Site icon ETHIO12.COM

በቴሌኮም ዘርፍ ጤናማ የግብይት ስርዓትን መተግበር የሚያስችል የታሪፍ ስርዓት ተግባራዊ ይደረጋል

በቴሌኮም ዘርፍ ጤናማ የግብይት ስርዓትን መተግበር የሚያስችል የታሪፍ ስርዓት ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።

ወጪን መሰረት ያደረገው የታሪፍ ስርዓት፤ በአገልግሎት አቅራቢዎች መካከል የዋጋ አለመግባባት እንዳይፈጠር እንዲሁም ደንበኞች ላልተገባ ወጪ እንዳይዳረጉ የሚያስችል ነው።

ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ውድድር በሚኖርበት ወቅት ጣልቃ በመግባት ማስተካከል የሚያስችል ሲሆን ስርአቱን ለመዘርጋት ጥናት እየተጠናቀቀ ይገኛል ተብሏል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ባልቻ ሬባ ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ በቴሌኮም ዘርፍ በውድድር ላይ የተመሰረተ ጤናማ ገበያ ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።

ለዚህም ለቴሌኮም አገልግሎት ወጪን መሰረት ያደረገ የዋጋ መከታተያ ስርአት መዘርጋት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ለሞባይልም ይሁን ለመደበኛ ስልክ አገልግሎት ዋጋ በሚተመንበት ጊዜ፤ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚወጣው ወጪ ብቻ ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

የሞባይል አገልግሎት ገቢን ለቋሚ አገልግሎት መደገፊያና የሞባይል የድምጽ ገቢን ለኢንተርኔት መደጎሚያ ማዋል ከተወዳዳሪነት አንጻር አይፈቀድም።

በመሆኑም ስርዓቱ መዘርጋቱ ደንበኞች ያልተጠቀሙበትን ወጪ እንዳይከፍሉ ለመከታተል ያግዛል ነው ያሉት።

ስርዓቱን ለመዘርጋት ከመሰረተ ልማት መጋራት ጋር ላይ ያለውን ትክክለኛ ዋጋ ማወቅ የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ኢትዮ-ቴሌኮምና ሳፋሪኮም ከአንድ ኔትዎርክ ወደ ሌላው ሲደውሉ የሚያስከፍሉት 31 ሳንቲም ክፍያ ትክክለኛ መሆኑን ጥናቱ ይዳስሳል ብለዋል።

ይህም አሁን አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ተቋማት ላይ ጫና የማይፈጥር በቀጣይ ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉትን የሚያበረታታ መሆኑን ለማወቅ የሚያስችል ነው።

ጥናቱ ሙሉ ለሙሉ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ተጠናቆ ከ2016 በጀት አመት ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለው የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ ሂደቱን የሚያፋጥኑ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ለዲጂታል ልማት መለኪያ የሆኑትን ተደራሽነት፣ ክህሎትና አጠቃቀምን እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በማድረግ አገልግሎቱን ለማስፋት እየሰራች እንደምትገኝም ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮ-ቴሌኮም 69 ሚሊዮን እንዲሁም ሳፋሪኮም 3 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል።

ከሞባይል ድምጽ ተጠቃሚዎች ቀጥሎ በፍጥነት እያደገ ያለው የኢንተርኔትና ዳታ አገልግሎት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገልግሎት ሰጪዎች ከ33 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የፊክስድ ብሮድ ባንድ ወይንም መደበኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ከ600 ሺህ በላይ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት እድገት አስተዋጽኦ ያለው የቋንቋ ይዘትን ታሳቢ በማድረግ በአማርኛ፣ በአፋርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማሊኛና በትግርኛ ቋንቋዎች እንዲኖሩ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version