሚሊዮን ብር ያለአግባብ ተጠቅሟል።

አዲሱ አንጋሳ የተከሰሰበት ሁለተኛዉ ክስ ደግሞ 2ኛ ተከሳሽ ከሆነዉ ከወንድሙ ከአቶ ታደለ ነጋሳ ጋር የጸመዉ ወንጀል ነዉ።

See also  «…የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅዱ ከሽፏል»

ሁለቱ ተከሳሾች ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቡ ቅርንጫፍ በመሄድ ከሚሊኪ የሲሚንቶ አከፋፋይ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ጋር ተመሳሳይ ባልሆነ በተጭበረበረ ሰነድ የባንክ ሂሳብ በመክፈት እና 12 ሚሊዮን ብር በአካዉንቱ ላይ ገቢ በማድረግ እንዲመዘበር አድርገዋል።

በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበዉ አራተኛዉ ክስ እንደሚያሳየዉ
የቱሉ ጉዲና ማህበር ሃላፊ የሆኑትን ግለሰብ እኔ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ወንድም ስለሆንኩ መሬት እንዲሰጥህ አደርጋለሁ በማለት ያሳምናል።

ጉዳዩን ለማስፈጸም 2 ሚሊዮን ብር ለስራ ማስኬጃ ደግሞ ሁለት መቶ ሺህ ብር ይጠይቃል።

ግለሰቡም 60 ሺህ ብር ተበድሮ ለተከሳሹ ሰጥቶታል።

በ1ኛ ተከሳሽ በአቶ አዲሱ አንጋሳ ላይ የተከፈተዉ ሌላዉ ክስ ተከሳሹ የኦሮሚያ ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ የደህንነት ክትትል ሠራተኛ ሆኖ ሲያገለግል በነበረበት ወቅት የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ 332 ሺህ ብር ደሞዝና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች አግኝቷል የሚል ነዉ።

የኦሮሚያ ክልል አቃቤ ህግ በቀረቡት አራት ክሶች ላይ የሰዉና የሰነድ ማስረጃ በማቅረቡ የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት1ኛ ተከሳሽ አዲሱ አንጋሳን ጥፋት ፈጽመሃል ብሎታል።

ፍርድ ቤቱም መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት በተከሳሽ አዲሱ አንጋሳ ላይ የ20 አመት ጽኑ እስራትና የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ቀጥት ዉሳኔ አስተላልፎበታል።

2ኛዉ ተከሳሽ አቶ ታደለ አንጋሳ የሚሊኪ ሲሚንቶ ማከፋፈያ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ሊቀ መንበር ነኝ ብሎ ሲሰራ በነበረበት ወቅት ለዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዲመዘበር በማድረግ እና በንግድ ባንክ በመሄድ ተመሳሳይ ባልሆነ ሰነድ የባንክ አካዉንት እንዲከፈት በማድረግ ወንጀል ተከሷል።

በዚህም ተከሳሹ በሌለበት 12 አመት ጽኑ እስራትና የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ወስኖበታል።

3ኛ ተከሳሽ አቶ ወርቁ ጫላ የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነዉ ሲያገለግሉ በነበረበት ወቅት ባለቤታቸዉ ወ/ሮ መሠረት አለሙ የሚሊኪ ሲሚንቶ ማከፋፈያ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር አባል መሆኗን : 1ኛ ተከሳሽ አቶ አንዲሱ አንጋሳ ደግሞ የማህበሩ አባል እንዳልሆነ እያወቁ ለዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍ ባልተጠየቀበት ሁኔታ የሲሚንቶ ሽያጭ ደብዳቤ በመጻፋቸዉ 5 አመት እስራት እና 10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

