Site icon ETHIO12.COM

ከአውሮፕላን አደጋ ተርፈው ለ40 ቀናት የአማዞን ጫካ ውስጥ የቆዩ አራት ህጻናት በህይወት ተገኙ

በኮሎምቢያ ከአውሮፕላን አደጋ ተርፈው ለሳምንታት የአማዞን ጫካ ውስጥ የቆዩ አራት ህጻናት በህይወት ተገኙ። ባለፈው ግንቦት መጀመሪያ ህጻናቱን፣ እናታቸውን እና ሁለት አብራሪዎችን የያዘችው ቀላል አውሮፕላን ጫካ ውስጥ በመከስከሷ የልጆቹ እናት እና ሁለቱ አብራሪዎቹ ህይወታቸው አልፏል።

ይህን ተከትሎም የጠፉትን የ13፣ 9፣ 4 እና የ1 አመት እድሜ ያላቸውን ህጻናት ለመታደግ በርካታ ወታደሮች እና የአካባቢው ሰዎች የተሳተፉበት የማዳን ዘመቻ ሲደረግ ነበር።

ልጆቹ እና እናታቸው ሲጓዙበት የነበረው ‘ሴሴና 206’ አውሮፕላን ከአራራኩዋራ ወደ ሳን ሆሴ ዴል ጉዋቪያር በመብረር ላይ ሳለም በሞተር ብልሽት ሳቢያ እንደተከሰከሰ ተገልጿል።

በአደጋው ህይወታቸውን ያጡት የሦስቱ ሰዎች አስከሬን አደጋው በደረሰበት ቦታ በሠራዊቱ የተገኘ ቢሆንም ልጆቹ ከአደጋው ተርፈው እርዳታ ለማግኘት ጫካውን ማሰስ በመጀመራቸው ሊገኙ አልቻሉም ነበር።

ህፃናቱ “ሁይቶ” የተባለ ማህበረሰብ ተወላጅ ሲሆኑ፤ ስለ ፍራፍሬ እና የጫካ ኑሮ እውቀት ያላቸው ስለሆኑ በህይወት የመቆየት እድል እንደሚሰጣቸው ተስፋ ተደርጎ ነበር።

የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ የህጻናቱ በህይወት መገኘት አስደናቂ ነው፤ በታሪክ ሲታወሱ የሚኖሩ የጀግንነት እና የጽናት ምሳሌ ይሆናሉ ብለዋል።

በኮሎምቢያ የመከላከያ ሚኒስቴር የተሰራጨው ቪዲዮ ህፃናቱ ከጫካው ረጃጅም ዛፎች ላይ በሄሊኮፕተር ሲወሰዱ አሳይቷል። በህይወት የተገኙት ህጻናት በኮሎምቢያ ዋና ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም ቢቢሲ ዘግቧል።

Exit mobile version