See also  ዳግም ጦርነት እንዳይጀመር ስጋት የገባው ኢሰመኮ የማስጠንቀቂያ ጥሪ አሰማ

7ኛ ተከሳሽ አቶ ሚሊዮን ቶሎሳ በዱከም ከተማ የጎትቻ ቀበሌ የስራ ዕድል ፈጠራ ጽ/ቤት ሠራተኛ ሆነዉ ሲያገለግሉ በነበረበት ወቅት ስራ አጥ እና ህጋዊ ያልሆኑ ግለሰቦችን በማደራጀት የንግድ ፈቃድና የንግድ ምዝገባ ህጋዊ ፈቃድ እንዲያገኙ አድርገዋል ተብለዉ የተከሰሱ ሲሆን ተከሳሹ የተጣለባቸዉን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸዉ ጥፋተኛ ተብለዋል። ለዚህ ጥፋታቸዉም በአንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ዉሳኔ ተላልፎባቸዋል።

9ኛ ተከሳሽ አቶ ከተማ ጉቱ የዱከም ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት የንግድ ምዝገባ ሠራተኛ ሆነዉ ሲሰሩ በነበረበት ወቅት የግብር መክፈያ ቁጥር ሰጥተዋል ተብለዉ የተከሰሱ ሲሆን ተከሳሹ የተሰጣቸዉን የስራ ሃላፊነት በአግባቡ መዉጣት ባለመቻላቸዉ አንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እና የ10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

10ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ገነት ታደሰ የሆለታ ከተማ ገንዘብ ጽ/ቤት ሠራተኛ ሆነዉ ሳሉ ዱከም ከተማ ጎቲቻ ቀበሌ በመሄድ በማህበሩ ዉስጥ በመደራጀት እና ኦሮሚያ ዐቃቤ ህግ በመሄድ ለአቶ አዲሱ አንጋሳ ዉክልና በመስጠት የተከሳሾቹ ተባባሪ በመሆናቸዉ የተከሰሱ ሲሆን የአንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እና የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

12ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ኢየሩሳሌም ጌታሁን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቡ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሠራተኛ ሆና ስትሰራ በነበረበት ወቅት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ተመሳሳይ ያልሆነ ሰነድ ተጠቅመዉ በማህበሩ ስም የሂሳብ ቁጥር ለመክፈት ወደ ባንኩ በሄዱበት ወቅት ሰነዱን ተቀብለዉ በማህበሩ ስም የባንክ ሂሳብ ቁጥር በመክፈት የወንጀሉ ተባባሪ በመሆናቸዉ አንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እና የ4ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

13ኛ ተከሳሽ አቶ ካሳሁን ኩምሳ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቡ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ ሲሰሩ በነበረበት ወቅት በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ስም የተዘጋጀዉንና በ12ኛ ተከሳሽ ተዘጋጅቶ የቀረበላቸዉን የባንክ ሂሳብ ቁጥር በማረጋገጥ የተጣለባቸዉን የስራ ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ባለመቻል የተከሰሱ ሲሆን ተከሳሹ የአንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እና የ4ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ዉሳኔ ተላልፎባቸዋል። የሸገር ከተማ ፖሊስ መምሪያ 2ኛ ተከሳሽን ካለበት ቦታ በመያዝ ማረሚያ ቤት እንዲያስገባዉ ዉሳኔ አስተላልፏል።

See also  Statement delivered to the African Union Peace and Security Council (AUPSC) on the Current Situation in Northern Ethiopia

በኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የጸረ ሙስና ዳይሮክተሬት ዐቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ግዛቸዉ ዳኜ ህብረተሰቡ ከመሰል የማጭበርበር ወንጀሎች ራሱን እንዲጠብቅና የመንግስት ሠራተኞችም የተሰጣቸዉን የስራ ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ መክረዋል። በባንክ የሚገኝ 5 መቶ 65 ሺህ ብር ጨምሮ 8 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ተወርሶ ለመንግስት ገቢ እንዲደረግ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ወንድማገኝ አሰፋ ኦ ቢ ኤን ነው የዘገበው

Leave a Reply